የተፈራው፣ ግን አትራፊዉ የትግል ስልት

0
154

የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በተለይም ከ2013 ዓ.ም ወዲህ የገባችበት ግጭት እና ጦርነት ዛሬም ድረስ መልኩን እየቀያየረ መፍትሄ ርቆት ዘልቋል:: ኢትዮጵያ ሥረ ምክንያቶችን ለይታ ዘላቂ መፍትሄ ያልሰጠቻቸው ችግሮች እያስከተሉት ያለው ሰብዓዊ ጉዳት፣ ምጣኔ ሐብታዊ መሽመድመድ፣ የማኅበራዊ መስተጋብር መመሰቃቀል፣ የማኅበራዊ አገልግሎቶች መስተጓጎል እና ሌሎችም ከፍተኛ ነው::

በለንደን የኢኮኖሚክስ እና የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ቤት ውስጥ አጥኚ የሆኑት መብራቱ ከለቻ (ዶ/ር) እ.አ.አ ሰኔ 30 ቀን 2023 ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ለግጭቶች መባባስ ዋነኛው ምክንያት የፖለቲካ ፉክክር እና የሥልጣን ሽኩቻ መሆኑን አንስተዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም የፖለቲካ ትርፍን በኃይል ለማሳካት የሚደረግ ጥረት ፍጹም እንደማይሳካ፣ ነገ እንመራሀለን የሚሉትን ሕዝብ እያገቱ እና እያሳደዱ ማሰቃየት ጉንጭ አልፋ ከመሆን የዘለለ እንደማይሆን በተለያዩ መድረኮች ሲናገሩ ይደመጣሉ::

የፖለቲካል ሳይንስ ባለሙያው የብሔር እና የእምነት ልዩነቶችን እንደ ማቀጣጠያ መጠቀም  ግጭቶች እንዲከሰቱ እና መፍትሄ ርቋቸው እንዲቀጥሉ ምክንያት እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

ሕዝብ የሚያነሳቸው ፍትሐዊ የኢኮኖሚ እና የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄዎች እንዲሁም ከወሰን እና ከማንነት ጋር የተገናኙ የሕዝብ ጥያቄዎች በሚፈለገው ጊዜ በመንግሥት በኩል ምላሽ ሳይሰጣቸው እየተንከባለሉ ከመቀጠላቸው በተጨማሪ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ኢትዮጵያ ሰላም እንዲርቃት አድርጓታል:: በእነዚህ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ግጭቶች እና ጦርነቶች በመሠረተ ልማት እና በተቋማት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ሕዝቡ ከመንግሥት የሚያገኘውን አገልግሎት እንዳያገኝ ያደርገዋል፤ ይህም ቀድሞውንም የግጭት ምክንያት ሆኖ ይነሳ የነበረው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንደ ገና አድማሱን አስፍቶ ለግጭቶች መባባስ ምክንያት ሲሆን ይስተዋላል::

በአጠቃላይ ግጭቶች የልማት ሥራዎች እንዲደናቀፉ፣ ምጣኔ ሐብታዊ እንቅስቃሴው እንዲዳከም በማድረግ ሕዝቡ ለከፋ ችግር እንዲጋለጥ ያደርገዋል:: የመንገዶች ደኅንነት መታወክን ተከትሎም በሸቀጦች እና በምርት ዝውውር ላይ የሚስተዋለው ችግር የኑሮ ውድነት የሕዝቡ ተጨማሪ ፈተና እንዲሆን ያደርጋል:: እነዚህ ሁሉ ችግሮች በአማራ ክልል ከ2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በተከሰተው የሰላም እና ደኅንነት መታወክ ምክንያት ተስተውለዋል::

ሁለተኛ ዓመቱን ይዞ የሚገኘው ግጭት እያደረሰ ካለው መጠነ ሰፊ ጉዳት ለመውጣት መንግሥት ለታጣቂ ኃይሎች የውይይት ጥያቄ ከማቅረብ ጀምሮ ሕዝቡ የሰላም ዘብ እንዲሆን የሚያደርጉ ውይይቶችን ሲያካሂድ ቆይቷል፤ ውይይቶቹ አሁንም ቀጥለዋል:: ግጭቱ ተማሪዎች ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ፣ መምህራን የተማረ ትውልድ ለመፍጠር ከሚያደርጉት የተወደደ ሙያ እንዲገለሉ፣ በመንገዶች መዘጋትም ይሁን በጤና ተቋማት ላይ በደረሰ ጉዳት የታመመው እንዳይታከም፣ ባለ ሐብቱ ከመኖሪያው ተፈናቅሎ ወደ ሌሎች አንጻራዊ ሰላም ወዳለባቸው አካባቢዎች እንዲሰደድ ማድረጉን የክልሉ መንግሥት በተለያዩ መድረኮች አስታውቋል::

ሕዝቡ የልጆቹ ከትምህርት ውጪ መሆን ያንገበግበዋል፤ በነጻነት መንቀሳቀስንም ናፍቋል:: በየትኛውም የክልሉ አካባቢ ሠርቶ ኑሮን የተሻለ ማድረግ ናፍቋል፤ ከምንም በላይ ደግሞ በየጊዜው የሚሰማው የሐዘን መርዶ እንዲያከትም ይፈልጋል፤ ለዚህም የሰላም ችግሩ በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ ያገኝ ዘንድ ከመንግሥት ጋር እያደረገ ባለው የሰላም ሕዝባዊ የምክክር መድረኮች በተደጋጋሚ ጠይቋል::

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ከላላ ወረዳ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች ስለ ሰላም እና ለዘላቂ ሰላም ከሕዝቡ ምን እንደሚጠበቅ ጠይቋል:: የሃይማኖት አባቶቹም እስካሁን የደረሰው ጉዳት እንዳይቀጥል፣ ውስጣዊ ችግሩም ለውጭ ጠላት በር እንዳይከፍት ልዩነቶች በንግግር መቋጫ ሊያገኙ እንደሚገባ ጠይቀዋል::

ሐሳባቸውን ለአሚኮ ካጋሩ የሃይማት አባቶች መካከል አባ ላዕከማርያም እሸቱ ይገኙበታል፤ እስካሁን የደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ እና የሚያሳዝን መሆኑን ጠቁመዋል:: ግጭቱ ያደረሰውን ጉዳት ለመመለስ ጊዜን የሚፈጅ እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎችም እንዲቋረጡ ማድረጉን ገልጸዋል:: ክልሉ አሁንም ወደ ቁልቁለት እንዳይጓዝ ሁሉም አካል ሁሉም ነገር የሚሰምረው በሰላም መሆኑን ተረድቶ ለሰላም እንዲቆም ጠይቀዋል::

ሼህ አብዱሶመድ አሊ በበኩላቸው የሁሉም ነገር መነሻም ሆነ መዳረሻ ሰላም መሆኑን ገልጸው ሁሉም አቻ ለማይገኝለት ሰላም ዘብ እንዲቆም ጠይቀዋል:: ሕዝቡ ወደ ጥፋት እየሄዱ ያሉ ልጆቹን በመምከር መመለስ፣ ለአስተማማኝ ሰላም መስፈንም የመረጃ አካል ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል::

መንግሥትም ባለፈው አንድ ዓመት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያደረገው ጥረት መፍትሄ አለማምጣቱን በመግለጽ ችግሩን ለመፍታት ሕግ የማስከበር እርምጃ መውሰድ መጀመሩን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም የመከላከያ ሠራዊት ከክልሉ መንግሥት ጋር በመሆን በሰጡት መግለጫ ማሳወቃቸው ይታወሳል::

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛ ዓመት አራተኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት አሁንም ለሰላም ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጣቸው ይታወሳል:: መንግሥት ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ከሚፈልግ ማንኛውም አካል ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን መሀል ላይ ቆመው ጥረቱን ለማሰናከል የሚጥሩ አካላት ፈተና መሆናቸውንም ጠቁመዋል::

በጉባዔው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትጥቅ የታገዘ ግጭት ይዞት የሚመጣው መዘዝ ከፍተኛ መሆኑን ለማስገንዘብ አብነቶችን እያነሱ አስረድተዋል:: ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ላይ በተለያዩ ሀገራት የሚደረጉ የትጥቅ ትግሎች ይዘውት የሚመጡት ውድቀት እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን በትጥቅ ትግል ወደ ሀገር መሪነት የመጡ የበርካታ ሀገራት መሪዎች መኖራቸውን በማሳያነት አንስተዋል:: ለአብነት ቻይና በማኦ፣ ታንዛኒያ በኔሬሬ፣ ዛምቢያ በኬኔት ካውንዳ ነጻነታቸውን መጎናጸፋቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን እነዚህ መሪዎች መንበረ ሥልጣኑን ከመቆናጠጥ ባለፈ የሀገራቸውን ምጣኔ ሐብት ከነበረበት ከፍ ማድረግ እንዳልቻሉ ጠቁመዋል:: ለዚህም ዋና ምክንያት አድርገው ያነሱት የመሪዎች የቀደመ ባህርይ ሁሉንም በኃይል የማሳካት ልምምድ ኢኮኖሚውንም በኃይል ለመፍታት መሞከራቸው ነው:: በአንጻሩ በሰላማዊ ትግል ወደ ስልጣን የሚመጡ መሪዎች ደግሞ ሀገራቸውን ወደ ዕድገት ጎዳና እንዳስገቡ ሲንጋፖርን እና ኮሪያን በአብነት አንስተዋል::

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አላስፈላጊ መባላት ሀገሪቱን በእጅጉ እንደጎዳት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል:: ኢትዮጵያ ወደ ኋላ እንድትቀር፣ መሪዎች በሄዱበት ሀገር ሁሉ አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዳይናገሩ ከማድረግ ውጪ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ አለማምጣቱን ጠቁመዋል:: ኦነግ ባለፉት 50 ዓመታት በትጥቅ ትግል ውስጥ መቆየቱን፣ ነገር ግን ለኦሮሞ ሕዝብ የሰጠው ጥቅም እንደሌለ ገልጸዋል::

በሱዳን የተቀሰቀሰው እና 19 ወራትን የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ሱዳናያንን ከባድ ዋጋ እያስከፈላቸው ቀጥሏል፤ እልቂቱ ደግሞ ልዩነቶችን በንግግር ከመፍታት ይልቅ ስልጣንን ያስቀደመ በመሆኑ ነው:: የሱዳን የሰላም ችግር የተፈጠረው በሀገሪቱ ሠራዊት እና ራሱን ልዩ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ብሎ በሚጠራው ኃይል መካከል ሲሆን ዋና ዓላማውም የስልጣን የበላይነትን ለመቆናጠጥ ነው::

‘ሱዳን ሪሰርች ግሩፕ’ ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት መሠረት በቀጥታ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ 26 ሺህ ያህል ሱዳናዊያን ሞተዋል፤ የአብዛኛዎቹ ሞት ምክንያት ደግሞ ሕመም እና ረሃብ መሆኑን አስታውቋል::

እንደ መረጃው ከሆነ በግጭቱ ምክንያት ከ11 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ ተፈናቅለዋል:: ይህም ሠርቶ አደር እጆች ለልመና እንዲዘረጉ አድርጓል፤ ትምህርት ፈላጊ ታዳጊዎቿ ከትምህርት ርቀው የነገን የተሻለ መሆን ናፍቀውባታል::

ኀያላን የሚባሉት ሀገራት ግጭቱ መፍትሄ አግኝቶ ዜጎች እፎይ የሚሉበትን ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ ለሚደግፉት ወገን የሚያደርጉት ድጋፍ እና እገዛ ሱዳናዊያንን ዋጋ እያስከፈለ ነው::

ዛሬ ዓለም የኃይል ሚዛንን አይታ አሰላለፍ በምታደርግበት እና ገላጋይነት ዋጋ ባጣበት ዘመን ዋናው መፍትሄ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ልዩነቶችን በራስ አቅም መፍታትን ማስቀደም ነው:: ይህ ካልሆነ ግን የዜጎች መከራ እየከፋ ነው የሚሄደው:: ለዚህ አብነታችንም ጎረቤት ሀገር ሱዳን ናት::

ዩጎዝላቪያ እና ሶሪያም ከሰላማዊ ትግል ይልቅ ኃይል የሁሉም ነገር መፍቻ ቁልፍ መሳሪያ ነው ብለው በማመናቸው ለዛሬው ሀገር ተረካቢ ትውልዳቸው የመከራ ውርስ አውርሰው አልፈዋል::

በሌላ በኩል ሩዋንዳ ከጦርነት እና ከሐሳብ የበላይነት ማን ይበልጣል ብሎ ለማረጋገጥ ጦርነት ከመግባት ከእኔ ተማሩ ያለች ይመስላል:: ሀገሪቱ በእርስ በእርስ ጦርነት ያጣቻቸውን 800 ሺህ የሚጠጉ ዜጎቿን በየዓመቱ እያሰበች ዳግም ወደ ጦርነት ላትገባ አስተማማኝ ሰላምን በሐሳብ የበላይነት ገንብታለች::

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኮትዲቯርም ከገጠማት የእርስ በእርስ የግጭት አዙሪት የወጣችው በልጆቿ ሰላም ዘማሪነት እና በመሪዎቿ አድማጭነት ነው::

ኢትዮጵያስ እንዴት ከተደጋጋሚ የግጭት አዙሪት ትውጣ? የሚለው የሐሳባችን መውጫ ጉዳይ ነው:: ሀገራችን ወደተሻለ ከፍታ እንድትሸጋገር፣ በግጭት ሕዝብ ሳይሞት፣ ሳይዘረፍ፣ ሳይፈናቀል እና የደኅንነት ችግር ሳይሰማው በፈለገበት ቦታ ተንቀሳቅሶ በመሥራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ፣ ሕዝባዊ መስተጋብሩ እንዲጠናከር ንግግር፣ ውይይት እና ድርድር ቀዳሚው የትግል ስልት ሊሆን ይገባል:: ስሜቱን አርግቦ በምክንያት የሚያምን ትውልድ መፍጠርም ተገቢ ነው::

ግጭቶች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ አግኝተው ሕዝብ ያለ ስጋት የሚንቀሳቀስባትን ሀገር ለመገንባት ሕዝቡ ታጣቂ ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ጫና መፍጠር ይጠበቅበታል:: መንግሥት ሕዝብ የሚያነሳቸውን የሕዝብ የልማት እና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን ለመፍታት እያሳየ ያለውን ጅምር ማጠናከር ይኖርበታል::::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here