የታዳጊዎች ለአስም መጋለጥ

0
184

የተለያዩ በካይ ውህዶች ከባቢ ዓየርን በሚቀላቀሉበት አቅራቢያ የሚኖሩ ታዳጊዎች በአስም በሽታ የመያዝ ምልክቶች እንደሚታዩባቸው በጥናት መረጋገጡን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ አስነብቧል::

በአሜሪካ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ በ269 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ታዳጊ ተማሪዎች ላይ ጥናትና ምርምር አድርጐ ለአስም ህመም የመጋለጣቸው መንስኤ ከ25 በካይ ትነቶች ውህድ ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን አረጋግጧል::

ለአስም ህመም መንስኤ አንድ በካይ ትነት አለመሆኑን የጠቀሱት የጥናትና ምርምሩ መሪ ሶልማዝ አሚሪ የተለያዩ የበካይ ትነት ውህዶች አንዱ ከአንዱ ጋር ሲጣመር በመጨረሻ ምልክቶቹ እንደሚታዩ ነው ያረጋገጡት::ተመራማሪዎው ከባልደረቦቻቸው ጋር 109 የዓየር ብክለቶች ጥምረትን /ውህደት/ በዘመናዊ ስልት ተጽዕኗቸውን ተንትነዋል::

ተመራማሪዎቹ ከአካባቢ ጥበቃ ተቋም በአቅራቢያው ከሚገኙ 10 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተሰበሰበ መረጃ ውጤት ለውህድ የዓየር ብክለት የተጋለጡት ሳል፣  የአተነፋፈስ ችግር እና የመርጃ መሣሪያ መጠቀምን ግድ እንደሚላቸው ተገንዝበዋል::

ከተለዩት መርዛማ ውህድ ትነቶች መካከል አንደኛ ለቤት ውስጥ የቁሳቁስ ጽዳት እና ማጣበቂያ /ሙጫነት/ የሚያገለግሉ ሁለተኛ፣ የቀለም ማቅጠኛና ማዋሀጃዎች ፣ በሦስተኛ ደረጃ ሻጋታ እና የሰውነት ቁስለት ማድረቂያ ፈሳሾች ተጠቅሰዋል::

የተጠቀሱት የበካይ ትነት መገኛዎች ከፊሎቹ በአንዳንድ ሀገራት የተከለከሉ ቢሆንም ከፊሎቹ በማከማቻ ቦታዎች ሊገኙ እንደሚችሉ ነው ተመራማሪዎቹ የጠቆሙት::

የተመራማሪዎቹ ግኝት አጉልቶ እንዳመለካተው ለከባቢ ዓየር ብክለት ለምንጩ ወይም መገኛው የሚኖር ቅርበት ለአብነት ለቀለም ማቅጠኛነት የሚያገለግሉ ማቅጠኛ ፈሳሽ ማምረቻ ፋብሪካ እና ወደ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች መጫኛ የሚኖር ቅርበት በእጅጉ ተጋላጭ እንደሚያደርግ አረጋግጧል::

የጥናትና ምርምር ቡድን መሪ ሶልማዝ አሚሪ ሲያጠቃልሉ ቀደም ብለው ከተካሄዱ የጥናት ውጤቶች ጋር በአዲስ የተጠናው ውጤት መዛመዱን አስምረውበታል::በትልልቅም ሆኑ በአንስተኛ ከተሞች የመርዛማ ትነቶች መገኛ ቅርበት ታዳጊዎችን ለአስም ህመም ከመጋለጥ ጋር እንደሚገናኝ ነው በአጽንኦት ያስታወቁት::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here