የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም
በሕዝብ ከተሰጣቸው አናሳ ግምት፣ በተዓምር ከሞት ካመለጡባቸው ሙከራዎች፣ የተፎካካሪያቸው የካማላ ሐሪስ የተጋጋሉ የቅስቀሳ ዘመቻዎች እና ሌሎች በእንጥልጥል ያሉ ገና ያልለየላቸው የፍርድ ቤት ክሶች፣ የሚዲያዎች የሰላ ትችት እና በመሳሰሉ ከባባድ ተግዳሮቶች መሀል “ሜክ አሜሪካ ግሬት ኤጌን” የሚል መሪ መፎክራቸውን እያስተጋቡ ለማሸነፍ እስከ ደም ጠብታ ተፋልመው ማሸነፋቸው፣ የሚጠሏቸውን ሳይቀር መላው ዓለም በፅናታቸው ተገርሟል።
እስከመጨረሻው ተተንባይ ያልነበረው የምርጫ ውጤት የማታ ማታ ይፋ መሆን ሲጀምር ድል በአስገራሚ ሁኔታ ወደ ዶናልድ ትራምፕ ማዝመሙን የሚያሳዩ የቁጥር ልዩነቶች መውጣት ጀመሩ። አብላጫ መቀመጫ ባላቸው በተለምዶ እስከመጨረሻው ማን እንደሚመረጥ በማይታወቅባቸው ትላልቅ ግዛቶች ሳይቀር ትራምፕ አሸነፉ፤ በአጠቃላይ አሜሪካ የአብዛኛው የዓለም ዓይኖች ያረፉባትን ተጠባቂዋን ካማላ ሀሪስን ቀጥታ፣ አይኗን ጨፍና ብዙም ያልተገመቱትን ዶናልድ ትራምፕን ከእነ ችግራቸውም ቢሆን አይኗን ጨፍና መርጣለች። ዶናልድ ትራምፕ 297 ለ 225 በሆነ በዝረራ በሚባል ሰፊ ልዩነት በማሸነፍ ቀጣዩ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት መሆናቸው እርግጥ ሆኗል።
የትራምፕ ደጋፊዎች በድሉ ሲፈነጥዙ ድል የጠበቁት የካማላ ደጋፊዎች በውጤቱ አዘኑ። ነገር ግን የትራምፕ መመረጥ ፌሽታ እና ሀዘኑ በአሜሪካ ውስጥ ተወስኖ አልቀረም። ዓለም ከጫፍ እስከ ጫፍ እንደ አሜሪካውያኑ ሁሉ የምርጫው ውጤት የተለያዩ ስሜቶች ደርሰውበታል። መላው ዓለም የአሜሪካን የምርጫ ውጤት እንደየሀገሩ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የተለታያዩ ፍላጎቶች ሲንፀባረቁ እንደመቆየታቸው በመጨረሻው የትራምፕ ድል ሲበሰር መላው ዓለም የተለያዩ ምላሾችን መስጠቱ ታይቷል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ የተመራጩ ዶናልድ ትራምፕ ዳግመኛ ወደ አሜሪካ የስልጣን ማማ መመለስ፣ ጦርነት እና ግራ መጋባት ሰቅዞ ለያዛቸው ለበርካታ የዓለማችን ክፍሎች መሰረታዊ ለውጥ የማድረግ ተስፋ በመስጠት የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ እንደገና ለማስተካከል ታስቧል።
ዶናልድ ትራምፕ በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት ምንም እንኳ ዝርዝር ማብራሪያዎችን የመስጠት ቢኖርባቸውም “አሜሪካ ትቅደም” በሚል የተለመደ መርሀቸው መሰረት ጥቅል የፖሊሲ ተስፋዎችን ሰጥተዋል።
የዶናልድ ትራምፕ ድል ብዙ ዓመታት አሜሪካ ትከተል በነበረው የውጭ ፖሊሲ አካሄድ ላይ እጅግ ወሳኝ አቅም ያለው የተለየ አቅጣጫ የመከተል ምልክቶችን ሰጥቷል። በመሆኑም ሰውየው ከሚሰጧቸው ሀሳቦች እና ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በከወኗቸው የስራ ታሪካቸው አንፃር በማገጣጠም በዓለም ፖለቲካ ሊከተሉ የሚችሉትን አካሄድ ማየት ይቻላል።
የአሜሪካ ተፅእኖ ጉልህ በሆነባቸው መቋጫ ያጡ ብቻ አይደለም፤ ዓለምን ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት እንዳያስገቡ በሚፈሩት በመካከለኛው ምስራቅ እና በሩሲያ እንዲሁም በዩክሬን መካከል የተለኮሱት አደገኛ ግጭቶች የጋረጧቸው ዓለማቀፋዊ የፖለቲካ ውጥንቅጦች እንዲቋጩ፣ ብሎም የኔቶ መፃኢ እድል እና ከቻይና ጋር ያለው የሻከረ ዲፕሎማሲ የመፍትሄ ቁልፉ አሜሪካ በምትመርጠው መሪ እንደሚከተለው የውጭ ፖሊሲ ይወሰናል። እናም ዓለም ለትራምፕ ድል የሰጠችው ምላሽ እንደየ ሀገሩ ፍላጎት መዘበራረቁን መገናኛ ብዙሃን አሳይተዋል።
24 ሰዓታት ለዩክሬን እና ለሩስያ ግጭት
አትላንቲክ ካውንስል የተሰኘው የትንታኔ ድረገፅ ላይ እንደወጣው ዘገባ ዶናልድ ትራምፕ በምረጡኝ ቅስቀሳው ወቅት የዩክሬን እና የሩሲያን ጦርነት በአንድ ቀን ማስቆም እንደሚችሉ ደጋግመው ይናገሩ ነበር። እንዴት ተብለው ሲጠየቁ፣ ሁለቱን በማደራደር የሚል ሀሳብ ያነሳሉ፣ ነገር ግን ዝርዝር አካሄዱን ለመስጠት አይፈልጉም።
የቀድሞ የትራምፕ ሁለት የደህንነት ባለስልጣናት በፃፉት ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ እንደተቀመጠው አሜሪካ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማድረጓን መቀጠል እንደሚገባ፣ ነገር ግን ድጋፉን ኬቭ ከሩሲያ ጋር ወደ ስምምነት እንድትገባ ቅድመ ሁኔታ በማድረግ እንደሚሆን ይናገራሉ።
ፍራንስ 24 ቴሌቪዥን እንደዘገበው ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የሰላም ድርድር ለማድረግ እራሷን እንድታዘጋጅ እና እንደ ክሪሚያ እና ሌሎች በሩሲያ የተያዙ ግዛቶች እንዲመለሱላት መጠየቅ ማቆም እንዳለባት ለዘለንስኪ አስቀድመው ቁርጡን አስታውቀዋል። ለሩሲያም ከዩክሬን ጋር ለመስማማት ዝግጁ መሆን እንዳለባት አለበለዚያ ግን ለዩክሬን እስካሁን ከሚደረግላት የበለጠ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደሚደረግ በማስጠንቀቅ ጦርነቱን የማስቆም አቅጣጫ ለመከተል እንደታሰበ አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ለፕሬዝደንት ቪላድሚር ፑቲን ይወግናል እያሉ በሚከሷቸው የዲሞክራት ፓርቲ ተቀናቃኞቻቸው፣ ይህ የትራምፕ አካሄድ ዩክሬንን ተሸናፊ የሚያደርግ እና መላ አውሮፓን አደጋ ላይ እንደሚጥል ይናገራሉ። ትራምፕ ግን በአቋማቸው ፈርጠም በማለት ዋና አላማቸው ጦርነቱን ማስቆም እና የአሜሪካን ሀብት ከአላስፈላጊ ብክነት መታደግ እንደሆነ ማስረዳታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ይሁን እንጅ ለትራምፕ መልካም ምኞታቸውን የገለፁት ፑቲን ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገር የመንግሥታቸውን ዝግጁነት ማሳወቃቸውን ተከትሎ፣ ትራምፕ በ24 ሠዓታት ጦርነቱን ለማስቆም ማሰባቸው እውነታውን ያላገናዘበ እንደሆነ አስረድተዋል። በርካታ ተንታኞች እንደገለፁትም ግጭቱ አሁን ያለበት ውስብስብ ሁኔታ ትራምፕ እንዳሰቡት ጦርነቱን በአንድ ጀምበር ለማስቆም ከባድ መሆኑን ያስረዳሉ።
የኔቶ እጣ ፋንታ
አዲሱ ተመራጭ ዳግም ወደ አሜሪካ ፕሬዝዳንትነት መመለስ በኔቶ መፃኢ እድል ዙሪያ አውሮፓውያኑን አሳስቧል። አውሮፓ በትራምፕ ዘመን የአሜሪካ ከኔቶ የመውጣት ሁኔታ ዳግም ሊያገረሽ ይችላል የሚል ስጋት አድሮባታል። እንደ ትራምፕ አቋም ኔቶን በተመለከተ ግልፅ ባይደረግም ከሚከተሉት ፖሊሲ የተለየ ሲሆን የቃልኪዳኑ አባል ሀገራት በተስማሙት መሰረት ሁለት በመቶ ከብሔራዊ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ለኔቶ ወታደራዊ በጀት የማዋጣት ሀላፊነታቸውን ካልተወጡ አሜሪካ በአባልነት እንደማትቀጥል የትራምፕ አቋም ነው። ይህም ከፍተኛውን የኔቶን በጀት የምትሸፍነው ኃያሏ አሜሪካን ማጣት ኔቶን አደጋ ላይ ስለሚጥል አውሮፓውያንን ከወዲሁ አስጨንቋል።
“አሜሪካ ትቅደም” በሚል የሚታወቁት ትራምፕ አሜሪካን ከኔቶ አጋርነት አስወጡም አላስወጡ እንዳለ ሆኖ፣ ሀሳቡ ግን ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል የዘለቀውን የትራንስ አትላንቲክ ወታደራዊ ግንኙነት እንዲያከራክር ማድረጋቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል።
ሰላም ለመካከለኛው ምስራቅ
ሮይተርስ እንደዘገበው ዶናልድ ትራምፕ ለመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ሰላም እንደሚዘይዱ ተስፋ ሲሰጡ በተደጋጋሚ ተሰምተዋል። በጋዛ ያለውን የእስራኤል ሀማስን ጦርነት እና የእስራኤል ሂዝቦላ ጦርነት እንደሚያስቆሙ ተስፋ ከመስጠት ባለፈ እንዴት እንደሚሰጡ ምንም አልገለፁም።
ከባይደን ይልቅ እርሳቸው ስልጣን ይዘው ቢሆን ኖሮ ሀማስ እስራኤልን ባላጠቃ ነበር በማለት ደጋግመው ይናገራሉ፤ ምክንያቱን ሲገልፁ ደግሞ ለቡድኑ የገንዘብ ድጋፍ በምታደርግለት ኢራን ላይ እርሳቸው በሚከውኑት ከፍተኛ ጫና የማድረግ ፖሊሲያቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
ይሁን እንጅ ለእስራኤል የምንግዜም ወዳጅ እንደሆኑ በኔታኒያሁ የተወደሱት ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ የሚከተሉት ፖሊሲ ቀጠናውን የማተራመስ ውጤት እንደሚኖረው ተችዎች ይሞግታሉ።
ፍልስጥኤማውያን የሚያነሱትን የኢየሩሳሌም ይገባኛል ጥያቄን ዋሽንግተን ውድቅ በማድረጓ የትራምፕን አስተዳደር አውግዘውት ነበር። በተጨማሪም ትራምፕ “አብርሃም አኮርድ” የሚባለውን፣ እስራኤልን እና ከአረብ ሀገራት እና ሙስሊም ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ትስስሮችን የማጠናከር እቅድ፣ አስፈፃሚ በሆኑበት ወቅት ፍልስጥኤማውያን የበለጠ መገለላቸውን ያስታውሳሉ።
በአጠቃላይ በአወዛጋቢነታቸው የሚታወቁት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ ታላቋ አሜሪካ የስልጣን መንበር የመለሳቸውን ሰፊ የሕዝብ ይሁንታ አግኝተው አዲሱን አስተዳደራቸውን በማዋቀር ላይ ይገኛሉ። አሁን የሀገር ውስጥ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በተደቀኑበት እና ዓለም ከመቼውም ጊዜ በተለየ ውስብስብ ችግሮች በተዘፈቀችበት አጋጣሚ ዳግም የአሜሪካ ስልጣን ሲያገኙ ከባድ ኃላፊነት እንደወደቀባቸው ተገንዝበው ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ ዓለም ይጠብቅባቸዋል። ምናልባትም ከአሁን በፊት በዓለም ዘንድ ያጡትን ተቀባይነት መልሰው የሚያድሱበት እድሉን ለመጠቀም የሚተጉበት ልብ ገዝተው ተመልሰው ይሆን? ሁሉንም አብረን እናየዋለን፡፡
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም