የትናንት ፈተና፣ የዛሬ ወኔ እና የነገ ራዕይ

0
153

የሁለት ሺህ አስራ ስምንት የኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በሰበታ ከተማ እየተደረገ ይገኛል። በውድድሩ አምስት ክለቦች እየተሳተፉ ሲሆን በዚህ ውድድር ከሚሳተፉ ክለቦች መካከል ባሕር ዳር ከተማ የሴቶች የቅርጫት ኳስ ክለብ ይገኝበታል። ውድድሩ በአምስት ዙር የሚደረግ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ባሳለፍነው ቅዳሜ ተጠናቋል። የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ካለፉት ዓመታት በተለየ ወኔ እና ዝግጅት አድርገው ውድድር መጀመራቸውን የባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ክለብ  አሰልጣኝ እና ተጫዋች ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ የስፖርት ክፍል ዝጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

ክለቡ ባለፈው ዓመት ደካማ ውጤት ማስመዝገቡ አይዘነጋም፤ ከተሳተፉ አራት ክለቦች ውስጥ አራተኛ ደረጃን ይዞ መጨረሱም የሚታወስ ነው። አሰልጣኝ  በለጠ ፀጋ ያለፈውን ዓመት ክፍተቶች ደፍነው ዘንድሮ ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየሰሩ መሆናቸውን ነግረውናል።

በቂ ዝግጅት እና ልምምድ አድርገው ወደ ውድድር መግባታቸውንም አሰልጣኙ እና ተጫዋቾች ይገልጻሉ። ካለፈው ዓመት አንጻር ሲታይ የዘንድሮው ስብስብ ይበልጥ ጠንካራ እንደሆነም የቡድኑ አባላት ይናገራሉ። ከዚህ በፊት በወሊድ እና በተለያዩ ምክንያቶች ከስፖርቱ ርቀው የነበሩ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ መመለሳቸው ለክለቡ የተሻለ ጥንካሬ ሰጥቶታል።  የተጫዋቾቹ ቅንጅት እና ጥንካሬ ከበፊቱ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አሰልጣኝ በለጠ ፀጋ ያብራራል። “የተመለሱት ልጆች አሁን ባለው ሁኔታ ጥሩ ጥንካሬ አላቸው፤ ቅንጅታቸውም ጥሩ ነው፤ ይህንን ጠብቀን ከሄድን ጥሩ ተፎካካሪ ሆነን ዓመቱን እንጨርሳለን” ሲሉ አሰልጣኙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ታዲያ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ደረጃ ውስጥ ገብተው  ለማጠናቀቅ እቅድ መያዛቸውን የቡድን አባላቱ ተናግረዋል።

ባለፈው የውድድር ዓመት የባሕር ዳር ከተማ ሴቶች ቡድን በታሰበው ልክ ውጤት ማምጣት አልቻለም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ቡድኑ በተከላካይ እና በአማካይ ክፍል  የሚሰለፉ በቂ ረጃጅም ተጫዋቾች ስላልነበሩት ነው። ኳስ እንዳይቆጠርባቸው የሚከላከል፣ የግብ እድሎችን የሚፈጥር፣ እንደ ፖወር ፎርዋርድ እና ሹቲንግ ጋርድ ባሉ ቦታዎች ላይ ክፍተቶች እንደነበሩባቸው አልሸሸጉም።  ይሁን እንጂ ዘንድሮ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ወደ ቡድኑ የተቀላቀሉ እና ከታች ያደጉ ተጫዋቾች መኖራቸው  ችግሩን እንደሚቀርፍላቸው ተስፋ አድርገዋል።

አምና የውድድር መርሃ ግብር አወጣጥ ፍትሃዊ እንዳልነበር የተናገረችው የክለቡ ተጫዋች መስከረም አዲሱ ውድድሩ ወደ ማብቂያው በተቃረበበት ወቅት በተለይም በአራተኛው እና አምስተኛው ዙር ተጫዋቾቹ ምንም አይነት እረፍት ሳያገኙ ተከታታይ ጨዋታዎችን እንድናደርግ ታግደን ነበር ስትል ትናገራለች።

አሰልጣኝ  በለጠ ደግሞ “ተጫዋቾቹ ተማሪዎች ስለነበሩ እና ፈተና ላይ ስለነበሩ መርሀግብሩ እንዲራዘምልን ጠይቀን ነበር፤ ነገር ግን ውድድሩ ወደ ኋላ ሲገፋ ፕሮግራሙ የታጨቀ (ኮምፓክት) ሆነ። ልጆቹ ያለ ምንም እረፍት ነው የተጫወቱት፤ አንድ ቀን እርፍት እንኳን አልነበረውም። ይህ ደግሞ ዋጋ አስከፍሎናል” ብለዋል። ይህ አይነቱ የአመራር እና የፕሮግራም ችግር የተጫዋቾችን አካላዊ ብቃት ከመፈተኑም በላይ በውጤት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ያሳድራል። ዘንድሮ ግን ቡድናቸው ከእንደዚህ አይነት ጫናዎች ነጻ ሆኖ በቂ ዝግጅት አድርጎ እና በሳምንት አራት ቀናት ልምምድ እየሰራ ለውድድሩ ቀርቧል።

በኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ አብዛኞቹ ክለቦች ውጤት ለማምጣት ሲሉ የፋይናንስ አቅማቸውን በመጠቀም ከተለያዩ ክልሎች አልፎ ተርፎም ከውጭ ሀገራት (ለምሳሌ ከኬንያ) ተጫዋቾችን በውድ ዋጋ ገዝተው ያሰልፋሉ። የባሕር ዳር ከተማ ግን የተለየ መንገድን መርጧል። የቡድኑ አባላት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የከተማው ልጆች ናቸው።

እነዚህ ተጫዋቾች ከታዳጊ ፕሮጀክት ጀምሮ በአሰልጣኝ በለጠ ፀጋ እጅ  ያደጉ፣ እርስ በርስ በደንብ የሚተዋወቁ እና ለከተማቸው ክብር የሚጫወቱ መሆናቸው ለቡድኑ ልዩ ጥንካሬን ፈጥሮለታል።  የቡድኑ ተጫዋች ቤተልሔም ገበየሁ “የባሕር ዳር ከተማ የሚጫወተው ሙሉ በሙሉ ራሱ ባሳደጋቸው ተጫዋቾች ነው፤ እኛን ልዩ የሚያደርገን ከፕሮጀክት ጀምረን አንድ ላይ የመጣን ልጆች መሆናችን ነው” በማለት ቡድኑ የተገነባበትን መንገድ ታስረዳለች።

የስፖርት ትጥቅ እና ቁሳቁስ ችግር እንደሌለባቸው አሰልጣኝ በለጠ ተናግሯል። “በክለቡ በኩል የሚደረግልን ነገር አሪፍ ነው፤ ምግብ አለ፤ ትጥቅም ከዚህ በኋላ ይሟላል ተብለናል” ስትል ቤተልሄም  ገበየው ተናግራለች። ከሌሎች ክለቦች አንጻር የሚከፈላቸው ደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ግን አነስተኛ መሆኑን ተጫዋቾች አልሸሸጉም።

በአሁኑ ሰዓት በባሕር ዳር ከተማ የቅርጫት ኳስን በፕሮጀክትም ሆነ በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ክለብ ይዞ እያሰለጠነ ያለ  አሰልጣኝ በለጠ ብቻ ነው። “ባሕር ዳር ላይ የሚያሰለጥን  ጋሽ በለጠ ብቻ ነው፤ በጣም ብዙ የቀድሞ ተጫዋች ያለ ቢሆንም የሚሰራ ግን የለም” ስትል ቤተልሄም ገበየው ትናገራለች። ስፖርቱ በአንድ ሰው ትከሻ ላይ ብቻ ከወደቀ፣ ያ ሰው በደከመ ጊዜ ስፖርቱም አብሮ የመሞት እድሉ ሰፊ ነው። በመሆኑም የክልሉም ሆነ የከተማው ስፖርት አመራሮች ለአሰልጣኞች ስልጠና እና ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አሰልጣኝ በለጠ ይመክራል። በየክፍለ ከተማው እና በየተቋማቱ ውድድሮች ቢደረጉ፣ ታዳጊዎች የሚታዩበት እድል ቢፈጠር እና አዳዲስ አሰልጣኞች ቢመጡ ስፖርቱ የተሻለ ደርጃ ይደርሳል ብሎ ያምናል።

አሁን ያሉት የክለቡ ተጫዋቾች ከፕሮጀክት የወጡ ናቸው፤ ነገስ እነሱን የሚተካው ማነው? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ይፈልጋል። አሰልጣኝ በለጠ ክረምት ላይ ለታዳጊዎች ስልጠና ለመስጠት እቅድ ቢይዝም በበጀት እጥረት ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱን በቁጭት ይገልጻል። እናም ታዳጊ ፕሮጀክቱ የነገው የክለቡ ህልውና መሰረት በመሆኑ በደንብ ሊታሰብበት እንደሚገባ አሰልጣኙ ይጠቁማል።

ለስፖርቱ ፍላጎት ያላቸው ሰልጣኞች ቢኖሩም ያንን ማመቻቸት እና ማደራጀት ግን ይጠይቃል የሚሉት አሰልጣኙ እቅዳቸው በዚህ ዓመት እንደሚሳካ እምነት አሳድረዋል።  የሜዳ ችግር  ትልቅ እንቅፋት መሆኑን የቅርጫት ኳስ ተጫዋቿ መስከረም አዲሱ ትናገራለች። “ፕሮጀክት እንዲሰራ በቂ ሜዳ ማግኘት አለብን፤ ያሉትን ሜዳዎችን ለመጠቀም ግን ብዙ ጊዜ ፈቃድ እያጣን ነው፤ የፕሮጀክት ሰልጣኞች እየተንገላቱ ነው” በማለት ችግሩን ታስረዳለች።

የቡድን አባላቱ ልክ ለእግር ኳስ የተሰጠውን ያህል ትኩረት ለቅርጫት ኳስም መሰጠት አለበት ባይ ናቸው። እኛም የሚመለከተው አካል  ከክለቡ ጎን ሆኖ በመደገፍ የከተማውን የቅርጫት ኳስ ታሪክ ወደ ቀድሞው ዝናው ለመመለስ በሚደረገው ጉዞ የበኩሉን መወጣት ይጠበቅበታል የሚል እምነት አለን።  የኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ሁለተኛው ዙር በየካቲት ወር የሚጀምር ይሆናል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥር 11  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here