የትኞቹ ይደምቃሉ? የትኞቹስ ይወርዳሉ?

0
127

የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

የዘንድሮው የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ውድድር ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሯል። በመድረኩ 14 ክለቦች እየተፎካከሩ ነው። በትልቁ የሴቶች ሊግ አሸናፊ የሚሆነው ክለብ ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ላይ የሚሳተፍ ይሆናል። ጉልበታቸው ዝሎ ሊጉን መቋቋም ያልቻሉት ሁለት ክለቦች ደግሞ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ይወርዳሉ። ባሳለፍነው ዓመት በመድረኩ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ይርጋ ጨፌ ቡና ሊጉን መቋቋም ተስኗቸው ወደ ከፍተኛ ሊግ ወርደዋል። በእነርሱ ምትክም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና ባሕር ዳር ከነማ የሴቶች ቡድን ፕሪሚየር ሊጉን በመቀላቀል እየተፎካከሩ ይገኛሉ።
ባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ክለብ በ2013 ዓ.ም መጨረሻ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው። ነገር ግን የግዮን ንግሥቶች ሊጉን መላመድ ባለመቻላቸው በመጡበት ዓመት ተመልሰው ወደ ታችኛው የሊግ እርከን መውረዳቸው አይዘነጋም። ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ ድጋሚ ፕሪሚየር ሊጉን በመቀላቀል እየተፎካከሩ ነው። በ2014 ዓ.ም የነበሩባቸውን ችግሮች ላለመድገም የውድድር ዓመቱ ከመጀመሩ በፊት ሰፊ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ነው ወደ ውድድር የገቡት።
በአሰልጣኝ ሰርካዲስ እውነቱ የሚመሩት የግዮን ንግሥቶች ዐስር አዲስ ተጫዋቾችን አስፈርመዋል። 12 የሚሆኑ የነባር ተጫዋቾችን ውል አድሰዋል፤ አምስት ተጫዋችን ደግሞ በቢጫ ቴሴራ በማሳደግ ነው አዲሱን የውድድር ዓመት የጀመሩት። የቡድኑ አሰልጣኝ ሰርካዲስ እውነቱ በአካል ብቃት፣ በቴክኒክ እና በታክቲክ ተዘጋጅተው ወደ ውድድሩ መግባታቸውን ለአሚኮ ተናግራለች።
በሊጉ ተፎካካሪ እንዲሆኑ የስፖርት ክለቡ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ዋና አሰልጣኟ ተናግራለች። “ባሕር ዳር ከተማ የስፖርት ክለብ ከሌሎች በተሻለ ለሴቶች የሚያደርገው ድጋፍ ጥሩ ነው፤ እንደ ወንዶች እኩል ድጋፍ ይደረግልናል”። ብላለች አሰልጣኝ ሰርካዲስ። ምንም እንኳ ውድድሩ ፈታኝ ቢሆንም ከዚህ በፊት የነበሩባቸውን ክፍተቶች አርመው በፕሪሚየር ሊጉ ለመቆየት ነው ዕቅዳቸው። ባሕር ዳር ከተማ በመክፈቻው ሳምንት አዲስ አበባ ከተማን ሦስት ለባዶ ማሸነፉ አይዘነጋም፡፡
ሌላኛው አዲስ አዳጊው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው። ክለቡ በመጀመሪያ ሳምንት መርሀ ግብር በኢትዮ ኤሌክትሪክ አምስት ለባዶ በመሸነፍ መጥፎ አጀማመር አድርጓል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሻምፒዮን በሆነበት ባሳለፍነው ዓመት ሀዋሳ ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ መቻል እና ቦሌ ክፍለ ከተማ ጠንካራ ፉክክር ማድረጋቸው አይዘነጋም። እነዚህ ክለቦች ዘንድሮም ተጠናክረው ለመምጣት ከቅድመ ውድድር ዝግጅት ጎን ለጎን የተጫዋቾች ዝውውር ላይ በንቃት ተሳትፈዋል። የአምናው ሻምፒዮኑ ኡትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ለፕሪሚየር ሊጉ ጠንክራ ዝግጅት ሲያደርግ እንደ ከረመ በጥቅምት 25 ቀን 2017 በኵር እትማችን ማስነበባችን አይዘነጋም።
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ቡድን ባሳለፍነው ዓመት ካደረጋቸው 26 ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ነው የተሸነፈው። አምስት ጨዋታዎችን ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። በፕሪሚየር ሊጉ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚዎች እንደነበሩ የሚታወስ ነው። ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ቀጥሎ አነስተኛ ግቦች ከተቆጠሩባቸው ክለቦች ውስጥ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ይህም ቡድኑ በሁሉም የሜዳ ክፍል ምን ያህል አስፈሪ መሆኑን ያሳያል። ክለቡ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ላይም አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ዋንጫውን በማንሳት በሻምፒዮንስ ሊጉ የሚሳተፍ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ክለብ መሆኑን አረጋግጧል። በአዲሱ የውድድር ዓመትም ለዋንጫ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል።
በተመሳሳይ ሀዋሳ ከተማዎች በዚህ ዓመት የሊጉ ድምቀት ይሆናሉ ተብለው ከፍተኛ ግምት አግኝተዋል። አምና ጠንካራ ፉክክር በማድረግ ከንግድ ባንክ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ይዘው ነበር ያጠናቀቀቁት። ዘንድሮ ከአምናው የተሻለ ውድድር ለማሳለፍ ጠንካራ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ነው ዓመቱን የጀመሩት። በአሰልጣኝ መልካሙ ታፈረ የሚመሩት ሀዋሳዎች ከዐስር በላይ የተለያዩ ሥፍራ ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ የአራት ነባር ተጫዋቾችን ውል ደግሞ አድሰዋል።
ሀዋሳ ከተማ የሴቶች ቡድን በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ከንግድ ባንክ ቀጥሎ በዋንጫ ታጅበው ያጠናቅቃሉ ተብለው ሰፊ ቅድመ ግምት አግኝተዋል። ሀዋሳ ከተማ በመጀመሪያ ሳምንት መርሀ ግብር በሲዳማ ቡና ሦስት ለባዶ ተሸንፏል፡፡
ሌላው ባሳለፍነው ዓመት በሴቶች ሊግ ተፎካካሪ የነበሩ ዘንድሮም ያንን አቋማቸውን ይደግማሉ ተብለው የሚጠበቁት ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሴቶች ቡድን ናቸው። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ የኋላ ክፍል እንደነበረው በ2016 ዓ.ም ተመልክተናል። በውድድር ዓመቱ አነስተኛ ግቦች ብቻ እንደተቆጠሩባቸውም አይዘነጋም። ከወትሮው በተለየ ይበልጥ ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ ሰፊ ዝግጅት አድርገው ነው የ2017 የውድድር ዓመት የጀመሩት። ምንም እንኳ በርካታ ተጫዋቾች ቡድኑን ቢለቁም አስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው ቀላቅለዋል። የዘጠኝ ነባር ተጫዋቾችን ውል ደግሞ አድሰዋል። በአሰልጣኝ መሰረት ማኔ የሚመራው ቡድን ዘንድሮ የተሻለ የውድድር ጊዜ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።
መቻልም አስራ አንድ አዳዲስ ተጫዋቾችን እና የስምንት ነባር ተጫዋቾችን ውል በማደስ ቡድኑን አጠናክሯል። መቻል የሴቶች ቡድን አምና የታየበትን ግብ የማስቆጠር ችግር የሚቀርፍ ከሆነ በቀላሉ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ሊጉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እና ጠንካራ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ ከአዲስ አዳጊዎች ባሕር ዳር ከተማ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተጨማሪ አምና ከመውረድ ለጥቂት የተረፉት ልደታ ክፍለ ከተማ እና አዳማ ከተማም ዘንድሮ ይፈተናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዘንድሮ የውድድሩ መርሀ ግብር ቀድሞ በመውጣቱ ክለቦች ጥሩ ቅድመ ዝግጅት በማድረጋቸው ጠንካራ ፉክክር ይሆናልም ተብሎ ነው የተገመተው። ሻምፒዮን ለመሆን እና የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎን ለማረጋገጥ ከሚደረገው ትንቅንቅ ባልተናነሰ ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክርም ከወዲሁ አጓጊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የቅርብ ጊዜ ውድድር ነው። ገና 13 ዓመታት ዕድሜን ብቻ ነው ያስቆጠረው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ማራኪ እና ጥሩ ፉክክር የሚታይበት ሊግ ሆኗል። ምንም እንኳ ክለቦች የንግድ ባንክን ኃያልነት መግታት ቢሳናቸውም እስከ መጨረሻው ሳምንት መርሀግብር ድረስ የሚያደርጉት ተጋድሎ ሊጉ እንዲወደድ እና ድባቡ ደመቅ እንዲል አስችሎታል። የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ታዳጊዎች ዕድል የሚያገኙበት እና የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾችም የሚወጡበት ቢሆንም አሁንም ድረስ ግን ሊጉ በብዙ ችግሮች የተተበተበ ነው።
ይህንንም አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች በተዳጋጋሚ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው። በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የተጫዋቾች ክፍያ እና ጥቅማጥቅም ከወንዶች እኩል መሆን አለበት የሚለው የመጀመሪያ ቅሬታቸው ነው። የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ በዲኤስ ቲቭ ፣በቀጥታ ስርጭት መተላለፍ ከጀመረ አምስተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። የሴቶች ፕሪሚየር ሊግንም በቀጥታ ስርጭት ለማስተላለፍ ፊፋ ፕላስ (Fifa Plus) እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስምምነት አድርገናል ቢሉም እስካሁን አልተጀመረም።
ሌላው የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሲጀመር በየዓመቱ እንደ ችግር ከሚነሱ ጉዳዮች ውስጥ በቂ እና ጥራት ያለው የመለማመጃ ሜዳ አለመኖር ነው። ክለቦች በቂ እና ጥሩ የልምምድ ሜዳ ካላገኙ ተጫዋቾች በቀላሉ ለጉዳት ይጋለጣሉ፤ አሰልጣኙ የሚፈልገውን፣ የሚያዝዘውን ታክቲክ እና ቴክኒክም ተግባራዊ ለማድረግ እንከን ይፈጥራል። የዳኞች የብቃት ማነስ ከዚህ በፊት በነበሩ ውድድሮች አልፎ አልፎ እንደ ቅሬታ ይነሳ እንደነበረ አይዘነጋም። የዳኞች ተገቢ ያልሆነ ውስኔ በክለቦች ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ከማሳደሩም በተጨማሪ የፉክክሩን ድምቀትም ያደበዝዘዋል።
ችግሩን ለመቅረፍም እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከውዲሁ ብዙ ሥራ መስራት ይጠበቅበታል። የሴቶችን ፕሪሚየር ሊግ ለመመልከት ወደ ስቴዲየም የሚገባው ተመልካች እና ደጋፊ ከዚህ በፊት በነበረው ልምድ አነስተኛ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። ታዲያ በሴቶች እግር ኳስ ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ ሴቶችን መደገፍ እና ማበረታታት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን የደጋፊ እና የተመልካችም ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ይጠይቃል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግን እስካሁን ሦስት ክለቦች ብቻ ናቸው ዋንጫውን ያነሱት። ደደቢት፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዳማ ከተማ ናቸው። ደደቢት ስድስት፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰባት እና አዳማ ከተማ ደግሞ አንድ ጊዜ ዋንጫውን አሳክቷል። ዘንድሮስ ማን ይነግሳል? የሚለውን በውድድር ዓመቱ መጨረሻ የምንመለከተው ይሆናል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here