እንደ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም እ.አ.አ 2018 መረጃ መሠረት የዓለም የደን ሽፋን አራት ቢሊዮን ሄክታር መሬትን ያካለለ ነው:: ይህ ከአሥር ሺህ ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በሁለት ቢሊዮን ሄክታር መሬት ያንሳል:: የግብርና እና የኢንዱስትሪ መስፋፋት ለዓለም የደን ሽፋን መቀነስ ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚወስዱም መረጃው ያሳያል::
በእነዚህ ምክንያቶች አሁንም ድረስ እየተመናመነ የመጣው ደን እና ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቀው ጋዝ የዓለምን ሕዝብ ከባድ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል:: በየጊዜው የሚስተዋለው ከፍተኛ ሙቀት፣ ድርቅ እና ጎርፍ እጁን ለሰብዓዊ እርዳታ የሚዘረጋው የዓለም ሕዝብ ቁጥር እንዲጨምር አድርገውታል:: ለዚህም ነው የዓለም መሪዎች በየጊዜው እየተገናኙ የተፈጥሮ ሚዛን እንዳይዛባ የሚመክሩት እና አቅጣጫዎችንም የሚያስቀምጡት::
በአሁኑ ወቅት በርካታ ሀገራት ከተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመላቀቅ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሸከርካሪዎችን መጠቀምን ከማበረታታት ጀምሮ ሰብዓዊ ቀውስን (ከእርዳታ ለመላቀቅ) ምርታማነትን በማረጋገጥ መውጣት እንደሚገባ አምነው የደን ሽፋንን ሊያሳድጉ የሚችሉ ፖሊሲዎችን እና አሠራሮችን እየተገበሩ ይገኛሉ::
ያደጉት ሀገራት የደን ልማትን የተፈጥሮ ሚዛንን ከማስጠበቂያ እና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጫነት ባለፈ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እና የተጨማሪ ገቢ ምንጭ አድርገው ሠርተውበታል፤ እየሠሩበትም ይገኛሉ::
የዓለም ባንክ እ.አ.አ በ2023 ይፋ ባደረገው መረጃ ላይ ሩሲያን የዓለማችን ከፍተኛ የደን ሽፋን ያላት ሀገር ሲል አስቀምጧታል:: 50 በመቶ የሚጠጋው የሩሲያ ሥነ ምሕዳር በደን የተሸፈነ መሆኑን በማሳያነት ይጠቅሳል:: ከዓለም አጠቃላይ የደን ሽፋን ውስጥ አንድ አምስተኛው በሩሲያ ውስጥ እንደሚገኝ መረጃው ያትታል::
እንደ ‘ግሎባል ውድ ማርኬት’ (www.Global Wood Marketsinfo.com) ድረ ገጽ መረጃ ሩሲያ እ.ኤ.አ በ2024 ከደን ኢንዱስትሪ ሽያጭ 18 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ አግኝታለች:: ይህም የደን ሐብት የተጨማሪ ገቢ ምንጭ ለመሆኑ ማሳያ ነው::
የሀገሪቱ የደን ሐብት ለከፍተኛ ገቢ አስተዋጽኦ ከማበርከቱም ባሻገር ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦን ዳይኦክሳይድን በመምጠጥ እና በማከማቸት የዓለምን የአየር ንብረት በመቆጣጠር ረገድ ወሳኝ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ተብላል::
ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (www.ilostat.ilo.org) ከሦስት ዓመት በፊት ይፋ ባደረገው መረጃ ደግሞ የደን ልማት ዘርፉ ለ33 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል::
ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተገበረችው የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጠቃሽ ነው:: ይህን መነሻ በማድረግም ያደጉት ሀገራት በደን ሐብት የደረሱበት ደረጃ ላይ ያደርሰን ይሆን? ባለፉት ስድስት ዓመታት የተተከሉ ችግኞችስ ምን ውጤት አስገኙ? ከመትከል ባሻገር የጽድቀት ምጣኔውስ ምን ይመስላል? የሚለውን መቃኘት ይገባል::
ሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ እየፈተናት ካለው የአየር ንብረት ለውጥ እና ከአካባቢ መራቆት፣ ከጎርፍ አደጋ፣ ከአፈር መሸርሸር፣ ከደን መመናመን ጋር ተያይዞ እየገጠማት ከሚገኘው የብዝኃ ሕይወት መመናመን መውጫው አረንጓዴ አሻራ መሆኑን በመረዳት በትኩረት እየሠራችበት ትገኛለች::
የሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው የደን ልማት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማሳካት፣ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የአየር ንብረት መዛባት ማስተካከል፣ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ዘርፉን ማስፋት እና ግለሰባዊ እንዲሁም ሀገራዊ ገቢን ከፍ ማድረግ ላይ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው:: በእኛም ሀገር ውጤቱ መልካም እንደሚሆን ያለፉት ዓመታት የተመዘገበው ውጤት ማሳያ ነው:: ሀገራዊ የደን ሽፋናችን ከ23 በመቶ በላይ መድረሱን ልብ ይሏል::
በኢትዮጵያም የደን ልማት ዘርፉ 12 ነጥብ 9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ድርሻ እንዳለው የአማራ ክልል የደን ምርምር ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል:: የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ተመራማሪ ምናለ ወንዴ (ዶ/ር) የአረንጓዴ አሻራ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል::
የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው ደግሞ እንደ ሀገር ከ43 በመቶ በላይ የሚሆነው መሬት በአሲዳማነት የተጠቃ ነው:: በአሲዳማነት የተጎዳን መሬት በኖራ በማከም ምርታማነትን እስከ ሦስት እጥፍ ማሳደግ ቢቻልም ለግዥ የሚወጣው ወጪ ግን ከፍተኛ ነው:: ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጥ የሚችለው ደግሞ ደን ልማት ላይ በስፋት መሥራት እንደሆነ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ያሳያሉ::
ባለፉት ዓመታት በሀገራችን የተተከሉ ችግኞችም ከምርት ውጭ የነበረ መሬት ወደ ምርት እንዲመለስ እያደረገ መሆኑን ባለፉት ዘገባዎቻችን ምስክርነትን የሰጡ አርሶ አደሮች እና የግብርና ባለድርሻዎች እማኝ ናቸው:: የደን ልማት በዝናብ መብዛት እና በጎርፍ እየታጠበ ለችግሩ የሚጋለጠውን መሬት ከማዳን ባለፈ ለኖራ ግዥ የሚወጣውን ሐብት በማስቀረት ይበልጥ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል::
እንደ ሀገር ባለፉት ስድስት ዓመታት 40 ቢሊዮን ችግኞችን የተከለችው ኢትዮጵያ፤ በዚህ ዓመት ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ወደተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባቷን ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል:: ከዚህ ውስጥ 63 በመቶ የሚሆነው ለምግብነት የሚውሉ መሆናቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል:: ይህም ሁሉም የጥቅሙ ተካፋይ ለመሆን በባለቤት እንዲሠራ የሚያደርግ በመሆኑ ለጽድቀት ምጣኔው ከፍ ማለት ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል ነው የተባለው:: በዚህም የምግብ ሉዓላዊነት ያድጋል፤ የአየር ንብረት ይስተካከላል፤ የሥራ ዕድል ፈጠራው እየጨመረ ይመጣል ሲልም ነው ሚኒስቴሩ ያመላከተው::
የአማራ ክልልም በተያዘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል:: ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስም 880 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል:: በችግኝ የተሸፈነው የማሳ መጠንም 114 ሺኅ ሄክታር መሬት ነው::
በተከላዉ የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጡ የፍራፍሬ ችግኞች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል:: ለዚህ አብነትም በደቡብ ወሎ ዞን ያለው ተሞክሮ ነው የሚነሳው:: በወሎ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት የሙዝ ክላስተር ችግኝ ተከላን በቃሉ ወረዳ ባከናወነበት ወቅት እንደተገለጸው በዞኑ በተያዘው የክረምት ወቅት 206 ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ ተብሎ ይጠበቃል::
በቀደሙት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የውኃ አቅም እንዲጨምር እና የአፈር ለምነት እንዲሻሻል ማድረጉን የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሊ መኮንን አስታውቀዋል:: ቀጣናው በክልሉ የፍራፍሬ ኮሪደርነት መለየቱንም ገልጸዋል::
የሰብል ልማትን ጨምሮ በደን እና በፍራፍሬ ልማት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆኑን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪዉ አሁንም የሚተከሉ ችግኞችን በአግባቡ ተንከባክቦ ለፍሬ ማብቃት ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል::
የወሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት አወል ሰይድ (ዶ/ር) በበኩላቸው በዚህ ዓመት በምርምር የተረጋገጡ የሙዝ ዝርያዎችን በአርሶ አደሩ ማሳ እየተከልን ነው ብለዋል:: 20 ሺህ የሚሆነው በቃሉ ወረዳ መተከሉን ገልጸው፣ ቀሪዉ ደግሞ በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ የሚተከል መሆኑን አስታውቀዋል:: የተተከሉት ችግኞች አስፈላጊውን ጥቅም እስኪሰጡ ድረስ ዩኒቨርስቲዉ ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋልም ብለዋል።
የ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በተካሄደበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ ባለፉት ዓመታት የተተከሉት ችግኞች የአፈር ለምነት እንዲጠበቅ እንዲሁም የተፋሰስ ደኅንነት እንዲረጋገጥ ጉል አበርክቶ አድርገዋል ብለዋል::
እየተተከሉ ያሉ ችግኞች የአረንጓዴ አሻራ ተፋሰሶች አረንጓዴ ሆነው ለቱሪዝም ምቹ እንዲሆኑ፣ ለም አፈራችን ወደ ባዕዳን ሀገራት እንዳይወጣ እንዲሁም የኃይል እና የመስኖ ግድቦቻችን በደለል እንዳይሞሉ ከፍተኛ ሚና አበርክቷል ብለዋል:: አረንጓዴ አሻራ ሀገራዊ የደን ሽፋኑ እንዲሻሻል ማድረጉንም አንስተዋል:: የደን ሽፋኑ በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ ሁለት በመቶ አሁን ላይ ወደ 23 ነጥብ ስድስት በመቶ ከፍ ማለቱንም ልብ ይሏል::
የአማራ ክልልም የአረንጓዴ አሻራን መነሻ አድርጎ ችግኞችን በመትከል ላይ ይገኛል:: የክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዳይሬክተሩ እስመለዓለም ምህረቱ የሚተከሉ ችግኞች የደን ልማት ሽፋንን የሚያሳድጉ፣ የጥምር ደን ልማትን የሚያበረታቱ እና በፍራፍሬ ምርት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል::
የተተከሉ ችግኞችን የጽድቀት ምጣኔ ከፍ ለማድረግ የሚተክለው አካል ለተተከሉ ችግኞች ባለቤት እንዲሆን ከማድረግ ጀምሮ በቢሮዉ በኩል ከፍተኛ ክትትል እና ቁጥጥር እንደሚደረግ አስታውቀዋል:: ችግኞች የተተከሉበት ጉድጓድ እርጥበት ይዞ እንዲቆይ ጉድጓድ የማልበስ ሥራ ይከናወናል:: የአረም እና ኩትኳቶ ሥራ በትኩረት ይሠራልም ብለዋል:: ችግኞች ከመተከላቸው በፊት ለፀሐይ ማጋለጥ፣ ውኃ ማጠጣትን መቀነስ እና ሥር መግረዝ ቀድሞ መሠራቱን ተናግረዋል::
ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች ያስገኙት ውጤት ከእኛም በላይ ዓለም የመሰከረለት እውነታ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል የ2017 አረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ባደረጉበት ወቅት የአረንጓዴ አሻራ በጎ ተጽዕኖን አንስተዋል:: ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል ያደረገችው ጥረት ከስንዴ ተረጂነት እንድትወጣ አድርጓታል ነው ያሉት:: ይህም ጥረቷ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና አግኝቶ በቅርቡ የምግብ ጉባኤ እንድታዘጋጅ ዕድል ማግኘቷን አስታውቀዋል:: በጳጉሜ ወር 2017 ዓ.ም የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤን ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ ሲደረግ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል እያከናወነች ያለው ጥረት ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል::
በአጠቃላይ “መትከል ምግብም ነው፤ ውበትም ነው:: የምንተክለው ምግባችንን ነው፤ የምንተክለው ለዐይናችን የሚያምር እና የሚመቸ መስክ ለመፍጠርም ጭምር ነው” ብለዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም