በደች የጥበብ ስራ ውጤቶች ቤተመዘክር አዲስ የተቀጠረ የጥገና ባለሙያ፤ አሳንሰር ውስጥ ያገኛቸውን ታዋቂ የጥበብ ሥራዎች አሮጌ የቢራ ማሸጊያ ጣሳ ናቸው በሚል በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ ጥሏቸው መገኘታቸውን ኦዲት ሴንትራል አስነብቧል፡፡
“አብረን ያሳለፍ ናቸው መልካም ጊዜያት” የሚል ርእስ የተሰጣቸው በፈረንሳያዊው ሰዓሊ አሌክሳንደር ላቬት የተሰሩት የቅብ ውጤቶች በ “LAM’’ ቤተመዘክር ነበር የተቀመጡት፡፡ “LaM” የጥበብ ውጤቶች ቤተመዘክር የጥበብ ውጤቶችን ባልተለመደ ቦታ በማኖር ለእይታ በማብቃት ነው የሚታወቀው፡፡
በጥበብ አድናቂዎች የአሌክሳንደር ላቬት የጥበብ ውጤቶች መጀመሪያ ሲታዩ የተጣሉ፣ የተጠረማመሱ የቢራ ጣሳዎች ሊመስሉ እንደሚችሉ እና በቅርበት በትኩረት ሲመረመሩ ግን በ “acrylic” ልዩ ቀለም በእጅ የተቀቡ ውድ የጥበብ ስራዎች መሆናቸው ሊታወቅ እንደሚችል ነው በጽሁፉ የተገለፀው፡፡
በመሆኑም አዲሱ ተቀጣሪ የአሳንሰር ባለሙያ ሁለቱን የአልሙኒዬም ጣሳዎች እንዳያቸው ውዳቂ ቆሻሻ መስለውት ሊጥላቸው እንደቻለ ጽሁፍ አመላክቷል፡፡
የ “LAM” ቤተመዘክር ሥራ አስኪያጅ ሲይትስክ ቫንዛንቲን ቤተመዘክሩ “የጥበብ ጐብኚዎች የእለት ተእለት ቁሶችን በአዲስ ብርሃን እንዲመለከቱ ያበረታታል፡፡ የጥበብ ስራዎችን ባልተጠበቁ ቦታዎች በማሳየት ልምዱን ማሳደግ እና ማስቀጠል እንፈልጋለን፤ ዓላማችን ይሄው ነው” ሲሉ ተናግርዋል፡፡
የቅብ ስራዎቹ መጥፋት መታወቁ መልካም አጋጣሚ እንደነበር ያስነበበው ድረ ገጹ ከአጭር የእረፍት ጊዜ በኋላ ወደ ስራው የተመለሰ የቤተመዘክሩ ባለሙያ ስራዎቹን በተመረጠው የማሳያ ቦታ እንዳጣቸው እና ሲያፈላልግ በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ እንዳገኛቸው ነው የተብራራው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም