ዓለም ከፍታዋን ያረጋገጠችበት የትምህርት ዘርፍ ዛሬ ላይ እጅጉን እየተፈተነ ነው:: የዓለምን ሕዝብ ወደ አንድ መንደር ማሰባሰብ የቻለውን የቴክኖሎጂ ዘርፍ መፍጠር የቻለው ትምህርት ዛሬ ደግሞ መጥፊያው ሆኖ ብቅ ብሏል:: በትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ጣሪያ ላይ ቁጭ ብለናል የሚሉን ኃያላኑ ሀገራት ሳይቀር ዛሬ ላይ የትምህርት ሥርዓታቸው እየተፈተነ ይገኛል:: ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የእርስ በእርስ ግጭቶች እና ድንበር ዘለል ጦርነቶች ናቸው:: ግጭቶች የትምህርት ተቋማት እንዲወድሙ እና የውስጥ ግብዓታቸው እንዲዘረፍ ከማድረግ ጀምሮ የትምህርት ሽፋን ተደራሽነትን በእጅጉ ይፈትናሉ::
የትምህርት ሥርዓቱ በእጅጉ እንዲፈተን እያደረጉ ካሉ ሌሎች ምክንያቶች መካከል በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ዓለም በተደጋጋሚ እያጋጠማት ያለውን ድርቅ ተከትሎ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ይገኝበታል:: ይህም ሰዎች መኖሪያ ቀያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ከማድረግ ጀምሮ ለኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች እንዲጋለጡ በማድረግ ሚሊዮኖች ታዳጊዎች ከትምህርት እንዲርቁ አድርጓቸዋል:: ነባራዊ ሁኔታው የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ነው:: የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትምህርት እና የትምህርት ሥርዓት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መውደቁን በተደጋጋሚ ሲያስታውቅ ቆይቷል፤ በዓለም ላይ ከ222 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን አስታውቋል::
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚያመለክተው ከላይ በተጠቀሱት ችግሮች ምክንያት እ.አ.አ በ2022 ብቻ 100 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለዋል:: ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ዛሬ ተምረው ለነገዋ ዓለም የተሻለ መሆን አስተዋጽኦ የነበራቸውና ትልቅ ሕልም ያላቸው ታዳጊዎች እና ወጣቶች ናቸው:: ድርጅቱ ግጭቶች በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያስረዳው እ.አ.አ ከጥር 2020 እስከ ታኅሳስ 2021 ባሉት ጊዜያት በ85 ሀገራት በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ አምስት ሺህ ጥቃቶች መፈጸማቸውን፣ የትምህርት ተቋማት ለወታደራዊ ማዘዣነት መዋላቸውን፣ ዘጠኝ ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች እና መምህራን መጠለፋቸውን፣ መታሰራቸውን፣ ለአካላዊ ጉዳት መዳረጋቸውን እና መገደላቸውን በመጠቆም ነው::
የአፍሪካ ሕብረት 37ኛውን የሕብረቱን ጉባኤ ባካሄደበት ወቅት እንዳስታወቀው ግጭቶች፣ ጦርነቶች እና ሌሎች ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በአህጉሪቱ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ከትምህርት ውጪ ሆነዋል::
ዓለም አቀፉ የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እ.አ.አ ነሐሴ 8 ቀን 2024 ይፋ ባደረገው ሪፖርት ኢትዮጵያ ያጋጠማት ግጭት 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት እንዲርቁ አድርጓቸዋል:: ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው:: የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የትምህርት ሚኒስቴርን የ2016 በጀት ዓመት እና የአንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን በጥቅምት ወር በገመገመበት ወቅት እንዳስታወቁት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የቀጠሉ ግጭቶች በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት ከነበረባቸው ተማሪዎች መካከል 26 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆኑት በጦርነት፣ በድርቅ፣ በጎርፍ እና መሰል አደጋዎች መምጣት አልቻሉም ብለው ነበር::
ትኩረቱን ትምህርት ላይ አድርጎ የሚሠራው ግሎባል ሲቲዝን በበኩሉ በኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የሰሜኑ ጦርነት በትምህርት መስኩ ላይ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ መሆኑን ያስረዳል:: እስከ 2013 ዓ.ም መጨረሻ ከሰባት ሺህ በላይ የትምህርት ተቋማት ለጉዳት ተዳርገዋል:: ጉዳት ያልደረሰባቸው ትምህርት ተቋማትም ለወታደራዊ ካምፕነት ውለዋል፤ ይህም በርካታ ተማሪዎች እና መምህራን ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል::
በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋም እና ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ሚያዚያ 04 ቀን 2016 ዓ.ም እንዳስታወቀው ከሆነ ደግሞ ጦርነቱ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እስከ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ጉዳትን አስከትሏል:: በዚህም ሁለት ሺህ 935 የትምህርት ተቋማት ከቀላል እስከ ከባድ ውድመት እንደደረሰባቸው ነው ያስታወቀው::
ግጭቶች ዛሬም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀጥለዋል። በዚህም ምክንያት ሚሊዮኖች ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል። ትምህርትን ትኩረት አድርጎ የሚሠራው አቴንዳንስ ራዳር (attendance radar) የተባለው ድረ ገጽ ተማሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህፍት ገበታ ከራቁ ዘርፈ ብዙ ቀውስ እንደሚያስከትልባቸው ያብራራል። ችግሩ በተለይ በሴቶች ላይ እንደሚከፋ የጠቀሰው የመረጃ ምንጩ ለዚህ ደግሞ ከባሕል ተፅዕኖ ባሻገር ያለባቸው ተደራራቢ ኃፊነት መሆኑን ያነሳል።
እንደ መረጃው ከሆነ ከትምህርት ገበታ የራቁ ታዳጊዎች የትምህርት አቀባበላቸው በእጅጉ ይቀንሳል፣ የማህበራዊ መገለል ስሜት ያድርባቸዋል፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ጉልበት ብዝበዛ እና መሰል ማሕበራዊ ቀውሶች ይገጥማቸዋል። ለዚህ በተጨማሪም የአዕምሮ ጤና መታወክ ሊያስከትል እንደሚችል ነው የጥናት ውጤቶችን ዋቢ አድርጎ ያብራራው። የመደፈር አደጋም ሊያጋጥም እንደሚችል በመጠቆም ችግሮቹ ተደራርበው የታዳጊዎቹ ነገ እንዲጨልም ያደርጋል ነው ያለው።
በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው እና ሁለተኛ ዓመቱን በያዘው በትጥቅ የታገዘው ግጭት ከሦስት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ተማሪ እንደናፈቁ ሳይከፈቱ እንዲባጁ አድርጓቸዋል:: ከትምህርት ውጪ የሆኑ ተማሪዎች ቁጥርም ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ መሻገሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል:: መምህራንም ከሚወዱት ትውልድ የማነጽ ሙያቸው ተገልለው እንዲቆዩ አድርጓቸዋል::
የሰላም እና ደኅንነት ችግሩ የተማረ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ላይ እያሳደረ ካለው አሉታዊ ጫና ለመውጣት ልዩነቶችን በንግግር እና ድርድር ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ሁሉም ሊደግፍ ይገባል:: ትምህርት የትምህርት ግብዓት እና የመማሪያ ክፍል መሟላት ብቻ ሳይሆን የወደፊት ሕይወትን ብሩህ አድርጎ ለማስቀጠል ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ በግጭት ውስጥ የሚገኙ አካላት ለትምህርት ልዩ ከለላ ሊሠጡም ይገባል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም