የቻይና ጉዞ

0
117

የቻይና ታሪክ በመንግሥታት (Dynasties) ይከፈላል:: ከመጀመሪያዎቹ የታወቁት መንግሥታት ሻንግ (Shang) እና ዞው (Zhou) ናቸው:: በእነዚህ ዘመናት የሥነ ጽሑፍ ሥርዓት፣ የግብርና ልማት እና የፍልስፍና መሠረቶች ዳብረዋል:: በተለይ ኮንፊሺየስ (Confucius) ያቀረበው ፍልስፍና በቻይና ማሕበረሰብ ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል:: ኮንፊሺየስነት ሥነ-ምግባርን፣ ታዛዥነትን፣ ሥርዓት እና ለመንግሥት ታማኝነትን ያበረከተ ነው::

የኢምፔሪያል (Imperial) ዘመን፡-

ቻይና በኢምፔሪያል ዘመን በጣም ኃያል መንግሥት ነበረች:: የቺን (Qin) መንግሥት ቻይናን ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ሀገር ያደረጋት ነው:: የታዋቂው የቻይና ታላቁ ግድግዳ (Great Wall) በዚህ ዘመን ነበር መገንባት የተጀመረው::

ሐን (Han Dynasty 206 BC – 220 AD)

የቻይና ከፍተኛው የልማት ዘመን ነበር:: በዚህ ዘመን ነበር ሲልክ ሮድን (Silk Road) ለዓለም ያበረከተችው:: ይህም ቻይናን ከእስያ፣ አፍሪካ እና አውሮፓ ጋር በንግድ አገናኝቷል:: በታንግ (Tang) እና ሶንግ (Song) ዘመናትም ሥነ-ጥበብ፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በጣም ተሻሽለዋል::

የዘመናዊ ታሪክ (19ኛው እና 20ኛው ክፍለ ዘመን)፡-

ለቻይና 19ኛው ክፍለ ዘመን  ከባድ ጊዜ ነበር:: የኦፒየም ጦርነቶች (እንግሊዞች ከህንድ ቅኝ ግዛቶቻቸው በቻይና ወደቦች ከቻይና መንግሥት ፍላጎት ውጭ በድብቅ ኦፒየም ያስገቡ ነበር)እና የአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ጫና ቻይናን እንዳዳከሟት ዘኮንቨርሴሽን ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያትታል::

ሌላው እ.አ.አ ከ1850 እስከ 1864 “የቴይፒንግ” አመፅ ተካሂዶባታል:: ይህም በሀገሪቱ የተካሄደ ታላቅ የማኅበረሰብ አመፅ ነበር:: በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ  ሕይወቱን አጥቷል:: ከዚያም እ.አ.አ ከ1894 እስከ 1895 የቻይና-ጃፓን ጦርነት ተካሄደ::  በመቀጠልም እ.አ.አ በ1900  የቦክሰር አመፅም ሀገሪቱን የፈተነበት ጊዜ ነበር:: በ1921 ደግሞ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ማኦዞ ዚዶንግ (Mao Zedong)  ተመሠረተ:: እ.አ.አ ከ1937 እስከ 1945 ቻይና በጃፓን ወረራ (በ2ኛው የዓለም ጦርነት) ተፈጽሞባታል::

ቻይና እ.አ.አ ከ1949 በፊት ዓለም ላይ ከሚገኙ በጣም ድሀ ሀገራት መካከል ትመደብ ነበር:: እስከ 90 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧም አርሶ አደር ነበር:: ይሁን እንጂ መሬት በጥቂት ባላባቶች እጅ ነበር:: ረሀብ፣ በሽታ እና ጦርነት በተደጋጋሚ ደርሶባታል:: አብዛኛው የቻይና ሕዝብ የዕለት ጉርስ ብቻ ነበር ማግኘት የሚችለው::

ጦርነት እና ውስጣዊ አመጽ በእጅጉ የጎዳት ቻይና በ1949 መጨረሻ አካባቢ የነበረው የአንድ ቻይናዊ ግለሰብ አማካይ የሀብት መጠን ከአብዛኞቹ የአሁኑ የአፍሪካ ሀገራት በታች ነበር:: የዜጎች የዕድሜ ጣሪያም ሠላሳ ስድስት ዓመት ብቻ ሲሆን ማንበብ እና መጻፍ የሚችሉ ሕዝቦቿም ከሃያ በመቶ አይበልጡም ነበር::

ቻይና እ.አ.አ ከ1949 እስከ 1978 ሶሻሊዝም እና የእኩልነት ፖሊሲ ነበራት:: የኮሙኒስት ፓርቲ ኃይሉን ካጣ በኋላ መሬት ከባለመሬቶች ተወስዶ ለአርሶ አደሮች ተከፋፍሏል:: መሠረታዊ ጤና እና ትምህርትም ለሁሉ እንዲዳረስ ተደርጓል:: ይህ እጅግ ጠቃሚ ነበር፤ ይሁንና ዜጎች እኩል ቢሆኑም ድሆች ነበሩ::

ይህ በእንዲህ እንዳለ እ.አ.አ በ1978 የዴንግ ዚያኦፒንግ ዐቢዮት ከተካሄደ በኋላ የሀገሪቱ ታሪክ ተለወጠ:: በዚህ ጊዜም “እኩልነት ብቻ አይበቃም፤ ሰዎች በመጀመሪያ ባለጠግነትን ማግኘት አለባቸው” የሚል ፖሊሲ ይዞ ብቅ አለ::

ከዚያስ ቻይና ምን አደረገች?

እ.አ.አ በ1978 ዴንግ ዚያኦፒንግ “ማሻሻያና መክፈቻ” የተሰኘውን አዳዲስ ስትራቴጂ ነገሮችን ሁሉ ቀይሯል:: አዲሱ ስትራቴጂ ግብርናን በቤተሰብ ኃላፊነት ሥርዓት በመተካትና በማዘመን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን በአጭር ጊዜ ከረሃብ አዙሪት አውጥቷል:: መሠረተ ልማትን በቁርጠኝነት ማስፋፋቷ እና ለሰው ኃይል ቅድሚያ መስጠቷ ለስኬት አብቅቷታል:: በየዓመቱም ከስምንት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ በምሕንድስና እና በሒሳብ ተማሪዎችን በማስመረቅ የሰው ሀብቷን አሳድጋለች::

ቻይና የንግድና የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴዋን በከፍተኛ ፍጥነት እንዲቀላጠፍ ለማድረግ ከአርባ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የፈጣን ባቡር መንገዶችንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ የሚባሉ ወደቦችን ገንብታለች:: በተጨማሪም ትናንሽ የዓሣ አጥማጅ መንደሮችን በአራት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ ወደ ግዙፍ የቴክኖሎጂና የፋይናንስ ከተማነት የቀየሩ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን መፍጠር አስችሏታል::

የቻይና የድህነት ታሪክ ሊቀየር የቻለው ዴንግ ዚያኦፒንግ  ለተግባራዊነትና ለውጤት ቅድሚያ በመስጠት ቻይናን ለውጭ ኢንቨስትመንትና ለዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር ክፍት በማድረጉ ጭምር ነው::

አርሶ አደሮች ምርታቸውን መሸጥ ተፈቀደላቸው:: የግል ንግድ ተጀመረ፤ የውጭ ኩባንያዎችም ወደ ሀገሪቱ መግባት በመጀመራቸው ኢንዱስትሪው ፈጣን ዕድገት አስመዘገበ:: ይህም ሰዎችን ከአርሶ አደርነት ወደ ከተማ በማምጣት በፋብሪካዎች እንዲሰማሩ አድርጓል::

ከዚያም ከ1980 አስከ 2010(እ.አ.አ) ድረስ ድህነትን በፍጥነት መቀነስ የሚል ዓለማ በመያዝ ተንቀሳቅሳለች:: የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ቻይና ድህነትን ከሀገሪቱ መንቅራ ለማጥፋት ዕቅድ የነደፈችው በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር ከ2013 እስከ 2021 ባለው ጊዜ ነበር:: እ.አ.አ በ2013 አካባቢ የተጀመረው የቻይና የድህነት ቅነሳ (TPA) ፕሮግራም በ2020 ድህነትን ለማጥፋት በእጅጉ ረድቷል::

እንደ የዓለም ባንክ መረጃ ቻይና በ40 ዓመት ውስጥ 800 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ከድህነት ማውጣት ችላለች:: ይህ በዓለም ታሪክ ትልቁ የድህነት ቅነሳ ነው:: ሥራ ፈጠራ፣ ገቢ የሚያመጡ ፋብሪካዎችን ማስፋፋት፣ በርካታ ወጣቶችን ከገጠር ወደ ከተማ እንዲገቡ በማድረግ በፋብሪካዎች እና በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች በማሰማራት ውጤት አስመዝግባለች::

እ.አ.አ በ2021 ነበር የቻይና መንግሥት “ከአስከፊ ድህነት ወጥተናል” በማለት ለዓለም ሕዝብ ይፋ ያደረገው:: ይሁንና ቻይና ድህነትን ቀነሰች እንጂ ፍትሃዊነትን አልፈጠረችም የሚሉ አሉ:: ቻይና ድህነትን ያሸነፈችው በጠንካራ መንግሥት፣ ገበያ መር ኢኮኖሚ እና ሶሻሊዝምን በመቀላቀሏ፣ ሥራ ፈጠራ ላይ ትኩረት በመስጠቷ እና ኢንዱስትሪ በማስፋፋቷ ነው::

ቻይና በረጅም ጊዜ ዕቅድ እና ቀጣይነት ባለው ፖሊሲ መመራቷ ለስኬት አብቅቷታል:: በብዛት  የሰው ኃይልን የምትጠቀመው ቻይና በቴክኒክ ትምህርት እና የፋብሪካ ስልጠናዎች ላይ ትኩረት አድርጋለች:: ቻይና “ድህነት በፖለቲካ ሳይሆን በሥራ ይፈታል” የሚል አባባልን ታራምዳለች::

ቢቢሲ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ቻይና በተለያየ ጊዜ በነበራት ወታደራዊ ትርዒት ላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን በፍጥነት ማምረት እንደምትችል አሳይታለች:: በተለያዩ ጊዜያት ባደረገቻቸው ወታደራዊ ትዕይንቶችም ቻይና የኒውክሌር ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ጨምሮ አዳዲስ የጦር መሣሪያዎችን ይፋ አድርጋለች::

ይሁንና ቴክኖሎጂዎች የአሜሪካ የላቁ መሣሪያዎች ቅጂ እንደነበሩ በሲንጋፖር ናንያንግ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመከላከያ ፕሮግራሞች ልማት ረዳት ፕሮፌሰር ሚካኤል ራስካ ለቢቢሲ ተናግረዋል::

በተለይም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን በማምረት ረገድ የመከላከያ ኢንዱስትሪዋ ምን ያህል የላቀ ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚያሳይ ነው:: አንዳንዶች ይህ ለአሜሪካ እና ለአጋሮቿ ግልፅ መልዕክት ነው ሲሉ ይናገራሉ:: ቻይና በየጊዜው ከሌሎች ሀገራት ጋር እና በተናጠል በተለያዩ ጊዚያቶች የምታደርጋቸው ወታደራዊ ትርዒቶች ቻይና በቴክኖሎጂ ከአሜሪካ ጋር ተገዳዳሪ እንደሆነች አመላካች ነው::

ቻይና ዛሬ ሠላሳ በመቶ የሚሆነውን የዓለም አጠቃላይ ማኑፋክቸሪንግ ድርሻ ትይዛለች:: ከሃያ በላይ ትላልቅ ከተሞችንና በዓለም ረጅሙን የፈጣን ባቡር መረብ ባለቤት ለመሆንም በቅታለች:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአሜሪካ ጋር ያላት የንግድ ትስስር ውዝግብ የበዛበት ቢሆንም  የዓለም ሁለተኛዋ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት ከመሆን አላገዳትም::

በዓለም ላይ ያላት ተጽዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረም ይገኛል:: በተለይም  ቻይና በአፍሪካ፣ በእስያ እና በላቲን አሜሪካ ከፍተኛ ተጽዕኖ የምታሳድር ሀገር ሆናለች:: በቤልት ኤንድ ሮድ “Belt and Road Initiative” አማካኝነት መንገዶች፣ ባቡሮች፣ ወደቦች በብዙ ሀገሮች ገንብታለች:: ቻይና አፍሪካ ውስጥ በኢኮኖሚ እና በኢንፍራስትራክቸር ልማት ትልቅ ሚና ትጫወታለች::  ብዙዎች የቻይና ታሪኳ፣ ፖሊሲዎችዋ እና ኢኮኖሚዋ የዓለምን አቅጣጫ በግልጽ ሁኔታ እንደሚቀይሩ ይገመታሉ:: ወደፊትም ቻይና በዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና እንደምትጫወት ይጠብቃሉ::

ከችግር፣ ከርሀብ እና ጦርነት የተላቀቀችው ቻይና የዓለም ባንክ እ.አ.አ2022 ይፋ ባደረገው መረጃው በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖረው የዜጎቿ መጠን ከ88 በመቶ ወደ አንድ በመቶ ዝቅ ብሏል:: የዜጎች የዕድሜ ጣርያ ወደ ሰባ ዘጠኝ ዓመት ከፍ ብሏል:: ዘጠና ሰባት በመቶ የሚደርሰው ሕዝቧም ማንበብ እና መጻፍ የሚችል ሆኗል::

ዐሥራ ስምንት በመቶ የነበረው ከተሜነት ወደ ስልሳ አምስት በመቶ አድጓል:: በአሁኑ ጊዜ ቻይና በአንድ ፓርቲ ስርዓት የምትመራ ሀገር ስትሆን ፓርቲው በመንግሥት፣ በወታደራዊ መዋቅሮች እና በኢኮኖሚ ላይ ሙሉ ቁጥጥር አለው:: የቻይና ፖሊሲ በውስጥ ጉዳይ ላይ መረጋጋትን እና እድገትን ሲያበረታታ በውጭ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብነትን የሚከለክል (Non-interference) መርህን ይከተላል::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥር 11  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here