የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ምን ይዟል?

0
101

የሀገራችን ግብርና አንጋፋ ዘመንን ያስቆጠረ ቢሆንም ከዕድሜው ጋር ወደፊት መራመድ አልተቻለውም፤ በመሆኑም ኢትዮጵያዊያንን እንኳን ሙሉ በሙሉ መመገብ እንደተሳነው በየጊዜዉ ይደመጣል ። ችግሩን ለመፍታት ታዲያ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን ከጥረቶች መካከልም  የግብርና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ደግሞ ተስፋ የተጣለበት ነው።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የክልሉን የአሥር ዓመት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን በተመለከተ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል። ዕቅዱም ክልሉ ያለውን ዕምቅ አቅም በመጠቀም ምርታማነትን በከፍተኛ መጠን ማሳደግን ዋና ዓላማ ያደረገ ነው፤ ዝርዝር ጉዳዮችም ቀርበው ሐሳብ ተሰጥቷል።

በውይይት መድረኩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ እንደተናገሩት ግብርና ከክልሉ ባለፈ እንደ ሀገርም  ዋነኛው የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው፤ አርሶ አደሩ የዓለም ገበያን አስቦ እንዲያመርት በተለይም ከምግብ ሰብሎች ባሻገር የኢንዱስትሪና የኤክስፖርት ሰብሎችን በስፋት እና በጥራት እንዲያመርት የክልሉ መንግሥት ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱንም ተናግረዋል። ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ከዕለታዊ ፍጆታ (ከቀለብ) ባለፈ የተሻለ አምርቶ ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ ማቅረብ እና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ማምረት ይገባል፤ ለዚህ ደግሞ ግብርናውን ከኋላ ቀር አሠራር በማላቀቅ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ማስታጠቅ ይገባል።

አቶ አረጋ አክለውም ግብርናውን ለማዘመን የተጀማመሩ ሥራዎች ቢኖሩም ያለውን ፀጋ ተጠቅሞ ግብርናው በሚፈልገው ደረጃ እና ስፋት የሚጠበቀውን ውጤት አስገኝቷል ለማለት አያስደፍርም ብለዋል። ለዚህ ደግሞ እንደየ ፀጋው እና እንደየ መልማት አቅማችን ግብርናውን መምራት አለመቻል ስለመሆኑ ነው ያነሱት። በመሆኑም ፀጋዎችን በአግባቡ ለመጠቀም በተሻለ ዕቅድ መመራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ችግሮቹን ለይቶ መፍትሔ በመስጠት፣ ጸጋዎችንም በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ታዲያ በቂ ጊዜ በመስጠት፣ ሀብት እና ባለሙያዎችን በመመደብ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ሥራ ለማስገባት ሲሠራ ቆይቷል፤ ይህም የክልሉ ፍኖተ ካርታ አንዱ አካል የሆነው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ርዕሰ መሥተዳድሩ እንዳሉት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ግብርናውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ እገዛው ከፍተኛ ነው። በግብርናው ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን ከመሠረቱ በመፍታት ክልሉ ያሉትን ፀጋዎች በአግባቡ ለይቶ ለመጠቀም ያስችላል። በመሆኑም ለተግባራዊነቱ ሁሉም  ባለድርሻ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ሌላው በውይይት መድረኩ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ለግብርና ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፤ የግብርናው ዘርፍ ሰፊ ሕዝብ የሚሳተፍበት፣ በርካታ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት እና ሰፊ ሀብት የሚሠበሠብበት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ይህ ሁሉ ታስቦ መሠራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ በሜካናይዜሽን (በትራክተር) የሚታረሰው መሬት አምስት ሚሊዮን ሄክታር ያህል ነው። የአማራ ክልል ከፍተኛ ፀጋ እንዳለው ያነሱት ሚኒስትሩ ይህም ለኢትዮጵያ ትልቅ አቅም እንደሆነ ጠቅሰዋል። ዶክተር ግርማ እንዳሉት የአማራ ክልል የሀገሪቱን አንድ ሦስተኛ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ ያበረክታል፤ ዘርፉን ከዚህ በላይ ለማሻሻል ታዲያ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

“ግብርና የሀገራችን ምጣኔ ሃብት ዋልታ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ ቢሆንም ተጨባጭ ለውጥ አለመገኘቱን እና ዘርፉን ማዘመን አለመቻሉን አንስተዋል። በመሆኑም “ግብርናው ከቃላት ባሻገር” በተግባር ለውጥ ማምጣት አለበት” ብለዋል።

ስለ ግብርና ብዙ ነገር ተብሏል፤ ይሁን እንጂ ምርታማነቱ ከእጅ ወደ አፍ አልተሻገረም:: ከበሬ ጫንቃ፣ ከዝናብ ጥገኝነት እና ከሌሎች ኋላቀር አሠራሮችም አልተላቀቀም። ለዚህ መሠረታዊ ምክንያቶች በቂ እና ተጨባጭ እርምጃዎች አለመወሰዳቸውም ነው።

“ግብርናው በሰጠነው ልክ ይሰጠናል” ያሉት ሚኒስትሩ መንግሥት ሀገር በቀል አቅጣጫን በመከተል ተግባራዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል። ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እና እሳቤ ለመከተል አቅጣጫ ስለመቀመጡም ነው ያመላከቱት። ፖሊሲው ግብርናው የት ተነስቶ የት መድረስ እንዳለበት እና አቅሞችን እንዴት መጠቀም እንደሚገባ ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተቃኝቶ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል።

ሚኒስትሩ እንዳስገነዘቡት ለግብርና ሥራ ማነቆ ሆነው የቆዩ አሠራሮችን ለማዘመን እየተሠራ ይገኛል። አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች በተናጠል ሊገዟቸው የማይችሏቸውን ማሽነሪዎች በመደራጀት እንዲገዙ የብድር ፖሊሲ እና አቅጣጫም ተቀምጧል። ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ከ500 በላይ የእርሻ ሜካናይዜሽን እና የመስኖ ልማት ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲሆኑ ተደርጓል። አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮችም የእርሻ ትራክተር እና የምርት መሰብሰቢያ ማሽን (ኮምባይነር) ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ተደርጓል።

ይሁን እንጂ የጥገና ችግር አሁንም ድረስ ቅሬታ እየቀረበበት ያለና ያልተፈታ ችግር መሆኑ ተወስቷል። በዚህ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን የተጋሩት ሚኒስትሩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ሁሉን አይነት ሥነ ምህዳር ያለው ነው፤ ይህን ጸጋ በመጠቀም የግብርና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ስኬታማ እና  ግብርናውንም ማዘመን እንደሚገባ ዶክተር ግርማ አመንቴ አስገንዝበዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ባለፉት ዓመታት መንግሥት የግብርና ዘርፉን ካለበት ኋላቀር አሠራር ወደ ዘመናዊ ለማሸጋገር የማሻሻያ እርምጃዎችን ወስዷል። የአፈር ማዳበሪያ ድጎማ በማድረግ በመጠን እና በወቅቱ እንዲቀርብ ከፍተኛ ጥረት መደረጉ፣ የእርሻ ሜካናይዜሽን (ትራክተርና ኮምባይነር) መሣሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መደረጉ እና ለአርሶ አደሩ የብድር አቅርቦት መመቻቸቱ ዋና ዋናዎቹ ተግባራት ናቸው።

የተዘጋጀው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማነቆዎችን በመለየት መፍትሄውንም ያስቀመጠ ነው፤ በመሆኑም ሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ብዙ ሀብት እየፈሰሰበት እና መዳረሻ ግቦች ተቀምጠውለት እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ናቸው። “በሀገር በቀል ሀሳብ፣ ሀብት እና አቅም የግብርናውን ዘርፍ ልማት በአግባቡ ከተጠቀምንበት ብዙ ማልማት እንችላለን” ብለዋል ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ሀገር በቀል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከ2013 ዓ.ም እስከ 2022 ዓ.ም ይተገበራል፤ በዚህም ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አቶ ተመስገን ተናግረዋል።

በአግባቡ ከተሠራ በየክልሎቹ በርካታ አቅሞች እና የመልማት ዕድሎች መኖራቸውንም በማንሳት፣ ዕቅዱን ለመፈጸም የሥራ ባሕልን ማዳበር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በግብርናው ዙሪያ ያሉ ሀብቶችን አቀናጅቶ ማልማት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የሥራ ባሕልን ማጎልበት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ዕቅዱን በውጤታማነት ለመፈፀም በቁጭት መነሳት እና በቁርጠኝነት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአማራ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን የአስር ዓመት ፍኖተ ካርታ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ፣ የአርሶ አደሩን ገቢ የማሳደግ፣ ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ የማቅረብ፣ የኤክስፖርት ሰብሎችን በስፋትና በጥራት በማምረት የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እና በዘርፉ ሰፊ የሥራ እድል የመፍጠር ግብ ያለው ነው፤ ፍኖተ ካርታው በግብርና ሚኒስቴርና በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩቱ በጋራ የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here