የተዘነጉት የኢትዮጵያ ወርቆች

0
89

በኢትዮጵያ ምድር በዓላት ሲመጡ የሚደምቁ፣ ከበዓላት መገባደድ ጋር አብረው የሚደበዝዙ በርካታ እሴቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የባህል ስፖርቶች ይጠቀሳሉ። በገጠሩ የሀገራችን ክፍል በስፋት የሚዘወተሩት ነገር ግን በከተማው ማህበረሰብ እና በዘመናዊው ትውልድ ዘንድ እንደ ኋላቀር ወይም ወቅታዊ የስፖርት ጨዋታ ብቻ ተደርገው የሚወሰዱት እነዚህ ስፖርቶች አሁን ላይ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።

በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ ውስጥ የባህል ስፖርቶች ያላቸው ቦታ እንደ በዓል ቀን ልብስ ነው። በዓመት አንዴ ወይም ሁለቴ ከሳጥን ወጥተው ይለበሳሉ፤ በዓሉ ሲያልቅ መልሰው ወደ ሳጥን ይገባሉ። የባህል ስፖርቶች የማንነት ማሳያ ከመሆን አልፈው የውድድር እና የገንዘብ ምንጭ የመሆን እድላቸው ሰፊ ቢሆንም እስካሁን ግን አልተሰራባቸውም። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት አቶ አዲስ ዓለም ምህረት ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ከወቅታዊ ጨዋታነት አልፈው ወደ ዘመናዊ የውድድር መድረክ ካልተሸጋገሩ ታሪካዊ ባለቤትነታችንን ለሌሎች አሳልፈን የምንሰጥበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የባህል ስፖርቶቻችን ዋነኛ ችግር ወቅትን ጠብቆ መከሰት እና መጥፋት ነው ያሉት አቶ አዲስ ዓለም  ኀብረተሰቡ ስለ ባህል ስፖርት ያለው አመለካከት መቀየር አለበት የሚል እምት አላቸው። ማህበረሰቡ የባህል ስፖርቶች እንደ ገጠሩ የሀገራችን ክፍል ጨዋታ ወይም በዓል ሲመጣ ብቻ የሚዘወተሩ አድርጎ ነው የሚያስባቸው ብለዋል። እናም ይህ አመለካከት እስካልተቀየረ ድረስ ስፖርቱን ማሳደግ እንደማይቻል ያሰረዳሉ።

በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች እና በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የሚዘጋጁ ውድድሮች ቢኖሩም ቀጣይነት እና ወጥነት ግን ይጎድላቸዋል። አንዳንዴ በዓመት ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ ውድድር ይደረጋል፤ አንዳንዴ ደግሞ ለባህል ስፖርት በጀት የለም ተብሎ ውድድሩ ይቋረጣል። የውድድር ሕጎቹም ወጥ አይደሉም።  ውድድሮች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ አሸናፊውን ለመለየት ዕጣ ይጣላል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ስፖርትን በዕጣ መወሰን የኋላቀርነት የመጨረሻው ጣራ ነው። እናም ሕጎችን ወጥ ማድረግ ቀዳሚው የቤት ሥራ መሆኑን የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ያብራራል።

የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች፣ የባህል አዋቂዎች እና የፌዴሬሽን አመራሮች፤ ለዓለም አቀፍ ውድድር የሚመች፣ አሸናፊ እና ተሸናፊን በግልጽ በብቃት የሚለይ ወጥ የሆነ የጨዋታ ሕግ ማጽደቅ አለባቸው- የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ምክረ ሀሳብ ነው። ስፖርቱ እንዲዘወተር እና እንዲያድግ ወደ ሊግ (League) ደረጃ ማሳደግ ቅንጦት ሳይሆን ግዴታ ነው ይላሉ አቶ አዲስ ዓለም። በየቀበሌው እና በየክፍለ ከተማው ወጥ የሆነ የውድድር መድረክ ከተፈጠረ ስፖርቱ ከበዓል ማድመቂያነት ወጥቶ ልክ እንደ እግር ኳስ  የብዙዎችን ቀልብ የሚስብ የገቢ ምንጭ እና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሆን ይችላል ተብሏል።

የባህል ስፖርቶቻችንን አለማዘመናችን የፈጠረው ትልቁ አደጋ የባለቤትነት መነጠቅ ነው። “ገና በካናዳ በኦሎምፒክ ተመዝግቧል፤ አይስ ሆኪን ያሳደጉት ከኛ በተወሰደው የገና ጨዋታ መሰረት ነው” ይላሉ  የስፖርት ሳይንስ መምህሩ አዲስ ዓለም። አሁን ደግሞ ተረኛው ገበጣ ሆኗል ይላሉ። ብራዚል የገበጣን ጨዋታ በራሷ ስም ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ እያደረገች እንደሆነ አቶ አዲስ ዓለም ምህረት አስረድተዋል። “ብራዚል እየወሰደችብን ነው፤ በቅርቡ ታስመዘግበዋለች። እኛ ግን ዝም ብለናል” ይላሉ።

የባህል ስፖርቶች ከመዝናኛነት ባሻገር ለህጻናት አዕምሮ እድገት እና ለትውልድ ግንባታ ያላቸው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው። አቶ አዲስ ዓለም በጎንደር ቋራ አካባቢ ያሉ ህጻናት ገበጣን፣ ሻህን እና ቡብን ሲጫወቱ የሚያሳዩት የአዕምሮ ፍጥነት እና የውሳኔ አሰጣጥ ክህሎት እጅግ የሚገርም ነው ሲሉ ትዝብታቸውን አጋርተውናል። ባህል ስፖርቶች መሰረት ትምህርት ቤቶች ሊሆኑ ይገባል። ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች የባህል ስፖርት አካዳሚዎችን በመክፈት ህጻናትን በሳይንሳዊ መንገድ ማሰልጠን እንዳለባቸው አቶ አዲስ ዓለም ይጠቁማሉ ።

“ህጻናት ታዳጊዎች ላይ ከተሰራ ጥሩ ውጤቱ ይመጣል” የባህል ስፖርቶችን በስርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት ስፖርተኞችን ማፍራት ብቻ ሳይሆን የልጆችን የማሰብ እና የመወሰን ክህሎት ማዳበር ይቻላል የሚል እምነትም አላቸው የስፖርት ሳይንስ መመህሩ። የባህል ስፖርትን ማዘመን ማለት ትልቅ ወጪ የሚጠይቅ ስታዲየም መገንባት ማለት አይደለም፤ ለእግር ኳስ ማሰልጠኛ ተብለው የሚሰሩ 40 በ 40 ሜትር ሜዳዎች ለገና ጨዋታ በቂ በመሆናቸው ስታዲየም ወይም ሜዳ ሲሰራ የባህል ስፖርቶችን ታሳቢ ማድረግ ይገባል ነው የተባለው።

የባህል ስፖርቶች የቱሪስት መስህብ እና የብራንድ ማስተዋወቂያ ማድረግም ይቻላል። ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ስፖንሰር እንዲያደርጉ፣ ስፖርቱ ሳቢ እና ብዙ ተመልካች ያለው መሆን አለበት። ይህ ደግሞ ታሪካችን እና እሴታችን እንዳይጠፋ ከማድረግ ባሻገር ስፖርቱ የራሱ የሆነ የንግድ ምልክት (Brand) እንዲኖረው ያስችለዋል።

አሁን ያለው የባህል ስፖርት አመራር እና አደረጃጀት የሚፈለገውን ያህል ጠንካራ አለመሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን ችግሩን ለመፍታት ጥልቅ ጥናት እና ምርምር እንደሚያስፈልግ አቶ አዲስ ዓለም ያምናሉ። “ዩኒቨርሲቲዎች እና የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች የሚሰሩትን ምርምር መደርደሪያ ላይ ከማስቀመጥ ይልቅ ወደ መሬት ወርዶ ሊተገበር ይገባል” ነው ያሉት።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here