የተጫዋቾች አጃቢ

0
189

እርስዎ የእግር ኳስ ደጋፊ ላይሆኑ ይችላሉ፣ ቢሆንም በተለያየ አጋጣሚ እግር ኳስን ተመልክተው የሚያውቁ ከሆኑ ታዳጊ ሕፃናት ከተጫዋቾች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደ ሜዳ ሲገቡ ተመልክተው ይሆናል። አሁን ላይ ይህ ድርጊት በዓለማችን የአራቱም ማዕዘን ባህል ሆኗል። ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት ከተጫዋቾች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚገቡ ሕፃናትም የተጫዋቾች አጃቢ (Child Mascot) ይባላሉ።

ታዳጊ ሕፃናትን ይዞ ወደ ሜዳ መግባት እ.አ.አ በ1970ዎቹ በብራዚል እንደተጀመረ የዘጋርዲያን መረጃ ያመለክታል። በአትሌቲኮ ሚኒሮ እና በአሜሪካ ሚኒሮ መካከል በተደረገው ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕፃናት ተጫዋቾችን አጅበው ወደ ሜዳ መግባታቸውን ታሪክ ይነግረናል። የታዳጊ ቤተሰቦችን ጨምሮ ሌሎች ደጋፊዎች ወደ ሜዳ እንዲመጡ እና ጨዋታውን እንዲከታተሉ ታስቦ ነበር በወቅቱ የተጀመረው።

በተለያየ አጋጣሚ ተጫዋቾች ለጨዋታ ወደ ሜዳ ሲገቡ  ልዩ ልዩ አጃቢዎች እንደነበራቸው ታሪክ ያስረዳል። ለአብነት የአያክስ አምስተርዳም ተጫዋቾች በእናቶች ቀን ከእናቶቻቸው ጋር ወደ ሜዳ ገብተው ታይተዋል። የብራዚሉ ሳኦ ፖሎ ክለብ ተጫዋቾች በውሾች ላይ የሚደርሰውን አካላዊ ጥቃት ለመከላከል እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ለመሥራት ከውሾች ጋር ወደ ሜዳ መግባታቸውም በታሪክ ተጽፏል።

የተጫዋቾች አጃቢ ሕፃናት ከስድስት እስከ 18 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ናቸው። እነዚህ ታዳጊዎች ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ከተጫዋቾች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ወይ አብረው የክለቡን ወይም የብሔራዊ ቡድኑን መዝሙር ይዘምራሉ። እ.አ.አ በ1990ዎቹ ሁለቱ ተጋጣሚ ቡድኖች ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ አጃቢ ሕፃናትን ብቻ ነበር ይዘው ወደ  ሜዳ ይገቡ የነበረው። ለአብነት በ1996 እ.አ.አ በመርሲሳይድ ደርቢ ሊቨርፑል እና ኤቨርተን በተጫወቱበት ጊዜ የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትዱ ተጫዋች ዋይኒ ሩኒ ለኤቨርተን ቡድን አጃቢ በመሆን ወደ ሜዳ ገብቶ ነበር። በታዳጊነት ዘመኑ የተጫዋቾች አጃቢ የነበረው ዋይኒ ሩኒ በመጨረሻ ህልሙን አሳክቶ ኮከብ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል።

ከፈረንጆቹ ሚሊኒየም ወዲህ ደግሞ ለሕጻናት ደስታን የሚያጎናጽፈው ይህ  መልካም ድርጊት የተለየ ትርጉም እና ትኩረት እየተሰጠው ይገኛል። ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ በጥምረት ባዘጋጁት እ.አ.አ በ2002ቱ የዓለም ዋንጫ ፊፋ እና ዩኒሴፍ “ለሕፃናት አዎ ይበሉ” (say yes to children) በሚል መፈክር የሕፃናትን መብት ለማስጠበቅ አብረው  በዘመቻ መሥራታቸውን መረጃዎች አስነብበዋል። እንደ መረጃው ከሆነ በዘመቻው ለሕፃናት ተስማሚ የሆነች ዓለም ለመገንባት ታስቦ ነው።

የሕፃናትን መብት ዘመቻ ማስተዋወቅ፣ የስፖርታዊ ጨዋነትን ማስፈን፣ የሕፃናትን ህልም ማሳካት እና በተለይ ለአካል ጉዳተኞች ደግሞ ሁሉም ከጎናቸው እንደሆኑ ድጋፋቸውን ማሳየት ነው ሁለቱ ግዙፍ ተቋማት የተስማሙት። በሌላ ጎኑ ደግሞ ከተጫዋቾች አጠገብ ሕፃናት ካሉ ደጋፊዎች አደጋ የመፍጠር ዕድላቸው አነስተኛ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው መረጃው ያክላል።በአጠቃላይ ዓላማው ግን የተወሰነ አለመሆኑን ተገልጿል። ሕዝባዊነትን ያጎለብታል፤ ለቤተሰብ ተስማሚ የሆነ ድባብ እና የማኅበረሰብ ተሳትፎን ለማሳደግም ይጠቅማል።

እ.አ.አ በ2014 ዘጋርዲያን ባወጣው ጥናት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አብዛኞች ክለቦች የተጫዋቾች አጃቢ የሚኖራቸው ሲሆኑ ከ450 እስከ 600 ፓውንድ ገንዘብ ያስከፍላሉ። ለታዳጊዎችም ክለቡ ሙሉ መስተንግዶ፣ ነፃ የስቴዲየም መግቢያ ትኬት፣ የተጫዋቾች ፊርማ ያረፈበት ኳስ እና ሌሎች ተጨማሪ ስጦታዎች ይበረከትላቸዋል። እ.አ.አ በ2014 በብራዚል  በተደረገው  የዓለም ዋንጫ ዓለም አቀፉ ማክዶናልድ ድርጅት ከ70 የተለያዩ ሀገራት የተመረጡ 1 ሺህ 408 ሕፃናትን ወጪ በመሸፈን የተጫዋች አጃቢ ሆነው በእያንዳንዱ ጨዋታ እንዲገቡ አድርጓል።

አሁን አሁን ሕፃናት ከተጫዋቾች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደ ሜዳ መግባት በዘመናዊ እግር ኳስ ባህል ሆኗል። ይህን ባህል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ለሰብአዊ ዓላማ አገልግሎት ላይ እንዲውል እያደረጉት ነው። ልጆች በተቻለ መጠን የተሻለ ህይወት እና ትምህርት እንዲያገኙ ይህ ድርጊት ያበረታታል። አለፍ ሲልም ታዳጊዎች በእግር ኳስ ስፖርት ከሚያደንቋቸው ከስፖርቱ ሰዎች ጋር ልዩ ጊዜ እንዲያሳልፉ በር ይከፍታል።

ታዳጊ ተጫዋቾች  እንደ ሊዮኔል ሜሲ እና  ክርስቲያኖ ሮናልዶ ያሉ ተጫዋቾችን ሜዳ ላይ ሲመለከቱ፣ እጃቸውን ሲጨብጡ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል ለመገመት አያዳግትም። ታዲያ ይህን የተረዱት በርካታ የአውሮፓ ክለቦች አጋጣሚውን ለበጎ አድራጎት ሥራ እየተጠቀሙበት ጭምር ነው። ይህን ሥራ በዋናነት ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች በመስጠት በተለይ የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸው፣ አካል ጉዳተኞች እና በአጠቃላይም ሕሙማን ታዳጊዎች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል። ይህ ደግሞ ለሕሙማን ህፃናት ገደብ የሌለው ደስታ እና ተስፋን ያለመልማል።

ግላስኮ ላይቭ የተባለው ድረ ገጽ እንዳስነበበው የስኮትላንዱ ክለብ ሬንጀርስ ደጋፊ የሆነው የአምስት ዓመቱ ሌይተን ስቲል የአዕምሮ ውስንነት ያለበት፣ ዐይነ ስውር እና በበርካታ ውስብስብ የጤና ችግሮች ምክንያት ዕድሜውን ሙሉ በሆስፒታል ማሳለፉን ያስነብባል። ሕፃን ሌይተን ከሆስፒታል ሕክምናውን ጨርሶ ሲወጣ የሬንጀርስ ተጫዋቾች አጃቢ ሆኖ ወደ ሜዳ መግባት እንደሚፈልግ ለቤተሰቦቹ ደጋግሞ ይናገር ነበር።

ሲያድግም እግር ኳስ ተጫዋች መሆን እንደሚፈልግ ቤተሰቦቹን ጠቅሶ ግላስኮ ላይቭ አስነብቧል። የታዳጊውን ህልም ለማሳካትም ሬንጀርስ ጨዋታውን ሲያከናውን በዊልቸር ታግዞ ተጫዋቾችን በማጀብ ሜዳ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል። ሕፃኑ ሌይተን ከተጫዋቾች ጋር ወደ ሜዳ ሲገባ  ያሳየውን ፈገግታ ሊገልጸው ከሚችለው በላይ ደስታ እንደፈጠረለት ወላጅ አባቱ በቃለ መጠይቁ   ተናግሯል።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ቤተሰቡ ከሚያስታውሳቸው የተጫዋቾች አጃቢ(palayers mascot) ውስጥ የቀድሞው የሰንደርላንዱ ሕፃን ብራድሌይ ሎሪ ቀዳሚው ነው። ብራድሌይ በወቅቱ የስድስት ዓመት ሕጻን ነበር፣ የሰንደርላንድ ቀንደኛ ደጋፊ እና ወዳጅ ናቸው ከሚባሉት ውስጥ ስሙ በቀዳሚነት በክብር መዝገብ ተቀምጧል። በተጫዋቾች እንዲሁም በአጠቃላይ በክለቡ የቡድን አባላት የሚወደድ ደጋፊ እንደነበር የሜል ስፖርት መረጃ ያሳያል።

በተለይ ደግሞ ከቀድሞው የክለቡ ተጫዋች ጀርሜን ዴፎ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው ይባላል። ብራድሌይ ሎሪ ለበርካታ ጊዜያት የተጫዋቾች አጃቢ በመሆን ወደ ሜዳ ገብቷል። በተለይ ደግሞ በ2013 እ.አ.አ የካንሰር ታማሚ ከሆነ በኋላ ክለቡ እና ቤተሰቦቹ በምድር ላይ ያለውን ቀሪ ዕድሜ በሚወደው እግር ኳስ እንዲያጣጥም አድርገዋል። በየጨዋታውም የሰንደርላንድን ተጫዋቾች በማጀብ ወደ ሜዳ ይገባ ነበር። ሕፃን ልጃቸው በታህሳስ 2016 ህይወቱ እንደሚያልፍ በዶክተሮች የተነገራቸው ቤተሰቦቹ በቀረችው አጭር ጊዜ ህልሙን እንዲያሳካ አድርገዋል።

እስከ ህልፈተ ህይወቱ ጊዜ ድርስም የክለቡ ተጫዋቾች ከጎኑ በመሆን ያላቸውን ፍቅር አሳይተውታል። የክለቡ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆኑ ታሪኩን የሰማው ሰፊው  የእግር ኳስ ቤተሰብም በብራድሌይ ልቡ መነካቱን ሜል ስፖርት ዘግቧል። ሰንደርላንድ እግር ኳስን ለበጎ ኃይል በመጠቀም ለሌሎች አርዓያ የሚሆን ሥራ ሠርቶ አሳይቷል ተብሏል።

በእኛ ሀገርስ? ምላሹን ለአንባቢያን ትተን የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸውን፣ አካል ጉዳተኛ  እና በአጠቃላይ ሕሙማን ህፃናትን በማቅረብ ፍቅራችንን እና ድጋፋችንን በማሳየት በኩል ብዙ መሠራት ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ይታመናል። ታዲያ ብዙ ችግሮችን የመቀየር ኃይል ያለውን ተወዳጁን እግር ኳስ እንደ መሣሪያ  ተጠቅሞ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች መሠራት አለበት የሚል እምነት አለን።

ዘጋርዲያን፣ ሜል ስፖርትን እና ግላስኮ ላይቭን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here