የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ባስቀመጠው ሕግ መሰረት እያንዳንዳቸው የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ቢ (የወጣቶች ) ቡድን እንዲይዙ ያስገድዳል። ክለቦቹ አምስት ታዳጊ ተጫዋቾችን ደግሞ በስብስባቸው ውስጥ ማካተት እንዳለባቸው በሕጉ ተቀምጧል። ሁሉም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ አስገዳጅነት ታዳጊዎችን በዋናው ቡድን ስብስብ ቢይዙም ከጥቂት ክለቦች በስተቀር የመሰለፍ ዕድል ሲሰጧቸው ግን አይስተዋልም።
ለታዳጊ ተጫዋቾች የመሰለፍ ዕድል በመስጠት ቀዳሚ ከሆኑ ክለቦች መካከል አዳማ ከተማ (ከአምናው ውድድር ጀምሮ) አንዱ ነው። የአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ቡድን ባሳለፍነው ዓመት ታዳጊዎቹ ራሳቸውን እንዲያሳዩ በሩን በመክፈት ስኬታማ እንደነበር አይዘነጋም። ዕድሉን ያገኙት ዮሴፍ ታረቀኝ፣ቢኒያም አይተንን የመሳሰሉት ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም ራሳቸውን አሳይተዋል። አዳማ ከተማ ዘንድሮም በስብስቡ ውስጥ ከአስር በላይ ታዳጊዎችን ሲይዝ ከእነዚህ ውስጥ እስካሁን ባለው የሊግ ጨዋታ የመሰለፍ ዕድል እያገኙ መሆኑን አሰልጣኙ ይታገሱ እንዳለ ከአሚኮ በኩር ዝግጅት ክፍል ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።
ከአዳማ ከተማ በተጨማሪ ቅዱስ ጊዮርጊስም ከባለፉት ስድስት ዓመታት በተለየ በዚህ ዓመት ለወጣት ተስፈኞቹ ዕድል እየሰጠ ይገኛል። ባሳለፍነው የክረምቱ የዝውውር ወቅት በርካታ ታላላቅ ተጫዋቾችን ማጣቱ ለወጣቶቹ በሩን እንዲከፍት አስገድዶታል። የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታው ክለብ በክረምቱ የዝውውር ወቅት የቡድኑ ወሳኝ የሚባሉትን እስማኤል ኦሮ አጎሮን፣ አማኑኤል ገብረ ሚካኤልን፣ ጋቶች ፓኖምን፣ሱሌይማን ሀሚድ እና ምኞት ደበበን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ማጣቱ ይታወሳል። አንጋፋው ክለብ ከዚህ በፊት ከሰማንያዎቹ መባቻ ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም ገደማ ድረስ ታዳጊ ተጫዋቾችን በሂደት በማብቃት ለራሱም ሆነ ለሀገራችን ትልቅ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል። ፈረሰኞቹ ዘንድሮ ወደ ቆየው ባህላቸው በመመለስ ታዳጊዎቹ ላይ ትኩረት አድርገዋል። ሀሮን አንተር ፣አቢሴሎም ዘመንፈስ፣ቢኒያም እንዳለ ፣ አሸናፊ ሞሽ ፣ ፉአድ ሀቢብ እና አብርሃም ጌታቸው ዋናውን የፈረሰኞች ቡድን የተቀላቀሉ እና የመሰለፍ ዕድል ከተሰጣቸው ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳሉ።
ከሁለቱ ክለቦች ባሻገር ባለፉት ዓመታት ወላይታ ዲቻ እና ሀዲያ ሆሳዕና ለታዳጊዎች ዕድል በመስጠት የሚታወቁ ክለቦች ናቸው። ሁለቱ ክለቦች በስብስባቸው በርካታ ታዳጊዎችን በመያዝ እና ዕደሉን በመስጠትም ከቀዳሚዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ፋሲል
ከነማም ከዚህ ቀደም ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን ፣ዓለም ብርሐን ይግዛውን ሐብታሙ ተከስተን እና እንየው ካሳሁንን በማሳደግ ወደ ትልቅ ደረጃ እንዲሸጋገሩ አድርጓል። አፄዎቹ አሁን ላይም በተወሰነ መልኩ ለታዳጊዎቹ እድል እየሰጡ መሆኑን እስካሁን ባለው ጨዋታ ስንመለከት የጣናው ሞገድ ባህር ዳር ከተማ ግን ብዙ ጊዜ ለታዳጊዎቹ ዕድሉን ሲሰጥ አልተመለከትንም። ባሕር ዳር ከተማ ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ታዳጊዎቹን በቡድናቸው ከመያዝ ባለፈ ሲጠቀሙባቸው ማየት እንግዳ ነገር ነው፡፡
አሰልጣኞቹ ለታዳጊዎቹ የመሰለፍ ዕድልን ለመስጠት ለምን ፈሩ?
ለአሰልጣኞቹ የሚሰጠው የውል ስምምነት አጭር መሆኑ አንደኛው ምክንያት ነው። በሀገራችን ክለቦቹ ለአሰልጣኞች የሚሰጣቸው የውል ስምምነት ብዙ ጊዜ ከሁለት ዓመታት አይበልጥም። አሰልጣኞቹ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥም ክለቡን ውጤታማ አድርገው ለቀጣሪዎቻቸው ማሳየት ይኖርባቸዋል። እስካሁን ባለው የፕሪሚየር ሊጉ ልምዳችን አንድ አሰልጣኝ በተከታታይ ሦስት ወይም አራት ጨዋታዎችን ከተሸነፈ ከክለቡ ይሰናበታል፡፡ አሰልጣኙ ይህ ዕጣ ፋንታ እንዳይደርሰውም ውጤት ለማምጣት ክታዳጊዎቹ ይልቅ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች ለመጠቀም ይገደዳል። አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለም ይህን ባህል ለመቀየር መጀመሪያ ለሰልጣኞች የሚሰጠው የውል ስምምነት መስተካከል አለበት ይላል።
በሀገራችን በርካታ ባለተሰጥኦ ታዳጊዎች እንዳሉ የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል። ይሁን እንጂ እነዚህ ታዳጊዎች በአካል ብቃት እና በታክቲክ ደካማ መሆናቸውንም አሰልጣኝ ይታገሱ ይመሰክራል። አሰልጣኙ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ በብቃት የሚጫወት ታዳጊ ማግኘት ከባድ እንደሆነ በመግለጽ ይህም በአስልጣኞቹ ዘንድ እምነት እንዳይጣልባቸው አድርጓቸዋል ብሏል።
ከታዳጊዎቹ ጋር በርካታ ዓመታት እንደሠራ የሚናገረው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በወጣቶቹ እምነት እንዲያሳድር እንዳደረገው ይናገራል። “ሁሌም ታዳጊዎችን ማጫዎት ሳይሆን ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ጋር እየቀላቀልን ካሰለፍናቸው ልምድ ያላቸው ተጫዋቾቹ ታዳጊዎችን ቅርጽ እንዲይዙ ያደርጋሉ” ብሏል፡፡ ውሳኔው በጥንቃቄ ከተደረገ እንደ ሀገርም እንደ ክለብም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጭምር የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ ተናግሯል።
ዓመቱን ሙሉ ተመሳሳይ ፊት ወይም ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች መጠቀም ዋናውን ቡድንም ቢሆን ያሰለቻል፣ በመካከላቸው የሚኖረው ፉክክር ይቀንሳል። ከፍተኛ መዋለ ንዋይ የሚፈስባቸው የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የሚደራጁበት መንገድ ትክክል አይደለም፤ ጊዜያዊ ውጤት ላይ የተመሰረተ ነው ተብሎ ይኮነናል። ሁሉም ክለቦች በየደረጃው ከ20 ዓመት በታች ፣ ከ17 ዓመት በታች እና ተስፋ ቡድን ይዘው እየሰሩ አለመሆኑም ይነገራል። ከዚህ ይልቅ ልምድ ያለውን ተጫዋች ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት እያስፈረሙ ይገኛሉ። ለዚህ ማሳያ ደግሞ ትርታ ሬዲዮ ባወጣው መረጃ መሰረት የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ከፍተኛው የደሞዝ ጣሪያ ከሦስት መቶ ሃምሳ ሺህ እስከ ስድስት መቶ ሃምሳ ሺህ መሆኑን አስደምጠዋል። ለተጫዋቾች ደሞዝ ይህን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጡ ክለቦችም ለታዳጊዎቹ በቀላሉ የመሰለፍ ዕድል ይሰጣሉ ተብሎ አይታሰብም።
ታዳጊ ተጫዋቾች በውሰት ውል ወደ ታችኛው የሊግ እርከን አምርተው ራሳቸውን የሚያጎለብቱበት ዕድል ክፍት ቢሆንም ደፈር ብሎ ለዚህ በር የከፈተ ተጫዋች ወይም ክለብ ግን የለም። ይልቁንስ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ዓመቱን ሙሉ ማሳለፍ ምርጫቸው መሆኑን አሰልጣኝ ይታገሱ ይናገራል፡፡በዚህ ምክንያት ታዳጊዎቹ ተጎጂ ሆነዋል።
በሀገራችን ብዙ የውድድር መድረክ ባለመኖሩ ታዳጊዎቹ ልምድ የሚያገኙበት እና ራሳቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚ አያገኙም። በጨዋታ ድግግሞሽ ምርጥ አቋም የሚያሳዩ ተጫዋቾች የመሰለፍ ዕድል ባለማግኝታቸው በርካቶቹ ተሰጥኦቸው ይባክናል፣ ታዲያ ይህ እንዳይሆን አሰልጣኞቹ ታዳጊዎችን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን የመሰለፍ ዕድሉን ሊሰጧቸው ይገባል፣ የአሰልጣኝ ይታገሱ አስተያየት ነው። በፕሪሚየር ሊጉ ለታዳጊ ተጫዋቾች የመሰለፍ ዕድል የሚሰጡ አሰልጣኞች ፣በጨዋታ ወቅት ሲመሩ ፣ሰዓት ለመግደያ እና እድል ሰጥቻለሁ ለማለት ብቻ መሆን የለበትም ፤ ታዳጊዎቹ የማሸነፍ ሥነ ልቦናን እና ጠንካራ የጨዋታ እንቅስቃሴን መልመድ እንዳለባቸውም አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ያምናል።
በዋናው ስብስብ ታዳጊዎቹ መኖራቸው እና ዕድሉን ማግኝታቸው ልምድ ያላቸውን ሌሎቹን ተጫዋቾች ያነቃቃል፣ የእኔነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል፤ ትልቅ ወኔ እና መነሳሳትም ይፈጥርላቸዋል። ከባለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ትልቅ የኢኮኖሚ መናጋት እየገጠማቸው ይገኛል። አብዛኞቹ ክለቦች የከተማ አስተዳደር (የከነማ ) ጡረተኞች በመሆናቸው ችግሩ ፀንቶባቸዋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት አዳማ ከተማ፣ወልቂጤ ከተማ ፣ሀድያ ሆሳዕና በገንዘብ እጦት ምክንያት ተፈትነዋል።አሁን ላይ በከፍተኛ ሊጉ የሚጫወቱት አርባ ምንጭ ከተማ ፣ጅማ አባጅፋር እና ሰበታን የመሳሰሉት በፕሪሚር ሊጉ እያሉ የኢኮኖሚ መናጋት ገጥሟቸው እንደነበር ይታወሳል። ከዚህ ችግር ሁነኛ መውጫ መንገድም ታዳጊዎችን መጠቀም መሆኑን አሰልጣኙ ይመክራል።
ምንም እንኳ አንድ ብሄራዊ ቡድን የረጋ ወይም ተጫዋቾች ረዥም ጊዜ አብረው መቆየት እንዳለባቸው ቢታመንም መተካካቱ ደግሞ አስፈላጊ ነው። ታዲያ ክለቦቹ ለታዳጊ ተጫዋቾች በቂ የመሰለፍ ዕድል ከሰጡ ቅርጹን የጠበቀ ከሃያ ዓመት ወይም ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ይገነባል። እነዚህ ታዳጊዎች አለፍ ሲልም ዋናውን ብሄራዊ ቡድን የሚያገለግሉ በመሆኑ አሰልጣኞች በትኩረት ሊሰሩ ይገባል። በርካታ ተስፋ የተጣለባቸው ባለተሰጥኦ ታዳጊዎች ወደ ዋናው ቡድን ቢቀላቀሉም የመሰለፍ ዕድል ባለማግኝታቸው ባክነው ቀርተዋል። ክለቦቹ ታዳጊ ተስፈኛ ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ስብስብ ካሳደጉ በኋላ በየጫወታው ተጠባባቂ ወንበር ላይ በማስቀመጥ ሳይጫወቱ ጊዜያቸውን እንዲያባክኑ ማድረግ የተለመደ ነው።
አንድ አንድ ታዳጊዎችም ዋናውን ስብስብ መቀላቀላቸውን ብቻ እንደ ስኬት በመቁጠር ተጠባባቂ ወንበር ላይ መቀመጠን በፀጋ ሲቀበሉ ተመልክተናል። ነገር ግን ታችኛው የሊግ እርከን በመውረድ ራሳቸውን ማጎልበት ይኖርባቸዋል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ታኀሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።