ስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ተማሪዎችን ማስተማር የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2016 ዓ.ም ዕቅድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ የተከሰተው በትጥቅ የታገዘ ግጭት የተማሪ ምዝገባ እና ትምህርት በወቅቱ እንዳይጀመር አድርጓል፡፡ በዚህም የክልሉ ትምህርት ቢሮ ታኅሳሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም እንዳስታወቀው የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት የማጠቃለያ ፈተና በሚሰጥበት ወቅት ተመዝግበው በትምህርት ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ቁጥር ሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብቻ ናቸው፡፡ አሁንም ድረስ ቀሪዎቹ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብለው ወደ መማር ማስተማር ለማስገባት በቅንጅት እየተሠራ ስለመሆኑ ቢሮዉ አስታውቋል፡፡
አንጻራዊ ሠላም ካገኙ በኋላ ወደ መደበኛ መማር ማስተማር ከገቡ አካባቢዎች መካከል አንዱ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነው፡፡ የከተማው ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አበባው ግዛቸው እንዳስታወቁት ያጋጠመው ክልላዊ የፀጥታ ችግር እንደ ቀደሙት ዓመታት ሁሉ የተማሪ ምዝገባ እና የመማር ማስተማር ሂደቱ በወቅቱ እንዳይጀመር፣ የመማሪያ ግብዓቶች እና የትምህርት ቤት የገጽታ ግንባታዎች ቀድመው እንዳይከናወኑ አድርጓል። እስካሁንም ትምህርት ያልተጀመረባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ችግሩ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋ እንዳይፈጠር የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል።
ያም ሆኖ በከተማ አስተዳድሩ እና ዙሪያው ገጠራማ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው 41 ትምህርት ቤቶች መማር ማስተማር መጀመሩን አስታውቀዋል። ቀጣይነቱን ለማረጋገጥም ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ውይይት መግባባት ላይ መደረሱን አንስተዋል። በቀጣይ ሕዝቡ የሰላም ባለቤት ሆኖ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት መላክ እንዲችል ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
በዞኑ መማር ማስተማር እየተካሄደባቸው ባሉ ትምህርት ቤቶች ግብዓት የማሟላት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑንም ኃላፊው አስታውቀዋል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ የተማሪ እና የመምህራን መቀመጫ ወንበር እንዲሁም የጥቁር ሰሌዳ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ ያጋጠመውን የመፃሕፍት እጥረት ለመፍታት ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው። በዚህም ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 34 ሺህ 285 መጻሕፍት ተሰራጭቷል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ መደረግ የጀመረው በተያዘው የትምህርት ዘመን ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያጋጠመው የመጻሕፍት እጥረት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ፈተና እንዳይሆን ትኩረት መደረጉን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በመፃሕፍት አቅርቦት እና ስርጭት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሮ መቆየቱን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ አልፎ አልፎ በተፈጠረው የመንገድ መከፈት መጻሕፍት ወደየትምህርት ቤቶች ገብተው እንዲሰራጩ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በዚህም እስካሁን ከ14 ሺህ 300 በላይ መጻሕፍት ለትምህርት ቤቶች ደርሰው መሰራጨታቸውን አቶ አበባው አስታውቀዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ በተለይ ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሁሉም መጻሕፍት በጊዜ ደርሰዋቸው እንዲዘጋጁ በማድረግ የክልሉን ወደ ዩኒቨርሲቲ የማስገባት ምጣኔ ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ዞን 924 የመጀመሪያ እና 72 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ:: ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች 633 ሺህ 326 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ታቅዷል፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር የትምህርት ዓመቱ በወቅቱ እንዳይጀመር ከማድረግ ባሻገር ዕቅዱ እንዳይሳካ ማድረጉን የዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊው አቶ ጌታሁን ፈንቴ አስታውቀዋል፡፡ በዞኑ ያለውን የሰላም ሁኔታ መሰረት በማድረግ ቀስ በቀስም መማር ማስተማር እየተጀመረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከመምህራን እና ከትምህርት አመራሩ ጋር ውይይት ማካሄድ፣ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች የመጠገን እና ሐብት ንብረታቸውን የማደራጀት ሥራ ወደ መማር ማስተማር ከመገባቱ ቀድሞ የተከናወኑ ሥራዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎች ሊፈቱ የሚችሉት በተማረ ዜጋ በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ እና መቆጣጠር እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
መምህራን ከተለመደው የመማር ማስተማር ሥነ ዘዴ ወጥተው ሙሉ ጊዜያቸውን በትምህርት ቤት እንዲያሳልፉ እና የማካካሻ ትምህርት አጠናክሮ መስጠት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡ በፀጥታ ችግር እየተፈተነ ያለውን መማር ማስተማር የትምህርት ግብዓትም ተጨማሪ ፈተና ሆኖ በተማሪዎች ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳይፈጥር ከወዲሁ መጻሕፍት ማሰራጨት ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡
እንደ አቶ ጌታሁን ማብራሪያ የመማሪያ መጻሕፍት ወደ ክዘና ማዕከላት መግበታቻውን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የተሽከርካሪ እጥረት ወደ ትምህርት ቤቶች በወቅቱ ለማድረስ ፈተና መሆኑን አስታውቀዋል፡፡:
የትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እየሩስ መንግሥቱ በበኩላቸው በትምህርት ዘመኑ 13 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን መጽሐፍት ለማሰራጨት ዕቅድ ተይዟል፡፡ ከዚህ ውስጥ እስካሁን አምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን መጽሐፍት ለአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሰራጨቱን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 918 ሺህ 76 መጽሐፍት ተሰራጭቷል፡፡
ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚውል ሰባት ነጥብ አራት ሚሊዮን መጻሕፍት ከውጭ ታትመው የገቡ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ገልጸዋል። በመጋዘን የተቀመጡትን በማከፋፈል ለመማር ማስተማር ተግባሩ እንዲውሉ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ግን አሁንም የትምህርት ዘርፉን ክፉኛ እየፈተነው ስለመሆኑ ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡ ማሳያቸው ደግሞ ሦስት ሚሊዮን መጽሐፍት በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ማሰራጨት አለመቻሉ ነው፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም