በኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ከተበሰረ በኋላ በኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ መስቀል፣ ገና፣ ፋሲካ /ትንሳኤ/ ጊዜያቸውን ጠብቀው ይከበራሉ፡፡ ከእነዚህ በዓላት መካከል የትንሳኤ በዓል በያዝነው ወር ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ይከበራል፡፡ ትንሣኤ የሚለው የግእዝ ቃል መገኛው ተንሥአ ፣ ተነሣ የሚለው ግስ ሲሆን ትርጕሙም መነሣት ፣ አነሣሥ፣ አዲስ ሕይወት ማግኘት ማለት እንደሆነ የኢትዮጵያ ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ያመላክታል፡፡
የትንሳኤ ክብረ በዓል ረጅም ሃይማኖታዊ ሥርዓት ያለው፣ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በጽኑ ፆም፣ ፀሎት፣ ሥግደት፣ ምህላ እና ተማጽኖ ከፈጣሪያቸው ጋር ለሁለት ወራት ገደማ ሲያደርጉት የቆዩትን ትስስር አጠናቀው የኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት መነሳት በማሰብ በተቻላቸው ሁሉ በደስታ እና በተድላ ለማሳለፍ በጉጉት የሚጠብቁት ቀን ነው። በዓሉ ከመንፈሳዊ ክዋኔው ባለፈ በመረዳዳት፣ በመተጋገዝ ፣ በመተሳሰብ፣ በመጠያየቅ በቤት ውስጥ የሚከበር ነው።
ለዚህም ነው ድምጻዊ ማናልሞሽ ዲቦ በሚስረቀረቀው ድምጿ፦
ጤና ለሰጠው ሰው እድሜውን ላደለው/ሁለት ጊዜ/
አውደዓመት ደስታ ነው፤ አውዳመት ፀጋነው፡፡
እሰይ መጣልን አውዳመት፣
ባሕላችን ዓውዳመት፣
ለዚህ ላበቃን ዓውዳመት፣
አምላክ ይመስገን አውዳመት… በማለት “አውዳመት” የተሰኘውን ዘመን የማይሽረው ሥራዋን ያበረከተችው፡፡
በዓሉ ከቅርብ እና ከሩቅ የሚኖሩ ቤተሰቦች፣ ጎረቤታሞች፣ ጓደኛሞች… በመገናኘት በደስታ ለማሳለፍ የሚጓጉለት ነው፡፡ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት የ68 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋው አቶ ወልደተንሣይ ገብሩ ለበኵር በሰጡት አስተያየት የበዓሉ ድባብ የሚጀምረው ገና ከፀሎተ ሐሙስ ነው፡፡ በዓሉ ጉልባን ማለትም ባቄላ ክክ እና ስንዴ ቅቅል ተቀቅሎ ለመብላት ጎረቤት ከጎረቤቱ ቡና በመጠራራት ከዚህ ነው የሚጀመረው፡፡ ቀጣዩ አርብ ደግሞ ሙሉው ቀን በቤተክርስቲያን ሕዝበ ክርስቲያኑ በአንድ ላይ በየአቅራቢያው በስግደት ካሳለፈ በኋላ የማታ ማታ ቡና ተፈልቶ፣ ድፎ ዳቦ ተጋግሮ በመገናኘት ተሰባስቦ በደስታ ያሳልፋል፡፡ ከሐሙስ ተርፎ ያደረው ጉልባንም የሚበላው በዚሁ ቀን እንደሆነ ያነሳሉ፡፡
አቶ ወልደተንሳይ እንዳሉት ቅዳም ሹር ወይም የበዓሉ ዋዜማ ቅዳሜ ደግሞ ለበዓል በግ፣ዶሮ፣ ለቅርጫ ከብት፣ ጨፌ እና ሌሎች ለበዓሉ የሚበሉ እና ማድመቂያ የሚሆኑት ይገዛሉ፡፡ ቤት ማዘጋጀቱም ሌላው የበዓል ሥራ ነው፡፡ እነዚህን ተግባራት ቀኑን ሙሉ ሁሉም ሲያከናውኑ ከዋሉ በኋላ የሚችል ማታ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ለመካፈል ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳል፡፡ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤት በመመለስ በፆም የቆየን ሆድ ለማለስለስ ተልባ በመብላት ይጀመራል፤ ዶሮ ከቤተሰብ
ታዲያ ያኔ ይላሉ አቶ ወልደተንሳይ፤ በቅርብ ጊዜ ኑሮው ሲወደድ እየቀረ መጣ እንጂ ለትንሳኤ በዓል ዶሮ፣ በግ እና የቅርጫ ሥጋ ይኖራል፡፡ ሁሉም ከቤት አልፎ ከቤተሰብ ጋር በመጠራራት ይውል ነበር፡፡ ይህም ትልቅ ማህበራዊ መስተጋብር የሚፈጠርበት እንደነበር ዛሬ አቶ ወልደተንሳይ በትዝታ ያስታውሱታል፡፡
የእርድ ሂደቱ በራሱ የተለየ ሥርዓት እንደነበረው የሚያነሱት አቶ ወልደተንሳይ፤ በቤተሰብ በኩል የመጀመሪያ እርድ የሚፈፀመው በዕድሜ ከትልቁ ቤት በመሄድ ነበር፡፡ ሳይበዛ ቀማምሶ ወደ ቀጣዩ ቤት እየተባለ ከጎረቤት እና ቤተሰብ ቤት በመዞር ቀኑ በጋራ በመብላት እና አብሮ በመጠጣት ያልፋል፡፡ ከቀጣዩ ቀን ጀምሮ ደግሞ በታረደበት ደረጃ ምሳ እና እራት በመጠራራት አብሮ በመብላት እና በመጨዋወት አይረሴ የፍቅር ጊዜ አሳልፈዋል፡፡
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወ/ሮ ማናሰብ ፈንቴ በበኩላቸው የፋሲካ በዓል ሲቃረብ መግደፊያ ለሌላቸው ነዳያን በየመንደሩ እየተዞረ ገንዘብ ሰብስቦ ከብት ገዝቶ በማረድ ስጋውን “እንኳን ለብርሐነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ!” በማለት ይታደላል፡፡ ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ድረስ ደግሞ ሕዝበ ክርስቲያኑ “እንኳን ለብርሐነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ!” እየተባባለ በዚህ መልኩ አብሮ እየበላ፣ እየጠጣ፣ እየተደሰተ እግዚአብሔርን ሲያመሰግን ይሰነብታል፡፡ ለሳቸው ትልቁ ትዝታ ደግሞ ቤተሰባቸው ብዙ ስለነበር ቤተሰቡን አንድ ቀን ጎረቤቱን ደግሞ ሌላ ቀን ስለሚጠሩ ሁለት ጊዜ በግ ለማረድ ይገደዱ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ወ/ሮ ማናሰብ ባለቤታቸውን በሞት ካጡ በኋላ ግን በግ ባያርዱም ቅርጫ ሥጋ አስገብተው ከቤተሰቡም ከጎረቤቱም ላለመለየት ያቅማቸውን አድርገው በዓሉን ያሳልፋሉ፡፡ አሁን ደግሞ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ሁሉም አቅም በማጣቱ መገናኘቱም ሆነ አብሮ መብላቱ እየቀነሰ ነው፡፡ በፋሲካ በእለቱ ብቻ ቡና ተጠራርቶ ወደ ማለፍ ሁሉ እየተሄደ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
በተለይ ከኮረና መከሰት በኋላ ባለው ጊዜ ገበያው እና ግብይቱም ቢሆን አንድም በዋጋ መናር በሌላም በኩል ያለው የሰላም መታጣት ያስከተለው ችግር እንደ ቀድሞው በደስታ ተሰባስቦ መብላት እና መጠጣቱ እየቀረ መምጣቱን ነው ወይዘሮ ማናስብ የነገሩን። በፊት በግም ፣ዶሮም፣ ሥጋም ይገባ የነበረ ሰው ዛሬ ዶሮ ብቻ አርዶ የሚውልበት አጋጣሚ ብዙ ስለሆነ ሰው መጥራትም ሆነ ሄዶ መብላት እየቀረ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ወ/ሮ ማናስብ እንደሚሉት በወላጆቻቸውም ሆነ በእነሱ ጊዜ የነበረው ትውልድ ከዘመዱም ከጎረቤቱም እየተጠራራ የሚበላ እና የሚጠጣ ነበር፡፡ አሁን ግን ቢጠራሩም ልጆች አብሮ ለመሔድ እንኳን ፈቃደኛ ስለማይሆኑ ከመቀራረቡ ይልቅ መራራቁ እየበዛ መሄዱን ከልጆቻቸው ጭምር የታዘቡት ነገር እንደሆነ ነው የሚያነሱት፡፡
በእነዚህ እና በኢኮኖሚ እጥረት እንደ በፊቱ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ሰዎች ከዘመዶቻቸው እና ከጎረቤቶቻቸው ጋር ተሰባስበው ደስታቸውንም ሆነ ችግራቸውን የሚወያዩበት፣ አንዱ ለሌላው ለችግሩም ሆነ ለደስታው ተጋሪ የሚሆንበት ጊዜ እየተሸረሸረ መጥቶ ትዝታ መሆኑን ከአስተያየት ሰጭዎች መረዳት ይቻላል፡፡ እናም አሁን ያለው ትውልድ ማኅበራዊ ትስስርን ከቀደምቶቹ መውረስ ይገባል! መልእክታችን ነው፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም