የቻይና  – አፍሪካ የንግድ ትስስር

0
42

እ.አ.አ. ከሁለትሺዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ቻይና በአፍሪካ ያላት ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል:: የአህጉሪቱ ትልቁ የንግድ አጋር እና አበዳሪ እንድትሆንም አድርጓታል::

አፍሪካ ወደ ቻይና የምትልከው በዋናነት እንደ ብረት፣ ማዕድናት እና ነዳጅ ያሉ ጥሬ ዕቃዎችን ያጠቃልላል:: ይህም ከጠቅላላው የወጪ ንግድ 60 ከመቶውን ይይዛል:: በሌላ በኩል ቻይና እንደ መሠረተ ልማት እና ቴክኖሎጂ ላሉ ዘርፎች ወሳኝ የሆኑ ምርቶችን፣ ኤሌክትሮኒክስ እና ማሽነሪዎችን ወደ አፍሪካ ትልካለች::

በ2025 እ.አ.አ የመጀመሪያዎቹ ስምንት ወራት ብቻ የቻይና- አፍሪካ ንግድ ትብብር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል:: ቻይና እና አፍሪካ  በዋናነት  ጥሬ ዕቃዎችን ወደ ቻይና በመላክ እና ያለቀላቸውን ምርቶች (ዕቃዎችን) ወደ አፍሪካ በማስገባት ላይ የተመሠረተ  የንግድ ልውውጥ ነው ያላቸው:: ቻይና ለመሰረተ ልማት እና ለኢነርጂ ፕሮጄክቶች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በኩልም የአፍሪካ ትልቋ አበዳሪ ናት:: ይሁንና አህጉሪቱ እየጨመረ በመጣው በቻይና ገበያ እና ዕዳ ላይ ጥገኛ መሆኗ ስጋት ፈጥሯል::

የብሉምበርግ የቻይና የጉምሩክ መረጃ ትንተና እንደሚያመለክተው  በ2025 የመጀመሪያዎቹ ሰባት ወራት ውስጥ ወደ አፍሪካ የገቡ የቻይና ምርቶች 122 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል:: እንዲሁም ከአንድ ወር በኋላ በ2025 የመጀመሪያዎቹ ስምንት ወራት ውስጥ በቻይና እና በአፍሪካ መካከል ያለው የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ ደግሞ 222 ነጥብ ዜሮ አምስት  ቢሊዮን ዶላር መድረስ ችሏል::  ይህም ከ2024 ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የ15 ነጥብ አራት  በመቶ እድገት አሳይቷል::

ሰርጅ አፍሪካ  (surgeafrica.org) ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው  እድገቱ በዋናነት የተቀጣጠለው ከቻይና ወደ አፍሪካ በሚላኩት ምርቶች ላይ ነው:: ይህም  በዓመት ውስጥ 24 ነጥብ ሰባት በመቶ ከፍ እንዲል አድርጎታል:: እንዲሁም  ከአፍሪካ ወደ ቻይና የሚገቡ ምርቶች ደግሞ በሁለት  ነጥብ ሦስት በመቶ ጨምሯል::

ናይጄሪያ  የቻይና ምርቶችን በመግዛት ቀዳሚ ናት።   ከቻይና ወደ አፍሪካ ከሚገቡት ጠቅላላ ምርቶች ውስጥም 11 በመቶውን  ትሸፍናለች:: በመቀጠልም ደቡብ አፍሪካ 10በመቶ፣ ግብፅ ዘጠኝ በመቶ፣ ላይቤሪያ ስምንት በመቶ እና አልጄሪያ ስድስት በመቶ የቻይና ምርትን በመግዛት  በቅደም ተከተል ይጠቀሳሉ::

ቻይና ወደ አፍሪካ የምትልካቸው ምርቶች መጨመር በዋናነት የተቀጣጠለው በአህጉሪቱ የግንባታ ማሽነሪዎች፣ ተሸከርካሪዎች እና የብረታ ብረት ከፍተኛ ፍላጎት በመኖሩ ነው:: የ“ሶላር ፓነሎች” (የፀሐይ ብርሃንን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚቀይሩ መሳሪያዎች) የትእዛዝ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር፤ የቻይናን ወደ አህጉሪቱ የሚላኩ ምርቶች ዋጋ ከፍ እንዲል አስችሏል::  በ 12 ወራት ውስጥ (እስከ ሰኔ 2025) ወደ አፍሪካ የገቡ የቻይና ሶላር ፓነሎች  በ 60በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል:: ምንም እንኳን አፍሪካ ከቻይና አጠቃላይ የወጪ ንግድ ስድስት በመቶውን ብቻ የምትወክል ቢሆንም  ከቻይና ወደ አህጉሪቱ የሚላኩ ምርቶች ዋጋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እድገት አሳይተዋል::

የዘርፉ ተቺዎች ግን ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት የተዛባ እንደሆነ እና   አህጉሪቱ ከቻይና ጋር ከፍተኛ የንግድ ጉድለት ሊያጋጥማት እንደሚችል  ስጋታቸውን ይገልጻሉ:: እ.አ.አ. በ 2024 አፍሪካ ለቻይና ምርቶች 178 ነጥብ 76 ቢሊዮን ዶላር አውጥታለች። ወደ ቻይና ከምትልካቸው ምርቶች ደግሞ 116 ነጠብ 79 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች:: ይህም የ61 ነጠብ 93 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ጉድለት መታየቱን አመላክቷል::

የአፍሪካ የፖሊሲ ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፒተር ካግዋንጃ ይህንን የንግድ ጉድለት ማጥበብ በአፍሪካ በኩል መዋቅራዊ ማስተካከያዎችን እንደሚጠይቅ ለአፍሪካ ቢዝነስ ተናግረዋል:: “አፍሪካ እንደ ኤሌክትሮኒክስ እና ማሽነሪዎች ከቻይና እስካስገባች እና ብዙ ዋጋ የማይጠይቁ ጥሬ እቃዎችን ለቻይና አቅራቢ እስከሆነች ድረስ ይህ ጉድለት እየሰፋ ይሄዳል” ይላሉ::

ሰኔ 2025 ላይ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ከቤጂንግ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለሚያደርጉ የ53 የአፍሪካ ሀገራት በሙሉ ከቀረጥ ነጻ የሆነ የንግድ ስርዓት  እንደምትዘረጋላቸው ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው። ቻይና እንደ ተገንጣይ ግዛቷ ለምትመለከታት ለታይዋን ባላት ዲፕሎማሲያዊ እውቅና ምክንያት ኢስዋቲኒ ከዚህ ስምምነት የተገለለች ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር ሆናለች::

“ቻይና ከ53 የአፍሪካ ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ የዋጋ ታሪፍ ለማንሳት መወሰኗም በረጅም ጊዜ ንግድን ለማመጣጠን ትልቅ እርምጃ ነው:: ነገር ግን አፍሪካ-ከቻይና ዜሮ ታሪፍ ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ለማግኘት የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ማፋጠን እና እሴት መጨመርን ማሳደግ አለባት” ሲሉ የአፍሪካ የፖሊሲ ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ያስገነዝባሉ::

ይህ በእንዲህ እያለ እ.አ.አ. በ 2013 የቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ (BRI) ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአፍሪካ ውስጥ 53 የአፍሪካ ሀገራትን በተለያየ ደረጃ በማሳተፍ  ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል:: በዚህ ኢንሼቲቭ እ.አ.አ. በ2023 የአፍሪካ ሀገራት በወደቦች፣ በባቡር ሀዲዶች እና በታዳሽ ኃይል ላይ ኢንቨስትመንቶችን ያካተተ 21 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ስምምነቶችን ከቻይና ጋር አድርገዋል::

ቻይና በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ (BRI) ዘላቂ እና ዝቅተኛ ስጋት ያላቸው ፕሮጀክቶችን ስታንቀሳቅስ፤ አፍሪካ ከፍተኛ ተጠቃሚ ትሆናለች:: ይሁን እንጂ የአፍሪካ ሀገራት እነዚህን ጥቅሞች ከራሳቸው ስትራቴጂካዊ ግቦች ጋር ለማጣጣም እና የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭን  አስተዳደር ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው የሚገለጸው::

በሌላ በኩል ሁልጊዜ በመስከረም ወር የሚካሄደው የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም (FOCAC) ቻይና በአፍሪካ ላይ የበለጠ ተጽዕኖ እንድታሳድር እድል ይሰጣል:: የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም በቻይና እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ትብብርን ለማጠናከር የተፈጠረ የአጋርነት መድረክ ነው:: አላማው የኢኮኖሚ ልማትን፣ ንግድን እና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ነው:: ፎካክ ከኤስዋቲኒ በስተቀር 53 የአፍሪካ ሀገራትን አባል አድርጎ ያቀፈ ሲሆን በአህጉሪቱ ትብብርን እና ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማረጋገጥ በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ይደገፋል:: ቻይና የፋይናንስ፣ መሠረተ ልማት እና ንግድ ላይ በማተኮር የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ  ትብብርን ለማስፋት የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም  ለመጠቀም አቅዳለች::

ይህ በእንዲህ እያለ ኢትዮጵያ እና ቻይና በጄኔቫ በሚገኘው የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት የሁለትዮሽ ገበያ ተደራሽነት ፕሮቶኮል በይፋ የተፈራረሙት በቅርቡ ነው:: ይህም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ለምታደርገው ሂደት ትልቅ እርምጃን ይወክላል ነው የተባለው::

ኢን ሳይትስ ሜድኢን ቻይና   (insights.made-in-china.com) ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እ.አ.አ ኅዳር 24 ቀን 1970 ነው:: ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ያለማቋረጥ እያደገ በመምጣቱ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸው የንግድ ግንኑኙነት ወደ አጠቃላይ አጋርነት ተቀይሯል:: እ.አ.አ. በጥቅምት 2023 ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት አሻሽለዋል:: ይህም  የትብብራቸውን ጥንካሬ እና ዘላቂነት አጉልቶ ያሳያል::

በቻይና እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የኢኮኖሚ እና የቴክኒክ ትብብር የተጀመረው ደግሞ እ.አ.አ. በ1971 መጀመሪያ ላይ ሲሆን በበርካታ የሁለትዮሽ የንግድና ልማት ስምምነቶች የተደገፈ ነው:: ቻይና ባለፉት ዓመታት በመላው ኢትዮጵያ እንደ አውራ ጎዳናዎች፣ የባቡር ሀዲዶች፣ የኃይል ማመንጫዎች፣ የእንስሳት ሕክምና ክሊኒኮች እና የውኃ አቅርቦት ኔትወርኮች ያሉ በርካታ ዋና ዋና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ገንብታለች:: በአሁኑ ጊዜ ሁለቱ ሀገራት በንግድ እና በኢንቨስትመንትም ጠንካራ ግንኙነት ፈጥረዋል::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የህዳር  8  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here