በአማራ ክልል ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ 10 ሺህ 874 ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሂደበት ወቅት ተመላክቷል:: ታዲያ በ2016 ዓ.ም በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ስድስት ሚሊዮን 292 ሺህ 241 ተማሪዎችን በመመዝገብ ማስተማር የክልሉ ትምህርት ቢሮ ዕቅድ ነበረ::
ይሁን እንጂ ከ2016 ዓ.ም ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው በትጥቅ የታገዘ ግጭት መጠነ ሰፊ የሆነ ሰብዓዊ ጉዳት፣ ምጣኔ ሐብታዊ ድቀት እና ማኅበራዊ ምስቅልቅል ከማድረሱም ባለፈ በተለይ የሰላም፣ ልማት እና ዕድገት መሠረት እንደሆነ የሚነገርለትን የትምህርት ዘርፍ ክፉኛ ፈትኗል:: የሰላም መደፍረሱ በወቅቱ የተቀሰቀሰው በክረምቱ ወቅት በመሆኑ የትምህርት ቤት የገጽታ የማስዋብ ሥራ ተስተጓጉሏል:: በበጎ ፈቃደኛ ወገኖች በየዓመቱ ይሰጥ የነበረው የማጠናከሪያ ትምህርት እና የአዲሱ የትምህርት ይዘት ትውውቅ አልተከናወነም፤ የተማሪ መጻሕፍት ስርጭት አልተካሄደም:: ይህም በአንድም ይሁን በሌላ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ያኮስሳል::
የጸጥታ ችግሩ ግን ዓመቱን ሙሉ ቀጥሏል:: ይህም የተማሪ ምዝገባ እና የትምህርት አጀማመሩ ወጥ በሆነ መንገድ ተጀምሮ እንዳይጠናቀቅ አድርጓል::
ክልሉን ያጋጠመው የሰላም እና ደኅነነት መናጋት በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ያለፉት 6 ሺህ 588 ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ በክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ወቅት አስታውቀዋል:: ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩት ተማሪዎች ቁጥር ደግሞ ሦስት ሚሊዮን 705 ሺህ 539 ብቻ ናቸው::
መፍትሄ ርቆት ዓመት ያለፈው በትጥቅ የታገዘ ግጭት 4 ሺህ 286 ትምህርት ቤቶች እና 2 ሚሊዮን 586 ሺህ 702 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው እንዲከርሙ አድርጓል:: የተፈጠረው የሰላም መታጣት በትምህርት ቤት ግንባታዎችም ላይ ጉዳት አድርሷል፤ ሐብታቸውንም እንዲያጡ አድርጓል::
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ደመላሽ ታደሰ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ለአሚኮ እንዳስታወቁት በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን በሁሉም የትምህርት ቤት ደረጃዎች ከ630 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለማስተማር ታቅዶ ነበር:: በዓመቱ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የከረሙት ግን ከስምንት ሺህ የማይበልጡት ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል:: ለዚህም ዋናው ምክንያት በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት እንደሆነ ምክትል ኃላፊዉ አስታውቀዋል::
በአሁኑ ወቅትም ለ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ጠንካራ የቅድመ ጅ ሥራ እየተደረገ እንደሚገኝ ታውቋል:: አዲሱ የትምህርት ዓመት ኅብረተሰቡ የሚካስበት እና ተማሪዎች ከደረሰባቸው የሥነ ልቦና ስብራት ነጻ የሚሆኑበት እንዲሆን ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል::
በ2017 ዓ.ም ቅድመ መደበኛን ጨምሮ ከ627 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ከነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪ ምዝገባ መጀመሩን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያረጋግጣል:: የምዝገባ ሂደቱም ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ወላጆች፣ መምህራን እና የትምህርት ቤት መሪዎች ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ምክትል መምሪያ ኃላፊዉ አሳስበዋል:: የታጠቁ ኀይሎችም ትምህርት ከየትኛውም ፖለቲካ ነፃ መሆኑን በመረዳት የተማሪዎች ምዝገባ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲከናወን እና የመማር ማስተማር ሥራው እንዲቀጥል ተባባሪ ሊሆኑ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል::
የሰሜን ወሎ ዞንም በዓመቱ ለሚከናወነው የመማር ማስተማር ሂደት ከወዲሁ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ቀርጾ እየሠራ ይገኛል:: እንደ ዞኑ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወንድወሰን አክሊሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በትምህርት ግብዓት አለመሟላት ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ ለመደገፍ ቀድሞ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው::
የትምህርት ግብዓት የማሰባሰብ ሥራው 42 ሺህ 222 ተማሪዎችን ተደራሽ እንደሚያደርግም ምክትል ኃላፊ መግለጻቸውን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ ያሳያል:: 27 ሺህ ደርዘን መማሪያ ደብተር፣ 10 ሺህ ባኮ እስክርቢቶ፣ ለአምስት ሺህ ተማሪዎች ዩኒፎርም ለማሰፋት ታቅዷል:: በመሆኑም ሁሉም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ ባለሐብቶች፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ግብር ሰናይ ድርጅቶች እና ሌሎች በጎ ፈቃድ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ምክትል መምሪያ ኃላፊዉ አስታውቀዋል::
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2017 ዓ.ም 6 ነጥብ 9 ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ማቀዱን አስታውቋል:: የትምህርት ዓመቱን በስኬታማነት ለማስቀጠል ከወዲሁ ትኩረት የሚሹ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል:: ቢሮው በመጀመሪያ ቅድሚያ ተሰጥቶ እንዲሠራበት ያስታወቀው ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሁሉም ህፃናት እንዲመዘገቡ እና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማስቻል እንደሚገባ ነው:: ሁሉም ነባር ተማሪዎች በወቅቱ እንዲመዘገቡ እና ትምህርታቸውን ከትምህርት መጀመሪያው ቀን ጀምሮ እንዲከታተሉ ማድረግ እንደሚገባም ቢሮው መመሪያ ሰጥቷል::
የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ መድረኮች በሁሉም አካባቢዎች እስከ ትምህርት ቤት ድረስ እንዲካሄድ ማድረግ እንደሚገባም ተመላክቷል። ኅብረተሰቡ ስለልጆቹ ትምህርት፣ ስለሚማሩበት ትምህርት ቤት ደረጃ እና ግብዓት አሁናዊ ሁኔታ መምከር፣ መወያየት እና መፍትሔ መስጠት እንዲችል ማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባም ተጠቁሟል::
የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ችግር በመንግሥት፣ በባለሐብቶች፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በግለሰቦች ተሳትፎ ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ቢሮው ጠቅሷል::
የትምህርት ቤት ምገባ ሥራ ለትምህርት ሥርዓቱ ውጤታማነት ፋይዳው ከፍተኛ ነው:: በመሆኑም በየደረጃው ያለው የትምህርት ባለድርሻ አካል የምገባ ሥራው የሚያስገኘውን ፋይዳ ለማኅበረሰቡ በጉልህ በማስረዳት ለተግባራዊነቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማድረግ ላይ እንዲተኮርም ጥሪ ቀርቧል::
ክልሉ ከገጠመው ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች አኳያ የግብዓት ችግሮች እንደሚኖሩ ታሳቢ በማድረግ “የአንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ” ንቅናቄን በስፋት እንዲሠራበት ቢሮው አስታውቋል:: በዚህም ደብተር፣ እስክብሪቶ፣ እርሳስ፣ ቦርሳ እና ዩኒፎርም በማሰባሰብ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች በማገዝ ወገናዊ አለኝታነታን ለመወጣት መትጋት ከሁሉም እንደሚጠበቅ ጥሪ ቀርቧል::
በየትምህርት ቤቶቹ የትምህርት መሠረተ ልማትን ማሟላት እና የተማሪዎችን ምዝገባ ቀድሞ ጀምሮ ቀድሞ ማጠናቀቅ እንደሚገባ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዉ ጌታቸው ቢያዝን አስታውቀዋል:: የ2017 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ተጀምሮ ጳጉሜ ላይ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም