የትኛዉ ይሻላል?

0
99

በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች ተንቀሳቃሽ ስልኮችን እንዳይዙ መታገዱን እናንተ እንዴት ዓያችሁት?

እኔ በበኩሌ አዋጁ በፍጥነት መተግበር አለበት ከሚሉት ጎራ ተሰልፌያለሁ፤ለዚህ ደግሞ ብዙ ምክንያቶችን ማቅረብ እችላለሁ::

ተማሪዎች የእጅ ስልካቸውን እንዳይጠቀሙ መከልከል ኋላ ቀርነት ነው ብለው ለሚያስቡ ወገኖቼ በመጠቀማቸው ምን ተጠቀሙ? የሚል ማነጻጸሪያ ጥያቄ ማቅረብ ግድ ይለኛል::

የእጅ ስልካችን ትምህርት በሬዲዮ ከተማርን የቀድሞ ተማሪዎች እና ትምህርታቸውን በፕላዝማ ከተከታተሉ የቅርብ ጊዜ ተማሪዎች በተሻለ የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዳለው አይካድም:: ችግሩ ያለው ምን ያህል ተማሪዎች በእጅ ስልካቸው ይማሩበታል? የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ላይ ነው::

ምንም እንኳን ሃሳቤ በጥናት የተመለሰ መሆን ቢኖርበትም በአብዛኛው በዙሪያችን የሚገኙ ተማሪዎች የእጅ ስልካቸውን የሚጠቀሙት ለአልባሌ ነገሮች ነው:: ፌስ ቡክ፣ ቲክቶክ፣ ኢንስታግራም፣ ዩቲዩብ እና መሰል የማኅበራዊ ገጽ ትሥሥሮች ወጣቶችን በተለይም ተማሪዎችን የሌላ ዓለም እሥረኞች እንዳደረጓቸው አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል::

ተማሪዎች ገደብ በሌለው መልኩ በነዚህ የማኅበራዊ ገጾች ላይ ትኩረት ማድረጋቸው በትምህርታቸው ላይ ተጽዕኖ አያሳድርባቸውም ማለት አይቻልም::በእነዚሁ የቲክቶክ እና የፌስ ቡክ መንደሮች ለተማሪዎቹ የሚቀርቡት ጽሑፎች እና ምስሎች አብዛኞቹ በአቻዎቻቸው የተዘጋጁ በመሆናቸው ሃሳቦቻቸውን የሚጠልፉ ገመዶች አይሆኑም ለማለትም ያዳግታል:: የአቻ ግፊት አንዱ የመሰናከያ ገመድ በመሆኑ ማለቴ ነው::

ተማሪዎች በእጃቸው የሚይዟቸው ተንቀሳቃሽ ስልኮች እየተማሩ ባለበት ወቅት ድንገት ጥሪ ቢያሰሙ (ቢጮሁ) የሌሎች ተማሪዎችንና የአስተማሪያቸውን ሃሳብ አይበርዙም ብሎ መከራከርም ረብ የሌለው ክርክር ይሆናል::

ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ሆነው የእጅ ስልካቸውን ድምጽ አልባ (ሳይለንት) ቢያደርጉት እንኳን መልዕክቶች ሲላኩላቸው ስልኮቹ በሚኖራቸው ንዝረት ምክንያት ለመልዕክቱ ጉጉት ማሳደራቸው አይቀርም:: የሚደርሳቸውን መልዕክት እስካላዩት ድረስ አስተማሪዎች ከሚያስተምሩት ትምህርት በበለጠ ቀልባቸውን የሚወስድባቸው ጉዳይ እንደሚሆንም አያጠራጥርም::

ብዙ ወጣት ተማሪዎች በተለይም ወንዶች በእጅ ስልኮቻቸው የውጭ ሀገር እግር ኳስ ጨዋታዎችን ውጤት ይከታተላሉ፤ የዚሁ ውጤትን የመከታተል ፍላጎት ደግሞ በዕለታዊ ትምህርታቸው ላይ እንዳያተኩሩ ያደርጋቸዋል ብሎ አለማሰብ የዋህነት ነው::

በእጅ ስልኮቻቸው የሚደግፏቸውን ክለቦች ውጤት ከመከታተልም ባለፈ በውጤት ግመታ ውርርዶች (ቤቲንግ) ሱስ የሚጠመዱ ታዳጊዎች ቁጥርም “ብዙ” የሚባል ይሆናል:: ትምህርት እና ቁማር (ምንም እንኳን ውርርድ እያልን ስሙን ብናሰማምረውም) ደግሞ ፈጽሞ መሳ ለመሳ የማይሄዱ ተቃራኒ ነገሮች ናቸው::

ተማሪዎች ትምህርት ቤትን ጨምሮ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከእጅ ስልካቸው ጋር ሲያሳልፉ፣ አብረዋቸው ለሚውሉት የክፍል እና የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ጊዜ ያጣሉ:: በትምህርት ቤት ውስጥ ከጓደኛ የሚገኘውን አብሮነት እና ፍቅር ማጣት ደግሞ በየትኛውም የሥነ ልቦና መመዘኛ ቢመዘን ጉዳቱ እንደሚያመዝን አያጠራጥርም::

ከእጅ ስልካቸው ጋር ፍቅር የያዛቸው ታዳጊዎች በትምህርት ቤት ውስጥ ከሚያገኟቸው ጓደኞቻቸው እና አስተማሪዎቻቸው ጋር ከመራራቃቸውም በተጨማሪ ወደ ቤት ሲመለሱም ለቤተሰቦቻቸው የሚኖራቸው ፍቅርም ውስን ይሆናል:: በትምህርት ቤት ውስጥ በትምህርታቸው ምክንያት ለጥቂት ጊዜያት የተራራቁትን የእጅ ስልካቸውን እቤት እንደገቡ መጎርጎር የሚጀምሩ ልጆች ፍቅራቸው ከቤተሰባቸው ይልቅ በእጅ ስልካቸው ውስጥ ለሚያዩት ዝባዝንኬ እንደሆነም እርግጠኞች መሆን እንችላለን::

የእጅ ስልክን በትምህርት ቤቶች ውስጥ ይዞ መገኘት ለኩረጃም በር የሚከፍት ይመስለኛል:: በሙከራ ፈተናም ይሁን በዋናው ፈተና ወቅት ጎበዝ ተማሪዎች ለሰነፎች መልሶችን በእጅ ስልኮቻቸው በመላክ፣ ሰነፎች ይበልጥ ሰንፈው የሚቀጥሉበት ሁኔታም ይፈጠራል::

ተማሪዎች የእጅ ስልክ መያዛቸው ጉዳት እንጂ ፈጽሞ ጠቀሜታ የለውም የሚል ጭፍን ሃሳብ እንደሌለኝ በጽሑፌ መግቢያ ላይ ለመግለጽ ሞክሬያለሁ፤ ይልቁንም በአንጻራዊነት ስናየው ተማሪዎች በትምህርት ቤት ውስጥ በሚይዙት የእጅ ስልካቸው ከሚጠቀሙበት ይልቅ የሚጎዷቸው ነገሮች ይበዛሉ የሚል ጽኑ ዕምነት አለኝ:: ማሳያዎችን አሁንም እቀጥላለሁ::

በእጅ ስልካቸው ላይ ቁንጽል መረጃዎችን በፍጥነት ማግኘት እና ማንበብ የለመዱ ተማሪዎች ጥልቀት ላላቸው መረጃዎች ፍላጎትም ሆነ ጊዜ አይኖራቸውም::ሁሌም በውስጣቸው ያለውን ዕውቀት ሳይሆን የእጅ ስልካቸውን ዋቢ የሚያደርጉ ተማሪዎች በውስጣቸው የሚቋጥሩት ብዙም የክህሎት ስንቅ አይኖራቸውም::

በኔ የተማሪነት ዘመን ብዙ በማንበብ ብዙ ዕውቀት የሚሸምቱ ተማሪዎች (ሸምዳጆች እንላቸዋለን) ነበሩ፤እኛ እነዚህን ልጆች ሸምዳጆች እያልን ብንተቻቸውም እነሱ ግን ደብተሮቻቸውንም ሆነ መጸሐፎችን አብዝተው በማንበብ በብዙ የሚበልጡን ጎበዝ ተማሪዎች ናቸው:: የእጅ ስልኮቻቸው ከእጃቸው የማይለያቸው የአሁን ዘመን ተማሪዎች ግን ሸምድደው በውስጣቸው ከሚያስቀምጡት ይልቅ ከሞባይላቸው ላይ መረጃዎችን ለማግኘት ሲፈጥኑ ይስተዋላሉ::

በእጅ ስልካቸው ቁምነገርን ሳይሆን ጌሞችን ሲጫወቱ የሚውሉ ልጆች ደግሞ ይሄው ሱሳቸው ትምህርት ቤት ድረስ ተከትሏቸው በመሄዱ አስተማሪ ወጥቶ አስተማሪ እስኪተካ ባለው ጊዜ ሳይቀር ጌም የሚጫወቱ ሱሰኞች ይሆናሉ::

የጌሞች እና የእጅ ስልኮችን የመነካካት ሱስ ደግሞ ከሰው ተነጥሎ በራስ ዓለም ውስጥ መኖርን ያላምዳል::እነኚህ ክፉ ልማዶች ደግሞ ልጆችን በራሳቸው ምህዋር እንዲሽከረከሩ ከማድረጉም በላይ ሽክርክሪታቸው አጠገባቸው ያለውን እውነት ሳይቀር ስለሚደብቅባቸው በሥነ ልቦና ጎዶሎ ይሆናሉ::

በእነዚህ እና በሌሎችም መስፈሪያዎች ስናየው ተማሪዎች የእጅ ስልክ ይዘው ትምህርት ቤት ከሚገቡ ይልቅ የእጅ ስልክ አለመያዛቸው ይጠቅማቸዋል:: ወይም ደግሞ ተማሪዎች የእጅ ስልካቸውን ከሱስ በጸዳ መልኩ በአግባቡ ይጠቀሙበት ዘንድ አማራጮችን መፈለግ ጥሩ መፍትሔ ይሆናል::

በርካታ የዘመኑ ተማሪዎች ጫት፣ ሲጃራ እና ሀሺሽን ለመሰሉ ሱሶች ሲጋለጡ በእጃቸው የሚይዟቸው ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ምንም ሚና አልነበራቸውም ብሎ ማሰቡም ስህተት ነው:: በአለባበስ፣ በአነጋገር፣ በአመጋገብ እና በሌሎችም የኛ በሆኑ ነገሮች ላይ ተማሪ ልጆች ከባሕላቸው ሲያፈነግጡ እያየን በስልካቸው የሚያዩት ነገር ምንም ለውጥ አላሳደረባቸውም ብሎ ማሰብም የዋህነት ብቻ ሳይሆን ስህተትም ጭምር ነው::

ተማሪ እና ወጣት የሆኑ ልጆች በሚይዟቸው ስልኮች ዙሪያ የቤተሰብ ክትትል እምብዛም በመሆኑ የወሲብ ቪዲዮዎችን (ፖርኖግራፊ) በማየት ጭምር ከኢትዮጵያዊ እሴቶች ላፈነገጡ ስህተቶች እና ላልተፈለገ እርግዝናም ጭምር እንደሚጋለጡ ነጭ ነጩን መነጋገር ይኖርብናል::

የእጅ ስልኮቻቸው ጥገኛ የሆኑ ተማሪዎች ስለ ሀገራቸው እና ስለ ሕዝባቸው በመጸሐፍ መልክ የተከተቡ ታሪኮችን የማወቅ ዕድላቸው ጠባብ ነው:: ለእነዚህ ዓይነት ወጣቶች ከአድዋ ታሪችን ይልቅ የሆሊውድ እና ቦሊውድ ፊልሞች እውነተኛ ታሪኮች ይመስሏቸዋል:: ከኃይሌ ገብረ ሥላሴ ድንቅ የአትሌቲክስ ገድሎች ይልቅ  የጀስቲን ቢበር ኪናዊ ውድቀት ያሳስባቸዋል::

የእጅ ስልኮቻቸው ጥገኛ የሆኑ ተማሪዎች የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት ከማወቅ ይልቅ ከአድማሱ ባሻገር ያሉትን የውጭ ሀገር ከያኒያን እና የእግር ኳስ ተጨዋቾችን ማወቅ ይበልጥ አዋቂነት ይመስላቸዋል::

በእጅ ስልኮቻቸው ዙሪያ የታጠሩ ተማሪዎች አራቱን የሒሳብ መደቦች ማለትም መደመር፣ መቀነስ፣ ማባዛት እና ማካፈልን በህሊናቸው ከማስላት ይልቅ በእጅ ስልካቸው ላይ ባለው ሒሳብ መሥሪያ (ካልኩሌተር) ቁጥር ሲያሰሉ ይስተዋላሉ:: በዚህም ምክንያት የሒሳብ ዕውቀታቸው ምንም የሚባል ነው:: የታክሲ መልሳቸውን እንኳን ለማወቅ ሞባይላቸው ከኪሳቸው መዥረጥ የሚያደርጉ ከቁጥር የሸፈቱ አላዋቂዎች ይሆናሉ::

መቼም ትዝብቴ ሁሉንም የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ተማሪዎች  እንዳልሆነ ግልጽ ነው:: ግን ደግሞ በሞባይል ስልኮቻቸው ምክንያት በደብተሮቻቸው ላይ ያለውን የጊዜ ቤት ቁጥሮችን እንኳን የማያውቁ ብዙ ተማሪዎች እንዳሉ እሙን ነው::

እኔ ተማሪዎች ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮቻቸውን ይዘው ወደ ትምህርት ቤት አለመሄዳቸው ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል ባይ ነኝ፤ ለዚህም ምክንያት ያልኩትን በከፊል ለመግለጽ ሞክሬያለሁ፤ ከኔ በተቃራኒ ሃሳብ ያለው ደግሞ ሃሳቡን በማንሸራሸር እንማማርበት ዘንድ ጋብዣለሁ:: ለሁሉም የሀገራችን ተማሪዎች 2018 ዓ.ም መልካም የዕውቀት መገብያ ዓመት እንዲሆንላቸው ምኞቴ ነው::

 

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here