የተጓተቱት ፕሮጀክቶች

0
111

በደቡብ ጐንደር ዞን ፎገራ ወረዳ  በግብርና ሙያ ከሚተዳደሩ አርሶ አደሮች አንዱ እንደነገሩን በመስኖ የሚያለሙት አንድ ነጥብ አምስት ሄክታር /ስድስት ቃዳ/ የእርሻ መሬት አላቸው፡፡ አርሶ አደሩ በጄኔሬተር ውኃ እየሳቡ በመስኖ በማልማት ተጠቃሚ ናቸው፡፡ በ2000 ዓ.ም ደግሞ እያገኙ ካሉት ትርፍ በላይ ምርት የሚያስገኝ ዘመናዊ የመስኖ ግድብ በአቅራቢያቸው ተጀምሮ በ2004 ዓ. ም እንደሚጠናቀቅ  ሰሙ፡፡  “በወቅቱ ’የርብ ወንዝ ተገድቦ ለመስኖ ልማት ሊውል ነው’ መባሉን ስሰማ ይህን ሳላይ እንዳልሞት!” ማለታቸውን በኵር ጋዜጣ በመስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም ዕትሟ አስነብባለች፡፡

በኵር ጋዜጣ የርብ ግድብ ይጠናቀቃል በተባለበት በ2004 ዓ.ም የግንባታውን ሂደት በድጋሚ በሕዳር 25 ቀን 2004 ዓ.ም ማስነበቧ ይታወሳል፡፡ ዘገባው እንደሚያመላክተው በወቅቱ የግንባታው ክንውን 25 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ለዕቅዱ አለመሳካትም በወቅቱ የነበሩት  የቢሮ መሀንዲስ ከዕቅዱ ውጭ የተፈጠሩ ሥራዎች እና የግንባታ ቁሳቁሶች ዋጋ መናርን  በምክንያትነት አንስተው ነበር፡፡

በወቅቱ አጠራር የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒሥቴር በበኩሉ ግድቡ ጥሩ መሠረት ባለማግኘቱ የዲዛይን ለውጥ ተደርጓል፡፡ ይህን ተከትሎም የመሠረት ሥራው እና ሙሊቱን የሚሠሩ ባለሙያዎችን ከውጭ ማስመጣት በማስፈለጉ እና እነሱን ለማስመጣት ረጅም ጊዜ በመውሰዱ ግድቡን በታቀደለት ጊዜ ማጠናቀቅ አለመቻሉን አሳውቋል፡፡

ከአንድ ዓመት በኋላ ግንቦት 12 ቀን 2005 ዓ.ም በኵር ጋዜጣ “ዘንድሮስ?” ስትል ጠይቃ ነበር፡፡ የወቅቱ የርብ ግድብ እና መስኖ ልማት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ እና መሐንዲስ የግንባታው ሂደት 39 በመቶ መድረሱን አሳወቁ፡፡ ለመዘግየቱም ካሁን ቀደም ከሚነሱት ምክንያቶች በተጨማሪ ተቋራጩ የሚያስፈልጉ የግንባታ መሣሪያዎችን አሟልቶ አለመግባቱን አንስተው ነበር፡፡ ይህንና ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት ግንባታው በ2006 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን አሳውቀው ነበር፡፡

የሁሉም አርሶ አደሮች ምኞት እንዲሳካ፣ ከክልሉ አልፎ ሕዝብን እና ሀገርን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችለው የርብ መስኖ ፕሮጀክት ከዳር እንዲደርስ  እየተከታተለች ምትዘግበው በኵር  ጋዜጣ “ፕሮጀክቱ ባለው ጊዜ ተጠናቆ ይሆን?” በማለት   በ2006 ዓ.ም መጋቢት 29 ዕትሟ ጠይቃ ግንባታው ገና 43 በመቶ ላይ መሆኑን አስነበበች፡፡

በወቅቱ የነበሩት የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ  በሠጡት አስተያየት “ግድቡ የተጓተተበት ምክንያት በጥራት እንዲሠራ ሲባል የዲዛይን ለውጥ በመደረጉ፤ በፊት የነበሩ የፕሮጀክቱ የሥራ ኃላፊዎች ትኩረት አለመስጠታቸው፤ የመሰረት ቁፋሮው ከተጠበቀው በላይ አስቸጋሪ መሆኑ፣ የመቆፈሪያ (መሠርሠሪያ) ማሽን እጥረት መኖሩ፣ የግንባታ ቁሳቁሶች አቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ጭማሪ በማጋጠሙ ነው” የሚል ነበር፡፡ ግንባታው መቼ እንደሚጠናቀቅ እንደማይታወቅም አስተያታቸውን ሠጥተዋል፡፡

የውኃ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒሥቴር የመስኖ ዘርፍ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት በበኩሉ “አሁን ግን ዋጋ ስለተስተካከለላቸው እንደማንኛውም ሥራ ተቋራጭ ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ግዴታቸውን ካልተወጡ ሕጋዊ ርምጃ ይወሰድባቸዋል በሚል ተስማምተናል፡፡ እነሡም በዚህ መንፈስ ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት፡፡ አሁን እያከናወኑት ያለው ሥራም በመሀል ችግር ካልተፈጠረበት በስተቀር በ2008 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ የርብን ግድብ ሥራውን እንጨርሳለን የሚል ዕቅድ ነው ያለው” በማለት አረጋግጠው ነበር፡፡

ነገር ግን በ2000 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ፕሮጀክት ከ10 ዓመት በኋላ የግድብ ሥራው ቢጠናቀቅም ለመስኖ ልማት የሚሆነው የአውታር (ካናል) ዝርጋታ ባለመጠናቀቁ  ለጓጉ አርሶአደሮች አገልግሎት መስጠት አለመጀመሩ ይታወሳል፡፡ በወቅቱም “ግድቡ ከተጀመረ አያል (ብዙ) ጊዜው ነው፡፡ ታላላቆቻችን ’ሳናየው እንዳንሞት’ ይላሉ፤ እኛም ደግሞ ግድቡን ሳናየው፤ ሳንጠቀምበት ልንሞት ነው እያልን ሠግተናል፡፡ ግድቡ ቢጠናቀቅማ በኀይል ነበር አልምተን የምንጠቀመው” በማለት አርሶ አደሮች ከ10 ዓመት በኋላ /በ2010 ዓ.ም/ ያልተሟጠጠች ተስፋቸውን እና ስጋታቸውን  በኵር መዘገቧ ይታወሳል፡፡

ይሁንና የመስኖ ልማት ሰፊ አቅም ያላቸው ርብን ጨምሮ በዋናነት የጎንደርን ነዋሪዎች የውኃ ጥም ይቆርጣል ተብሎ በ2001 ዓ.ም የውል ስምምነት የተፈፀመበት የመገጭ እና ሌሎች የመስኖ፣ የመንገድ …ፕሮጀክቶች ዛሬም ድረስ ተጠናቀው ለአገልግሎት ባለመዋላቸው ከወረዳ እስከ ፌዴራል በሚካሄዱ ጉባኤዎች በመልካም አስተዳደር ችግር ሳይነሱ የማይቀሩ ጥያቄዎች ሆነው ዘልቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የማይቀሩት የርብ፣ የመገጭ …የመስኖ እና ሌሎች ግንባታዎች  አፈጻጸም መዘግየትም ከሰሞኑ በተካሄደዉ የክልሉ ምክር ቤት  ጉባዔ በተወካዮቻቸው ተነስቶ ነበር፡፡ የላይኛው እና የታጭኛው ርብ፣ የጣና በለስ የስኳር ፕሮጀክት አሁንም ድረስ ግንባታቸው አለመጠናቀቁ ተገልጿል፡፡  ሆኖም የመካከለኛ እና ሜጋ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማስቀጠል የአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ ቢሮ ብቻውን ስለማይችል የሚያደርገው ጥረት እንደ ተጠበቀ ሆኖ የበላይ አካላትም ከቢሮው ጋር እየገመገሙ በመምራት እገዛ እንዲያደርጉ  ተጠይቀዋል፡፡ መገጭን በተመለከተም በቅርቡ በልዩ ድጋፍ ግንባታው መቀጠሉን የቢሮው ኃላፊ ለምክር ቤት አባላቱ አሳውቀዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው የክልሉን መንግሥት የስድስት ወራት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ የ2017 ግማሽ በጀት ዓመት የክልሉን የወጪ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደተናገሩት ከጸደቀው 150 ነጥብ 6 ቢሊዮን በጀት ውስጥ ባሳለፍናቸው ስድስት ወራት 34 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጭ ተደርጓል።

ከዚህ ውስጥ ለመደበኛ ሥራዎች ማስፈጸሚያ 30 ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር ወጭ ተደርጓል። ቀሪው 3 ነጥብ 59 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለካፒታል ሥራዎች የወጣ ስለመሆኑ ለምክር ቤቱ ጠቁመዋል። ያለውን ውስን ሃብት በመጠቀም የተጀመሩ የካፒታል ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ በዚህ ዓመት ለመመረቅ እና ወደ ልማት ለማስገባት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።

ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል 17 ነጥብ 43 ቢሊዮን ብር መመደቡንም ተናግረዋል። 1 ሺህ 40 የሚሆኑት ፕሮጀክቶች በ2017 በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቁም ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገልጸዋል፡፡

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here