የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ወደ ማልማት ተሸጋግረዋል ተባለ

0
150

በ2017 በጀት ዓመት በ815 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡት 16 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ወደ ልማት መሸጋገራቸውን የሰሜን ሸዋ ዞን መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ ችሮታው አስፋው ለአገልግሎት የበቁት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ለዘመናት የመልካም አሥተዳደር ችግር ሲነሳባቸው የነበሩ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶቹ ከአራት ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት  የሚችሉ  መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ከስምንት ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

ከ16ቱ የመስኖ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ 63 አነስተኛ ጉድጓዶችም ተዘጋጅተዋል፡፡ እነዚህም ከ240 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ በአጭር ጊዜ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ መጨረስ ላይ የተሠራው ሥራ ተሞክሮ ሊወሰድበት የሚገባ ተግባር መሆኑንም  ጠቅሰዋል።

 

በዓመቱ በተከናወኑ የመስኖ አውታር ግንባታዎች ከዘጠኝ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በጊዜያዊ እና በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም መምሪያ ኃላፊው ተናግረዋል።

ግንባታዎቹ ከዘላቂ ልማት ግብ፣ ከምግብ ማጠናከሪያ ሥርዓት መርሐ ግብር፣ ከሰቆጣ ቃልኪዳን እና ከሴፍቲኔት በተገኙ የገንዘብ አማራጮች የተሠሩ ናቸው።

ከሰቆጣ ቃል ኪዳን በተገኘ ድጋፍ በዞኑ ለሰባት የመስኖ ካናሎች (ግድቦች) ጥገና መደረጉንም አቶ ችሮታው ገልጸዋል።

መምሪያው በ2018 በጀት ዓመት 151 ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስችል የፕሮጀክት ጥናት እና ዲዛይን ሥራ አጠናቅቆ በጀት በማፈላለግ ላይ ይገኛል።።

 

(ገንዘብ ታደሰ)

በኲር የሐምሌ 7  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here