“እኔ የታሸጉ ወይም በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን በብዛት ለልጆቼ እገዛለሁ፡፡ ነገር ግን ስገዛ የመጠቀሚያ ጊዚያቸውን አልፎ አልፎ ሳስታውስ ካልሆነ አላይም፤ ለፀሐይ ብርሃን የተጋለጠ ነው? ወይስ ያልተጋለጠ? የሚለውን አስቤ አላውቅም”፤ በማለት አስተያየት የሰጠችን የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ ፋሲካ ወርቁ ናት፡፡ ሌላዋ የዚሁ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወ/ሮ አትጠገብ ዓለሙ ደግሞ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምርቶችን ስትገዛ የመጠቀሚያ ጊዚያቸውን እንደምታይ እንዲሁም ምግቦቹም ሆኑ መጠጦች ፀሐይ አግኝቷቸዋል? ወይስ አላገኛቸውም? የሚለውን ከመደርደሪያዎቹ ላይ ቃኝታ እና ሻጮቹን ጠይቃ እንደምትገዛ ነግራናለች፡፡ እኛም ይህን ጉዳይ ይዘን ወደ ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ አቅንተን ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲው በኬሚካል እና ምግብ ምሕንድስና ፋኩልቲ የምግብ ደኅንነትና ጥራት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር አድማሱ ፋንታ ጋርም ቆይታ አድርገናል፡፡ ዶ/ር አድማሱ እንዳስረዱት በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች ጎጂ ናቸው ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ እንዲያውም ምቾትን ይጨምራሉ፤ ማለትም የታሸጉ ምግቦች ጥሬውን ገዝተን ከምናበስላቸው ጋር ሲነጻጸሩ ጊዜ እና ድካምን ይቆጥባሉ፣ ለማብሰል የምንጠቀምበትን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታን ወይም የእንጨት እና የከሰል ወጭን ይቀንሳሉ፡፡ ለጤናም የታሸጉ(የተቀነባበሩ) ምግቦች የጎደሉ ንጥረ ነገሮችን ስለሚያካትቱ ጠቃሚ ናቸው፡፡ ለአብነትም የስንዴ ዱቄት (ፊኖ)ሲዘጋጅ በማቀነባበር ሂደት ያጣውን ንጥረ ነገሮችን ለመተካት በአይረን እና ዚንክ እንዲበለፅግ ተደርጎ ስለሚዘጋጅ ለጤና ተስማሚ ነው፡፡
የተቀነባበሩ ምግቦች ምን ሲሆኑ ጉዳት ያስከትላሉ?
በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምርቶች በራሳቸው ለሕመም አይዳርጉም፡፡ይሁንና የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን ለማራዘም እና የምግብ ማቅለሚያዎችን ለማካተት የሚያስችሉና የተፈቀዱ ግብዓቶች ከመጠን በላይ ሲጨመሩ፣ ባዕድ ነገሮች ተጨምሮባቸው ሲታሸጉ እና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሲያልፍ ለጤና ጎጂ ይሆናሉ፡፡ ይሄ እንዳለ ሆኖ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ነግሮች አብረው ሊታሸጉም ይችላሉ፡፡
እንደ ዶ/ር አድማሱ ገለጻ ባለማወቅ ሊኖሩ የሚችሉ ጎጂ ነገሮች እንደ ሻጋታ ወለድ መርዛማ ኬሚካሎች (አፍላቶክሲን) እና የፀረ፟ ተባይ ቅሪት ዓይነቶች ናቸው፡፡ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚጨመሩ ደግሞ ለምሳሌ ለምግብ ያልተፈቀዱ ማቅለሚያዎችን የመሳሰሉ ባዕድ ነገሮች መጠቀም ለጤና ጠንቅ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ለምግብ ማሸጊያነት መዋል በሌለባቸው ቁሳቁሶች ሲታሸጉ፣ በተፈቀደው ደረቅ ወይም ቀዝቃዛ ቦታ ላይ ሳይቀመጡ ሲቀር እና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሲያልፍ ጤና ላይ እክል ይፈጥራሉ፡፡
ፈሳሽ ምግቦች ለምሳሌ ዘይት (በግልጽ ወደ ውስጥ በሚያሳይ የፕላስቲክ ማሸጊያ ታሽጎ ለፀሐይ ብርሃን እና ሙቀት ከተጋለጠ ለጤና ጎጂ የሆኑ ኬሚካሎችን ይፈጥራል፡፡
እንደ ጁስ፣ ውኃ እና ዘይት የመሳሰሉ ፈሳሽ ምግቦች ሙቀት በበዛባቸው እና ለፀሐይ አጋልጦ ማስቀመጥ ጉዳት አለው፡፡ በተለይ ዘይት ለከፍተኛ ሙቀት ሲጋለጥ ለጤና ጠንቅ የሆነ ኬሚካል ይፈጥራል፡፡ በተጨማሪም ማሸጊያው የተሠራበት ኬሚካል ወደ ምግቦቹ ሊሸጋገር ስለሚችል ተጨማሪ የጤና ስጋት ይፈጥራል፡፡
የታሸገ ውኃ በራሱ ችግር እንደሌለው የጠቆሙት ዶ/ር አድማሱ፤ በአቀነባባሪዎች ዘንድ ግን በአግባቡ በሚፈለገው መጠን ደኅንነቱ ተጠብቆ ካልታሸገ፣ የሚቀመጥበት ቦታ ሳይንስ በሚመክረው መንገድ ደረቅ፣ ቀዝቃዛ ወይም ለፀሐይ ብርሃን የተጋለጠ ከሆነ ችግር ያመጣል፡፡ ለካንሠር በሽታዎችም የማጋለጥ አጋጣሚን ይጨምራል፡፡
የሚያስከትሉት የጤና ጉዳቶች፡-
ዶ/ር አድማሱ እንደሚሉት የተቀነባበሩ ምግቦች እና መጠጦች ባልተቀነባበሩ ጥሬ ምግቦች ላይ እንደሚከሰቱት ሁሉ በባዮሎጂካዊ (ህይወት ያላቸው ጎጂ ባክቴሪያ፣ ቫይረስና ሻጋታ የመሳሰሉ ተዋህሲያን) እና በኬሚካላዊ በካይ ነገሮች ተበክለው ጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ በባዮሎጂካላዊ ነገሮች የተበከለን ምግብ እንደተመገብን የምግብ መመረዝ በማስከተል ወዲያው ሕመም ያጋጥማል፡፡ በኬሚካላዊ በካይ ነገሮች በአነስተኛ መጠን የተበከሉ ምግቦች ግን ሳይታወቀን ቀስ በቀስ ጤና ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል አስረድተዋል፡፡ በተለይም ለተለያዩ የካንሠር ሕመም የሚያጋልጠውም ኬሚካላዊው የብክለት መንገድ ነው፡፡
ምን መደረግ አለበት፡-
ለምግብ ብቻ እንዲውሉ የተፈቀዱ እንደ ምግብ ማቅለሚያና የመሳሰሉ ግብዓቶችን ብቻ በተፈቀደው መጠን መጨመር፣ ስንገዛም ለጤና ተስማሚ ናቸው? ወይስ አይደሉም? የሚለውን አገናዝቦ መግዛት፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን መለየት፣ ምግቦች ከተመረቱበት ፋብሪካ እስከ ተጠቃሚው እስኪደርሱ ድረስ ከፀሐይና ከፍተኛ ሙቀት መጠበቅ እንዳለባቸው የዘርፉ ሙህር አስገንዝበዋል፡፡ ሲቀመጡም ደረቅ ወይም ቀዝቃዛ ቦታ መሆን አለበት፡፡
የመጠቀሚያ ጊዜን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም አንዳንድ ምርቶች ላይ ከዚህ ቀን በፊት ይጠቀሙ/ቤስት ቢፎር/ ተብሎ ሲገለጽ ይህ ቀን ካለፈ በኋላ ቢመገቡት የምግብ ደኅንነት ችግር ሳይሆን የጥራት ጉድለት ስለሚኖር ከተቀመጠው ቀን በፊት ብትጠቀሙ የተሻለ ይሆናል ለማለት ነው፡፡
የመጠቀሚያ ጊዜ /ኤክስፓየሪ ዴት/ ከሆነ ግን የመጠቀሚያ ጊዜው ሲያልፍ የምግብ ደኅንነት ችግር ሊኖር እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡
በተፈቀዱ የምግብ አይነቶች ላይ ማቅለሚያዎች(foodclour)መጠቀም ችግር እንደሌለው ነገር ግን መጠኑ ከበዛ እና ለምግብነት መዋል የሌለበት የምግብ ማቅለሚያ ቀለም ጥቅም ላይ ከዋለ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡በተለይም ዳቦ ቆሎን፣ ገብስ ቆሎ እና ኩኪሶችን ሰዎች ካዘጋጁ በኋላ አሽገው ለማስቀመጥ ሲያስቡ በዘይት ማሸት እንደሌለባቸውም ዶ/ር አድማሱ ምክር ለግሰዋል፡፡ ምክንያቱም ዘይት ከሙቀትና ዓየር ጋር ሲገናኝ ሌላ ለጤና ጎጂ የሆነ ኬሚካል ይፈጥራል፡፡ በፍጥነት የሚበላ(የማይቆይ) ከሆነ ግን ችግር እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡
በመንግሥት በኩል የሚደረግ ቁጥጥር ብቻውን የምግብ ጥራትና ደኅንነትን ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ የማያስችል ስላልሆነ ዋናውን ድርሻ የሚወጣው ባደጉ የዓለም ክፍሎችም እንደሚደረገው ራሱ ተጠቃሚው እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡ ተመጋቢው ግንዛቤው ሲኖረው ይሄ ይጎዳኛል፣ ይሄ ደግሞ ይጠቅመኛል ብሎ ሲያስብ እና ሲተገብረው አምራቹ በራሱ ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲያመርት እንደሚገደድ ጠቁመዋል፡፡
ተቆጣጣሪ አካላትም ከተጠቃሚው አቅም በላይ ሲሆን የራሳቸውን ሥራ ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመጡ ማስቻል እንዳለባቸው ዶ/ር አድማሱ አሳስበዋል፡፡ ተጠቃሚው ጥራቱ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ ምርት ብቻ የሚገዛ ከሆነ፣ በተጨማሪም አምራቾች እና ሻጮች የያዙት ምግብ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን የሚያረጋግጥላቸው የምግብ ደኅንነት ማረጋጋጫ ሠርተፊኬት ከተቆጣጣሪ አካላት የተገኘ እና በትክክለኛው መንገድ የመጣ መሆኑን አውቀው መግዛት እንዳለባቸው ምክረ ሐሳብ ለግሰዋል፡፡
ታዲያ ጊዜ ያላቸው ሰዎች በፋብሪካ ተቀነባብረው ከታሸጉ ምግቦች ይልቅ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች ሙሉ በሙሉ በጥሬነታቸው ገዝተው ራሳቸው አዘጋጅተው ቢመገቡ መልካም መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በምግብ እና መድኃኒት ባለስልጣን የአማራ ክልል ቅርንጫፍ የኢንስፔክሽን ባለሙያ አቶ መለሰ እንግዳየሁ በበኩላቸው እንደገለጹት ወደ ኢትዮጵያ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች ከውጭ ሀገራት ይገባሉ፤ በሀገር ውስጥም ይመረታሉ፡፡ ታዲያ ባለስልጣን መሥሪያቤቱ በሁሉም ላይ ቁጥጥር እና ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው ወይ? የሚለውን ፈትሾ ነው ወደ ተጠቃሚው የሚደርሰው፡፡
ባለሙያው እንደሚሉት በሀገር ውስጥ በሚቀነባበሩ የምግብ ምርቶች ላይ የቁጥጥር መስሪያ ቤቱ በራሱ ደኅንነታቸውን አረጋግጦ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡ አምራች ኢንዱስትሪው ባለበት አካባቢ የሚገኙ የጤና ተቋማት እና መምሪያዎችም ደኅንነቱን አረጋግጠው የብቃት ማረጋገጫውን መስጠት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በዓመት አራት ጊዜ ከሚያደርገው ቁጥጥር በተጨማሪ ከሕብረተሰቡ በሚመጣለት ጥቆማ እንዲሁም በጤና ላይ እክል ሲያጋጥምም ፍተሻ እና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ነግረውናል፡፡ ለአብነትም በቅርቡ በህዳር ወር 2018 ዓ.ም በምዕራብ አማራ ባሉ ዞኖች እና ወረዳዎች በሚገኙ ሱቆች በተደረገ የአሰሳ ሥራ ጥራታቸው የተጓደለ ከሕጻናት አልሚ ምግቦች ጀምሮ የተለያዩ ብስኩቶች እና ከረሜላዎች ተወግደዋል፡፡ 14 ሺህ ካርቶን ጥራቱ የተጓደለ ብስኩትም በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት በጥቆማ ተገኝቶ ተወግዷል፡፡ በጎንደር ከተማም ለሕጻናት የሚውል 18ሺህ ደርዘን ጭማቂም በባለፈው ዓመት መወገዱን አንስተዋል፡፡
መንግሥት ሕገወጥ ድርጊትን በበላይነት የመቆጣጠር ኃላፊነት ቢኖረውም በዋነኝነት ግን ሕብረተሰቡ በባለቤትነት መሳተፍ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ሰዎች ምግቦች ጥራታቸው የጎደላቸው መስሎ ሲሰማቸውም ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ማሳወቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ጤና አዳም
*ምግቦች ከፀሐይ ብርሃን እና ከከፍተኛ ሙቀት መጠበቅ አለባቸው፡፡
*በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን ሲገዙ የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን ማየት አይርሱ፡፡
*ጥራቱ እና ደኅንነቱ የተረጋገጠ ምርት ብቻ ይግዙ፡፡
*ጥራቱ የተጓደለ ምርት የሚያመርቱ ወይም የሚሸጡ ግለሰቦች ሲያጋጥሙዎት በአካባቢዎ ለሚገኝ ምግብ እና የመድኃኒት ባለስልጣን መስሪያ ቤት፣ ጤና ተቋም ወይም የጸጥታ ኀይል ያሳውቁ፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


