የታጠረ ማንነት

0
178

እውቅና ያለው ሉዐላዊ ሀገር ባይኖራቸውም ሲወርድ ሲዋረድ ይዘውት የዘለቁት ሰፊ እርስት አላቸው። ኩርዲስታን የሀገሪቱ መጠሪያ፣ ኩርድ የሕዝቡ መጠሪያ እንደሆነ እስከዛሬ ድረስ ግዛታቸው በምእራባውያን በተለይ በእንግሊዛውያኑ ደባ ለአምስት ያህል ሀገራት ተከፋፍሎ የተሰጠባቸው ባዛኝ ሕዝብ የሆኑ የአለማችን የኢፍትሃዊነት ሰለባ ማሳያዎች ናቸው። ስለእነዚህ ሕዝቦች ሀገራት የሚያደርሱባቸውን በደል እና የትግል ታሪካቸውን ቀጥለን እንመለከታለን፤ መልካም ንባብ።!

ከመካከለኛው ምስራቅ የበቀሉት ለዓለማችን ስልጣኔ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱት ኩርዶች  ሀገር የመሆን መብታቸው የተነፈገ የምእራባውያን ሴራ ሰለባዎች ናቸው። ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርስ ቁጥር እንዳላቸው የሚገመቱትን ኩርዶችን ሀገር አልባ ያደረገው ጠባሳ ለዘመናት የተሻገረ መከራ እና በደል አሸክሟቸዋል።

የኩርዶች በደል

በቱርክ፣ ኢራቅ፣ ኢራን፣ ሶሪያ፣ አርመንያ እና በአዘርባጃን ተሰራጭተው የሚገኙት ከ36 ሚሊዮን የሚበልጡት ኩርዶች የተለያዩ በደሎችን አስተናግደዋል። የኢራቅ፣ ሶሪያ እና ኩዌትን ሉዓላዊ ሀገርነት የፈጠረው የ1913ቱ የ’ሳቨረስ ውል’ እየተባለ የሚታወቀው የስምምነት ሰነድ ለኩርዶቹ ሀገር ይሰጣል የሚል ተስፋ አሳድሮ የነበረበት ሁኔታ በተግባር አልተተገበረም። በዚህ መካከል ለኩርዶቹ ከባድ ጥላቻ የነበረው የቱርክ አባት እየተባለ የሚጠራውን አታቱርክ አዲሷን ቱርክ የማስተዳደር ስልጣን የያዘበት ሁኔታ የኩርዶችን ተስፋ የበለጠ አጨለመው። ከቱርክ ዘውዳዊ አገዛዝ መውደቅ ማግስት ነፃ የኩርድ ሀገርነት ጥያቄን ላለመቀበል ቱርክ፣ ኢራቅ እና ኢራን በተናጠል ተስማምተው ነበር።

ኩርዶች ከዚህ በኋላ በየሚኖሩባቸው የቱርክ፣ ኢራን እና ኢራቅ መንግሥታት  ስር ሆነው አስከፊ ጭቆና ይደርስባቸው ጀመር። በተለይ የቱርክ መንግስት በግዛቱ ላይ በሚኖሩ ኩርዶች ላይ የሚፈፅምባቸው በደል የከፋ ነበር። ኩርዳዊ ማንነታቸውን ነፍጎ “የተራራው ቱርኮች” እንዲባሉ አደረገ። በቋንቋቸው የመናገር መብት የሚከለክል ሕግ አወጣ። በየከተሞች የኩርድ ባህላዊ አለባበስ እና ትውፊት በፍፁም የተከለከለ መሆኑን አወጀ። በተጨማሪም ኩርዶች ካሉበት ስፍራ ወደ ሌላው የቱርክ ግዛት እንዲዛወሩ በማበረታታት ከሌላው ማህበረሰብ ክፍል ጋር እንዲዋሃዱ ለማድረግ ብዙ ርቀት ሄዷል። ቱርክ በግዛቷ ውስጥ የሚኖሩ ኩርዶችን እንደ አናሳ ማህበረሰብ በመቁጠር የማንነት እውቅና ያለመስጠት ፖሊሲን ለዘመናት ተግብራባቸዋለች። የመብት ጥያቄ በሚያነሱት ኩርዶች ላይም ከፍተኛ ጭፍጨፋ ፈፅማለች።

አታቱርክ ዘረኛ እና ጨካኝ መሪ እንደነበር ይነገራል። እንደውም ሳዳም ሁሴን እና ሒትለር እንደ አርአያ የሚያዩት እንደአስተማሪያቸው የሚቆጥሩት ሰው ነበር ይሉለታል። ኩርዶችን ከመጠን በላይ ይጠላ ስለነበር የዘር ጭፍጨፋ አድርጎባቸዋል። አልበገሬዎች በመሆናቸው የነፃነት ታጋዮችን ትግል ለመበቀል የአያሌ ንፁሃን ኩርዳውያን እጅ ተቆርጧል። የኩርዶችን አመፅ ለማፈን በሚል ሰበብ ከ100 በላይ የኩርድ ሙሁራንን በጆንያ ጠቅልሎ በመስፋት ወደ ቫን ሐይቅ እንዲወረወሩ ተደርጓል። በአሜሪካ ሰራሽ ጀቶች 5000 ኩርዶችን የጨፈጨፈው የ1980ዎቹ የሀላባጃው ድብደባ በኩርዶች ትዝታ ውስጥ መቼም አይጠፋም።

በኢራቅ የሚገኙት ኩርዶች አበሳም የከፋ ነበር። በተለይ በሳዳም ሁሴን አገዛዝ ዘግናኝ የጅምላ ጭፍጨፋ ተደርጎባቸዋል። በ1980ዎቹ መጀመሪያ በኢራቅ እና ኢራን መካከል የተደረገው ጦርነት ዳፋውን በኩርዶች ላይ አሳርፏል። በዚህ ጦርነት ላይ ኩርዶቹ ለኢራን ወግነው ኢራቅን ወግተዋል በሚል ኩርፊያ  በኬሚካል የጦር መሳሪያ በጅምላ እንዲጨፈጨፉ አድርገዋል። በዚህ ረገድ ኬሚካል አሊ እየተባለ እስከመጠራት የደረሰው የሳዳም አንድ ባለስልጣን ለዚህ ወንጀል ግምባር ቀደም ሚና እንደነበረው በታሪክ ይወሳል።

በሶሪያ ያሉት ኩርዶችም ተመሳሳይ ፍዳ በልተዋል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሀገሪቱን ሙሉ ዜግነት አይሰጡም፡፡ ቋንቋውን መናገር፣ ባህላቸውን ማራመድ፣ አይፈቀድላቸውም ነበር።  በ1949 ዓ.ም የሶሪያ አረብ ብሔርተኝነት አባል እንደሆኑ የሚጠረጠሩ ሀይሎች በአንድ ቲያትር ቤት ውስጥ ባስነሱት ቃጠሎ ከ250 በላይ የኩርድ ሕፃናት ለህልፈት ተዳርገዋል።

የነፃነት ትግል

በየሄዱበት በያሉበት ተመሳሳይ ግፍ እያስተናገዱ የቀጠሉት ኩርዶች ከ20 ክፍለ ዘመን የጀመረው የሀገርነት ጥያቄ ምላሽ ሳያስገኝ ወደ 21ኛው ክፍለ ዘመን ተሻግሯል። የኩርድ ሕዝብ ይህን ያህል በደል ሲያስተናግድ በተደራጀ መንገድ ለመብቱ የሚታገልለት የተደራጀ ሀይል ማሰባሰብ የተጀመረው ዘግየት ብሎ ነበር። በተለይ ከ1980 እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሁለት የኢራቅ ኩርድ ቡድኖች ተመስርተዋል።  የኩርዲስታን ዲሞክራቲክ ፓርቲ የተባለው በማሱድ ብራዚያኒ የሚመራው እና በጃላል ታላባኒ የሚመራው ፓትሪዮቲክ ዩኒየን ኦፍ ኩርዲስታን በመባል የሚታወቀው ይጠቀሳሉ። እነርሱም በሰሜን ኢራቅ ስልጣን ለመጋራት ብርቱ ትግል አድርገው የማታ ማታ ቢያንስ የኢራቅ አንድ ራስ ገዝ የመሆን መብት አስከብረዋል።

በዚህ መካከል በምህፃረ ቃሉ ፒኬኬ እየተባለ የሚታወቀው የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ በቱርክ ደቡባዊ ምስራቅ ክፍል የሽምቅ ውጊያ ያወጀ ፓርቲ በ1970ዎቹ ላይ ተደራጅቶ እስከዛሬም ይታገላል። ፒኬኬ ማንኛውም ነፃ የኩርዳውያን ግዛት ለመላው ህዝብ መኖሪያ መሆን እንዳለበት ጠንካራ አቋም የሚያራምድ ድርጅት ሲሆን ከቱርክ መንግስት ጋር ከፍተኛ ትንቅንቅ ሲያደርግ የቆየ አንጋፋ ድርጅት ሲሆን በታዋቂው አብደላ ኦቻላን ይመራ ነበር።

በአብደላ ኦቻላን የሚመራው ፒኬኬ እና በብራዚያኒ የሚመራው ኬዲፒ በቱርክ እና በኢራቅ ወሰኖች ግዛት ተቆጣጥረው ይታገሉ የነበረ ቢሆንም የጋራ ስምምነት ግን አልነበራቸውም። እናም ትግላቸው የተናጠል በመሆኑ ሀገራትን የተናጠል ጥቃት መመከት ፈተና ነበር። ያም ሆኖ የፒኬኬው መሪ አብደላ ኦቻላን ከቱርክ ወደ ኬንያ ተሰድዶ ከሚኖርበት ተይዞ ቱርክ ዘብጥያ ወርዶ ሞት ተፈርዶበት እስከዛሬ ቆይቷል። ይህም ሆኖ ትግሉ ግን ቀጥሏል።

አዲስ ተስፋ

የኩርድ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት ከአምስት በላይ በሆኑ ሀገራት ውስጥ እየባዘነ የሚኖር ተንከራታች ፍትህ ያጣ ህዝብ ከሆነ በቅርቡ የዘመናት እንቆቅልሽን ይፈታ ይሆናል የሚል ተስፋ ብልጭ ያለ ይመስላል። በቱርክ ታስሮ የሚገኛው የፒኬኬ አማፂው ቡድን መሪ አብደላ ኦቻላን ለታጣቂዎቹ የትጥቅ መፍታት ጥያቄ በማቅረብ ከቱርክ መንግሥት ጋር የሰላም ድርድር እንዲኖር ነገሮች የተመቻቹ ይመስላል። ይህ ደግሞ የዓለም ሚዲያዎችን ያነጋገረ እንዲሁም የዘመናት ጥያቄዎችን ምላሽ የሚሰጥ ያህል ተደርጎ እየታሰበ ይገኛል  ። በሲሪያም ከአላሳድ በኋላ የመጣው አዲሱ መንግስት ከሶሪያ ኩርዶች ጋር የሰላም ስምምነት ላይ እንደደረሱ እየተነገረ ይገኛል። እኛም ፍትህ ያጣው የኩርድ ሕዝብ መልካሙ ሁሉ እንዲገጥመው እየተመኘን በዚሁ አበቃን።

(መሠት ቸኮል)

በኲር የመጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here