ግሪን ፋክትስ (www.greenfacts.com) የተሰኘው ድረ ገጽ እንዳስነበበው የዓለማችን የአየር ንብረት መዛባት የሰዎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት እየፈተነው ይገኛል፤ የሕዝብ ቁጥር መጨመር እና ይህንኑ ተከትሎ የሚመጡ ክስተቶች ደግሞ ለአየር ንብረት መዛባት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ የምድራችን የሚበዛው ክፍል ውኃማ እና በደን የተሸፈነ ነው፤ ይሁን እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየው በከፍተኛ መጠን የዓለማችን ሕዝቡ ቁጥር መጨመር ፍላጎቱን ለማሟላት ሲል የደን መመንጠርን አስከትሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የዓለማችን የደን ሽፋን በእጅጉ እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡
“ሚሊኒየም ኢኮሲስተም አሰስመንት” የተሰኘ ድረ ገፅ እንዳስነበበው ደግሞ ከ60 ሺህ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ የዕፅዋት ዝርያዎች የሕልውና አደጋ ተደቅኖባቸዋል። ይህ ደግሞ የዓለማችንን የአየር ንብረት መዛባት እያባባሰው ነው። በመሆኑም “የዕፅዋት ዝርያዎችን መጠበቅ እና መትከል ለምድር ጤናማነት መመለስ መድኃኒት ነው” ብሏል።
በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) እንዳስታወቀው በኢንዱስትሪ እና በእርሻ መስፋፋት ምክንያት በሚደርስ መመንጠር 75 በመቶ የዕፅዋት ዝርያ ጠፍቷል። ከዚህ የከፋ አደጋ ለመውጣት ታዲያ ለደን ልማት ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ በመጠቆም አፋጣኝ የተግባር ሥራን እንደሚጠይቅ ነው ያሳሰበው፡፡
በሌላ በኩል ድርሳናት እንደሚያስረዱት በንጉሣዊያን የአገዛዝ ዘመን የኢትዮጵያው የደን ሽፋን ከ60 በመቶ በላይ ነበር። ይሁን እንጂ ለዘርፉ የተጠናከረ ፖሊሲ እና መመሪያ አለመኖር፣ ትኩረት አለመስጠትም የሀገሪቱ የደን ሽፋን በእጅጉ እንዲያሽቆለቁል አድርጎታል፡፡ ሽፋኑም እስከ 3 በመቶ ወርዶ እንደነበር ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቅርብ ዓመታት በፊት ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የደን ሽፋኑ በማገገም ላይ ይገኛል፤ የግብርና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የሀገሪቱን የደን ሽፋን ወደ 23 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡ ለአብነትም የአረንጓዴ አሻራ በሚል 2011 ዓ.ም ክረምት ላይ ተጀምሮ በመጀመሪያው ምዕራፍ ተከታታይ አራት ዓመታት ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። በሁለተኛው ምዕራፍ ቀጣይ አራት ዓመታት ደግሞ ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ይተከላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀገራችን እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቁጥር ግነት ያለበት እና ለጥራት ትኩረት ያልሰጠ ነው ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ተፈጥሮን የመረዳት እና የተፈጥሮ ፀጋዎቻቸውን የመንከባከብ ልማዳቸው ከፍ ያለ ነው። ለዚህም ስራቸው እማኝ የሚያደርጉት በየዘመናቱ እየዘመነ የመጣውን ሳይንስ ሳይሆን ራሷን ተፈጥሮን ነው። ሳይንስ ተፈጥሮን ስለመንከባከብ ጥቅም ከመዘርዘሩ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጥሮን መጠበቅ እና መንከባከብ እንደ አንድ ሕገ ልቦና ይወሰድ ነበር። በርግጥ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚኖሩ ሕዝቦችም የዚህ ታሪክ ተጋሪዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ገዳማቱን እና አድባራቱን፣ መስጅዳቱን እና የተለያዩ ጥንታዊ የአምልኮ ስፍራዎችን ለጎበኘ ሰው፣ እድሜ ጠገብ ዛፎችን፣ ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ዕፅዋትን እና አዝዕርትን፣ ዓይነተ ብዙ አእዋፋትን እና የዱር እንስሳትን ይመለከታል። የሰው ልጅ ተላምዶ አብሮ ይኖር ዘንድ የሚከብዱ የዱር አውሬዎች በእነዚህ ቦታዎች አደብ ገዝተው ሲኖሩ ሊመለከት ይችላል። ተፈጥሮን መረዳት ከዚህ በላይ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም።
ዘመናዊው ዓለም ባስገኛቸው በርካታ የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶች እና በካይ ጋዞች ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ የከባቢ አየር ብክለት እየተከሰተ መሆኑን ተከትሎ ዓለም በሙቀት መጠን መጨመር እና መሰል የስነ-ምህዳር ቀውስ ፈተና ውስጥ መግባቷን በርካታ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ማሳወቅ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ለዚህ ቀውስ ግንባር ቀደም የመፍትሔ አማራጭ ሆኖ የሚቀመጠው ተፈጥሮን መንከባከብ ነው። ተፈጥሮን ከምንንከባከብበት መንገድ አንዱ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራን ማስቀመጥ ነው።
የአረንጓዴ አሻራ ልማት ባለፉት አምስት ዓመታት በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ያለ ዘመን አይሽሬ ሥራ ነው። የአረንጓዴ አሻራ ጥቅም የአንድ ወገን ወይም የግለሰብ አይደለም። አረንጓዴ አሻራን የማስቀመጥ መርሃ ግብር በጊዜ እና በቦታ የተገደበ የአንድ ሰሞን ተግባር አይደለም።
ዓለም በከፍተኛ የሙቀት መጠን መጨመር እየተፈተነች ነው። በአንዳንድ ሀገራት የሙቀት መጠን ከልክ በላይ በመጨመሩ ምክንያት የዕለት ተዕለት ተግባርን መከወን ይቅርና ወጥቶ ለመግባት እንኳ ሲቸገሩ ታይተዋል። በሙቀቱ መጠን መጨመር የነፍሰጡር እናቶች እና የህፃናት ተጋላጭነት የጎላ ነው። በተለይ በቆላማና በረሃማ ቦታዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የችግሩ ቀዳሚ ገፈት ቀማሾች ናቸው። ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እና የተስተካከለ የአየር ንብረት እንዲኖር ለማድረግ የአረንጓዴ አሻራ ልማትን አጠናክሮ መቀጠል ለነገ የማይባል የመፍትሄ ተግባር ነው። እንደ ዓለም ለተጋረጠው የአየር ንብረት ቀውስ ፈተና ተቀዳሚ መፍትሔ በመሆን የተቀመጠው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ነው።
የአረንጓዴ አሻራ ታሪክ የሚቀመጠው ለሰው ልጅ ቀጣይ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለአዕዋፋቱ እና ለእንስሳቱም ጭምር ነው። የአረንጓዴ አሻራ ልማት የሰው ልጆችን ብቻ ሳይሆን እንስሳትንና አዕዋፋትን የሕልውና ደህንነት ማረጋገጥ እና ማስቀጠል የሚያስችል በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የመምታት ተግባር ነው።
ኢትዮጰያ በርካታ ሀገር በቀል ዛፎች ያሏት ከመሆኑም በላይ የብርቅዬ እንስሳት መገኛም ናት። የእነዚህን ፀጋዎቿን ቀጣይነት ለማረጋገጥ እና ተጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የማይተካ ሚና አለው። ዛሬ እኛ የምንቆርጠው ትናንት የተከሉትን ነው። ዛሬ ካልተከልንስ ነገ ማን የተከለውን እንቆርጣለን? ከከተሞች መስፋፋት እና ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ እየተከሰተ ያለውን ከፍተኛ የፍጆታ ፍላጎት አመጣጥኖ ለማስቀጠል አረንጓዴ አሻራ ወሳኝነት አለው። በአጠቃላይ አረንጓዴ አሻራ ማለት የዓለምን ህልውና ጠብቆ የማስቀጠል ኃይል ያለው ተግባር መሆኑን ልብ ማለት ይገባል።
(ደረጀ ደርበው)
በኲር ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም