የትምህርት ሽፋን እና ጥራትን የሚያሳድጉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑ ተጠቆመ

0
75

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ የትምህርት ተሳትፎን በሚያሳድጉ እና ጥራትን በሚያረጋግጡ ሥራዎች ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ጎጃም እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች እንዲሁም ከአዊ ብሄረሰብ፣ ከባሕር ዳር ከተማ እና ደብረታቦር ከተማ አስተዳደሮች ጋር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን በባሕር ዳር ከተማ ገምግሟል፡፡ በዚህ ወቅት የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አንዷለም አቤ (ዶ/ር) በከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ቤቶችን መሠረት ልማት ማሟላት፣ ገጽታ ማሻሻል እና የተማሪ ምገባን እንደ ትምህርት ሽፋን ማሳደጊ እና የትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ አድርገው እየሠሩበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 

የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት እና ገጽታን ለማሻሻል 158 ሚሊዮን ብር ፈሰስ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ከመንግሥት በጀት በተጨማሪ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የኅብረተሰቡ እና የፕሮጀክቶች ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡

እንደ ከተማ አስተዳደር ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ላይ ሰፊ ችግር ያለ በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት ለመሥራት ዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል፡፡

 

የትምህርት ቤት ምገባ ሌላው በትኩረት እየተሠራበት ያለ ጉዳይ መሆኑን አንዷለም (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ ኃላፊዉ ጥናትን መነሻ አድርገው እንዳስታወቁት በከተማ አስተዳደሩ አሥር ሺህ ሕጻናት ቁርሥ ሳይበሉ ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ፡፡ ከቤት ሳይበሉ ቁርሳቸውን አዘግይተው ለመብላት ይዘው የሚመጡትም ከበቂ በታች የሆነ እና ያልተመጣጠነ ምግብ መሆኑን እንደታዘቡ ነግረውናል፡፡

 

ከተማ አስተዳደሩ አመጋገብ በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ላይ የሚያሳድረውን ጫና በመረዳት የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባን በቁርጠኝነት ይዞ እየሠራበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለፕሮግራሙ ዕውን መሆንም በመንግሥት 20 ሚሊዮን ብር፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች 13 ሚሊዮን ብር፣ በሕዝቡ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡ ምገባው በዋናነት መሠረት ያደረገው የቅድመ መደበኛ እና የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ነው ያሉት አንዷለም (ዶ/ር)፣ በፕሮግራሙ 17 ትምህርት ቤቶች እና ዘጠኝ ሺህ 237 ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ይህ ከተማ አስተዳደሩ በዚህ ዓመት የምገባ ተጠቃሚ አደርጋቸዋለሁ ብሎ ካቀዳቸው 10 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ ነው፡፡

 

ምገባ በተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች አርፋጅ ተማሪዎች አለመኖራቸውን፣ ቀሪ መቀነሱን፣ የትምህርት አቀባበል ላይ ከፍተኛ መሻሻል መምጣቱን ለፋይዳው ማሳያ አድርገው አንስተዋል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here