በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ አንቀጽ 26 ንኡስ ቁጥር ሁለት እና የኢኮኖሚ ፣ የማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ዓለም አቀፍ የቃልኪዳን ሰነድ አንቀጽ 13 ሥር በግልጽ እንደተደነገገው “የትምህርት ዓላማ የሰውን ልጅ በተሟላ እድገት ለማራመድ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶችን እና መሠረታዊ ነጻነቶችን ለማክበር የሚደረገውን ጥረት ማጠናከር /ማገዝ/ ነው። ከዚህ አንጻር ትምህርት የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ እድገት / አካላዊ ፣ አዕምሯዊ እና ሥነ-ልቦናዊ/ የማምጣት ዓላማ አለው።”
ሰብአዊ መብቶች እርስ በርስ ተደጋጋፊ፣ ተዛማጅ እና የማይነጣጠሉ ስለሆኑ ይህ መብት በራሱ መሠረታዊ የሆነ እና ሁሉም የሰው ልጆች ያለ ምንም ልዩነት ሊጠቀሙበት የሚገባ መብት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የሰብአዊ መብቶች መከበርም እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚቆጠር ነው። ስለሆነም ትምህርት የማግኘት መብት በአግባቡ አለመተግበር ሌሎች ሰብአዊ መብቶች እንዲጣሱ ምክንያት ይሆናል።
የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን ትምህርት የማግኘት መብትን በዝርዝር እና ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ የተነተነ ሕግ ነው ማለት ይቻላል። ይህ የቃልኪዳን ሰነድ በአንቀጽ 13 ንኡስ ቁጥር አንድ ላይ አባል ሀገራት ሁሉም ሰው ትምህርት የማግኘት መብት እንዳለው ዕውቅና እንደሰጡ የሚያሳይ ነው:: ሰነዱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎችም ይዘረዝራል። ሰነዱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት በግዴታ በነጻ መቅረብ እንዳለበት፤ የቴክኒክና ሙያ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በአጠቃላይ ለሁሉም ክፍት፣ ተደራሽ እንዲሆን አስፍሯል::
ትምህርት ሁሉም ዜጋ ያለክፍያ የመማር መብት እንዳለው አባል ሀገራት ቢስማሙም በዓለማችን በአምባገነን መንግሥታት እና በእርስ በርስ ጦርነቶች እና ግጭቶች ምክንያት ከ430 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት እና ታዳጊዎች ለትምህርት ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ይኖራሉ:: ሌሎች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከትምህርት በመፈናቀል እንደሚሰደዱ በ2017 እ.አ.አ የተደረገው የሰላም ኮንፈረንስ ላይ መነሳቱን መረጃዎች አመላክተዋል::
በ2023 እ.አ.አ የወጣው የዩኒሴፍ እና የሴቭ ዘ ቺልድረን ሪፖርት ደግሞ ግጭት እና ጦርነት የትምህርት ዕድልን ከሚዘጉ ችግሮች ዋናው ሆኗል:: በዓለማችን ከትምህርት ገበታ የተነጠሉ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል:: በተለይ ደግሞ የታዳጊዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው::
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ የመን፣ በርማ፣ ጋዛ፣ ዩክሬን፣ ናጎርኖ ካራባኽ እና ሌሎችም በግጭት ቀጣናዎች የሚኖሩ በርካታ ታዳጊዎች በትምህርት ዕጦት የሚቀጡባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን በየጊዜው የሚወጡ ዓለም አቀፍ ዘገባዎች ያመላክታሉ::
በሱዳን በአሁኑ ጊዜ ከሦስት ሕፃናት አንዱ ወይም 6.5 /ሥድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን/ ሕፃናት በብጥብጥ እና በፀጥታ መቃወስ የትምህርት ዕድል አጥተዋል:: በግጭት ቀጣናዎች 10 ሺህ 400 ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል:: ጦርነቱ በይፋ ከመጀመሩ ከሚያዝያ ወር በፊት ሰባት ሚሊዮን ታዳጊዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ነበር:: ከነዚህ ውስጥ አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ታዳጊዎች ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ አስቻይ ሁኔታ መኖር አለመኖሩን ባለሥልጣናት ማረጋገጫ መስጠት አለመቻላቸው ታውቋል:: በሀገሪቱ ጦርነቱ ተባብሶ የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ አንድም ታዳጊ የትምህርት ቤት ደጅን መርገጥ እንደማይችል መረጃዎች አመላክተዋል::
ግጭት በተፈጠረባቸው ቀጣናዎች ትምህርት ቤቶች መውደማቸው እና የተማሪዎች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁ ዓለም አቀፍ ችግር ሆኗል:: ለአብነት በግጭት ቀጣናዎች የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ለማጠናቀቅ የሚበቁ ተማሪዎች ቁጥር 30 በመቶ ብቻ ናቸው:: በስደተኞች /ተፈናቃዮች/ መጠለያ ውስጥ ከሚገኙ ሕፃናት ውስጥ ደግሞ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚጨርሱ 50 በመቶ ብቻ ናቸው::
ዕድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ ታዳጊዎች ውስጥ ዘጠኝ በመቶዎቹ /64 ሚሊዮን/ ትምህርት ቤት እንዳልገቡም ቀደም ብሎ እ.አ.አ. በ2017 የወጣው መረጃ ይጠቁማል:: በዋናነት በትምህርት እጦት ወይም መቋረጥ ተጎጂ የሚሆኑት ደግሞ በታዳጊ እና በደሀ ሀገራት የሚገኙ ታዳጊዎች ናቸው::
መረጃው እንዳስነበበው የትምህርት እጦት በትውልዱ ላይ የጤና ዕጦት፣ የገቢ መቀነስ እና የተስተካከለ የአዕምሮ ጤና እጦት ያስከትላል:: አንድ ታዳጊ ከትምህርት ገበታ የሚርቅበት ጊዜ በረዘመ ቁጥር ደግሞ የሚመለስበት ዕድል እየጠበበ ነው::
ዓለም አቀፉ የሕፃናት ፈንድ ሪፖርት እንደሚጠቅሰው እ.ኤ.አ. በ2020 በመላው ዓለም በትምህርት ቤቶች ላይ 535 ጥቃቶች ተፈጽመዋል:: ይህ ቁጥር ደግሞ በ2019 ከነበረው 17 በመቶ ያደገ ነው::
በሴራሊዮን እ.አ.አ. ከ1991 እስከ 2002 በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት 14 ሺህ ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ ተነጥለው ለጦርነት ተማግደዋል:: ይህ ሁኔታ ደግሞ አሁንም ቢሆን እንደ ሶሪያ እና የመን ባሉ የግጭት ቀጣናዎች ሲደጋገም ይታያል::
በግጭት ቀጣና ያሉ ታዳጊዎች በተለይ ሴቶች ያለ ዕድሜያቸው ለማግባት ከመገደድ ጀምሮ ፆታ ተኮር ችግር ይገጥማቸዋል:: እ.አ.አ. በ2023 በዓለም በአማካይ በቀን ከሁለት ዶላር በታች በሆነ አነስተኛ ገቢ ኑሮን የሚገፋ ሕዝብ ቁጥር 648 ሚሊዮን መሆኑን መረጃው ያመላክታል:: ለዚህ ችግር ቀዳሚው መንስኤ ደግሞ የትምህርት እጦት ወይም ማቋረጥ ነው:: በሪፖርቱ የትምህርት እጦትን የዘለዓለም የድህነት ነቀርሳ የሚያስከትል ችግር ሲል አስፍሯል::
ጥቅምት ወር 2023 እ.አ.አ ሪፓርተር ጋዜጣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር እና ተባባሪ ፕሮፌሰር በላይ ሐጎስን ጠቅሶ እንደዘገበው ግጭት እና ጦርነት በትምህርት ላይ ከባድ ተፅዕኖ እንዳላቸው አንስተው:: “በመላ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት /በኮሮና፣ በድርቅ፣ በጎርፍ፣ በጦርነት…/ በተከሰቱ ችግሮች የትምህርት መደነቃቀፍ እያጋጠመ ነው:: ለዚህ ሲባል የትምህርት ሥርዓቱን ማጠናከር ያስፈልጋል:: ለሚገጥሙ የትምህርት መስተጓጎል ችግሮችም ምላሽ አሰጣጥን ማጠናከር ያስፈልጋል” በማለት ገልጸዋል::
ባለሙያው አክለውም ኢትዮጵያ በትምህርት መቆራረጥ ችግር አዙሪት ውስጥ መገኘቷን እና ከ1960ዎቹ ጀምሮ ብዙ ትውልድ በዚህ ችግር መባከኑን አውስተዋል:: “ከ1966 እስከ 1970 ዓ.ም መምህራን የሌሉበት፣ ሥርዓቱ የተረበሸበት ነበር:: በሶማሊያ ጦርነት፣ የኢሕአፓ አባል በመሆን፣ በድርቅ እና ረሀብ ብዙ ተማሪዎች ትምህርት ሳያገኙ ሕይወታቸው ተቀጥፏል:: ያ ችግር ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ተመልሶ እንደገና መጣ:: ይህ ራሱን መልሶ የሚደግም የትምህርት ዘርፍ የቀውስ አዙሪት ነው” በማለት በየጊዜው ሀገሪቱን ያጋጠሙ የትምህርት መስተጓጎሎችን አንስተዋል::
በዓለም በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የሰላም እጦቶች በትምህርቱ ዘርፋ ላይ እያደረሱት ባለው ችግር ኢትዮጵያም ዋናዋ ሰለባ መሆኗን መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ለአብነት የበኲር ጋዜጣ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በዕውቀት ጎዳና ዐምድ ለንባብ ባወጣው ዘገባ ላይ ”በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው በትጥቅ የታገዘ ግጭት አንድ ዓመቱን ሊደፍን ተቃርቧል:: በእነዚህ ጊዜያት ከሦስት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ከመማር ማስተማር ውጪ ሆነው ከርመዋል:: በዚህም ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል” ሲል መዘገቡ ይታወሳል::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም