የችግሩ መውጫ መንገድ ምን ይሆን?

0
226

ስማቸውን ለመናገር ያልፈቀዱ የባሕር ዳር
ከተማ ነዋሪ እና በጎልማሳነት ዕድሜ የሚገኙ
ናቸው። በመንግሥት ሥራ ተቀጥረው ኑሮን
እንደሚመሩ የነገሩን ነዋሪው፣ በአሁኑ ወቅት
ሀገራችን ለገጠማት ችግር መውጫው ምን ይሆን
ስንል ሐሳባቸውን እንዲያካፍሉን ጠይቀናቸዋል።
እርሳቸውም ቁምነገር አዘል አባባልን መነሻ
አድርገው ሐሳባቸውን ጀመሩልን።
“ጠዋት ስንሄድ ያነቀፈን ድንጋይ ስንመለስ
እንዲያነቅፈን መፍቀድ አይገባም። ምክንያት
ከተባለም ከመጀመሪያው ስህተት መማር
አለብንና ነው” በማለት።
ነዋሪው እንዳሉት በሀገራችን በተለይ
በክልላችን የገጠመን ችግር ምክንያቱ ተመሳሳይ
ነው። ይሁን እንጂ ችግሮቹን የምንይዝበትና
ምላሽ የምንሰጥበት መንገድ ችግሮቹን የሚፈውስ
አይደለም። ይባስ ተብሎም ችግሮችን ለማስታገስ
ሙከራ የሚጀምረው ከፍተኛ ውድመትን
ካስከተለ በኋላ ነው። ለዚህም ከፍተኛ ሰብአዊ
እና ቁሳዊ ውድመት ያደረሰውን የሰሜኑን ጦርነት
አንስተዋል።
የሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት ካደረሰ
ማግሥት በድርድር መቆሙ ይታወሳል። እናም
እርሳቸው እንዳሉት፡- “ከዚህ አውዳሚ ጦርነት
ትምህርት ሳይወሰድ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ
መገኘታችን እጅግ አሳዛኝ ነው። የኋላ ኋላ ችግሩ
በውይይት መፈታቱ ላይቀር የሰው ሕይወት
እስኪጠፋ መጠበቅ አልነበረብንም” ብለዋል።
በመሆኑም አሁንም ቆም ብሎ በማሰብ ሁሉን
አካታች ውይይት በማድረግ ችግሩን መፍታት
እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሌላው ሐሳባቸውን ያካፈሉን የጎንደር
ከተማ ነዋሪዋ እና የትራንስፖርት አገልግሎት
በማጣታቸው ባሕር ዳር ከተማ ያገኘናቸው ነዋሪ
ላቂያ ዓለሜነህ ከላይ የሰፈረውን ሐሳብ ይጋራሉ።
ነዋሪዋ እንዳሉት ከቀናት በፊት በግል ጉዳይ
ወደ ባሕር ዳር ከተማ መጥተዋል። ይሁን እንጂ
የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡ በፈለጉት
ቀን ወደ ቤተሰባቸው መመለስ አልቻሉም።
“በተፈለገው ጊዜ አለመመለሴ ለልጆቼ ጭንቀት
ፈጥሮብኛል። ከዚህ በከፋም በተለያዩ ቦታዎች
ብዙዎች ሕይወታቸውን እያጡ ነው። ከባድ
ችግር ውስጥ ነን” ብለዋል።
ያለፈው ችግር ከበቂ በላይ ተሞክሮን
የሚሰጥ መሆኑን በማንሳትም ሰላም እንዲሰፍን
ጠይቀዋል። ለዚህ ደግሞ የሚመለከተው ሁሉ
(ለሰላም መስፈን የማይመለከተው የለም)
የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።
በመጨረሻም “ሀገራችንን ከነ ሙሉ ክብሯ
ጠብቀው ያስረከቡን ዘር ቀለም ሳይቆጥሩ
ነው። አጥንታቸው ሊወጋን ይገባል። ከታሪክ
ተወቃሽነት መዳን አለብን” በማለት ነው
መልዕክት ያስተላለፉት።
ሀገራችን ሰላም ከራቃት ዓመታት
ተቆጥረዋል። በዚህም ከምትክ የለሹ ሰብዓዊ
ውድመት ባሻገር ዜጎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ
አልቻሉም። ለዘመናት የተዘራው ብሔር ተኮር
መርዝ ፍሬ አፍርቶ ኢትዮጵያዊነት ኮስሶ ሁሉም
በየብሔሩ እንዲታጠር ሆኗል። በአማራ ክልልም
ችግሩ ሰፍቶ ክልሉን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጂ
እንዲተዳደር አስገድዷል።
አዋጁ ከመታወጁ ቀደም ብሎ የክልሉ
ምክር ቤት አባላት ሁሉም ወገኖች ወደ ውይይት
እንዲመጡ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። የምክር ቤት
አባላትም የችግሩን አሳሳቢነት በማለባበስ ማለፍ
እየከፋ እንዲሄድ እንደሚያደርገው ጠቁመው
ነበር። የችግሩ ዋና መንስኤ ምላሽ ያላገኙ
የሕዝብ ጥያቄዎች ተከማችተው የፈጠሩት ብሶት
መሆኑንም መናገራቸው ይታወቃል።
በኢትዮጵያ ጉዳይ (በዋናነት በሰሜኑ ጦርነት
ምክንያት) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት
የፀጥታው ምክር ቤት ከ11 ጊዜ በላይ መሰብሰቡ
ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚታየው
ግጭት በውይይት እንዲፈታ የተለያዩ ሀገራትና
የችግሩ መውጫ መንገድ ምን ይሆን?

ተቋማት ጥሪ አድርገዋል። ለአብነትም አሜሪካ
ጉዳዩ እንደሚያሳስባት አስታውቃለች። ግጭቱም
በፖለቲካዊና በሰላማዊ ውይይት እንዲፈታ
አሳስባለች።
የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
የውጪ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ
ኮሚቴ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከሰሞኑ
ተወያይቷል። ኢትዮጵያ በከፋ ችግርና የደህንነት
ስጋት ውስጥ እንደምትገኝም ገልጿል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክዕክተኛ
ማይክ ሐመር በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰውን
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከኢትዮጵያ መንግሥት
ጋር ሲያደራድሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤
በአማራ ክልልም ዕድሉ ከተሰጠ ሰላማዊ ንግግር
እንዲደረግ ድጋፍ ለማድረግ አሜሪካ ዝግጁ
መሆኗን አስታውቀዋል።
ልዩ መልዕክተኛው አክለውም እየተካሄደ
ያለውን ግጭት ለማስቆም ወታደራዊ እርምጃ
መፍትሔ እንደማይሆን እና መንግሥት
ልዩነቶቹን በንግግር እንዲፈታ አሜሪካ ግልጽ
አቋሟን ለኢትዮጵያ መንግሥት ማስታወቋን
ተናግረዋል።
አያይዘውም በሀገሪቱ በሚታየው የሰብአዊ
መብት አያያዝ ደስተኛ እንዳልሆኑና ሁኔታዎች
እንዲሻሻሉ በተደጋጋሚ መናገራቸውን ገልፀዋል::
የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ያስቆመው
የሰላም ስምምነት መፈረሙ ትልቅ ስኬት ነው
ያሉት ማይክ ሐመር፤ በአማራ እና በኦሮሚያ
ክልሎች ያለውን ግጭት ለማስቆም ንግግር እና
ድርድር እንዲደረግ ጫና እያሳደሩ መሆኑን
ተናግረዋል።
ከተባባሰ ወራት ያሰቆጠረውን በአማራ ክልል
እየተካሄደ የለውን ግጭትም ለማስቆም “ዕድሉ
ካለ ለማደራደር እና ሰላማዊ ንግግር እንዲደረግ
ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን” ያሉት ማይክ ሐመር
ግጭቶቹ በወታደራዊ እርምጃ እልባት ሊያገኙ
እንደማይችሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አክለውም ከወራት በፊት በፌደራሉ
መንግሥት በአማራ ክልል ላይ ተጥሎ
የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ
እና መገናኛ ብዙኃን ወደ ክልሉ እንዲደርሱ
ጠይቀዋል። ተቋርጦ የሚገኘው የኢንተርኔት
አገልግሎት እንዲጀመር የኢትዮጵያ መንግሥትን
መጠየቃቸውንም ተናግረዋል።

“በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች
የሚፈጸሙት ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች፣
ስቃዮች እና እስሮች በእጅጉ አሳስበውናል”
ብለዋል። በሀገሪቱ ባለው የሰብዓዊ መብት
አያያዝም ደስተኛ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።
ፐሮፌሰር ገብሩ ታረቀ የታሪክ ምሁር
እና የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ተንታኝ
ናቸው። ኢትዮጵያን በተመለከተ ሁለት የታሪክ

መጻሕፍትንም (Ethiopia: Power & Pro-
test and The Ethiopian Revolution)

አበርክተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ምሁሩ
ወቅታዊውን የሀገራችንን ጉዳይ በተመለከተ
ከበኲር ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ምሁሩ እንዳሉት የአፍሪካ ቀንድ ውጥንቅጡ
የወጣ፣ ግጭት ርቆት የማያውቅ አካባቢ ነው።
ለዚህ ደግሞ ድህነትና ኋላቀርነት መሠረታዊ
ምክንያቶች መሆናቸውን ይዘረዝራሉ።
በተመሳሳይ የሕዝቡ ቁጥር በከፍተኛ መጠን
መጨመር እና ያለው ሀብት አለመጣጣሙን
ያነሳሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘም የአፍሪካ መሪዎች
ስልጣንን የዕድሜ ልክ ስጦታ አድርጎ መመልከት
እና መበልፀጊያ ማድረግ መገለጫቸው መሆኑን
እንደማሳያም ያነሳሉ።
ፐሮፌሰር ገብሩ እንዳብራሩት በተለይ
ኋላቀርነት በብሔሮች መካከል፣ በወሰን አካባቢ
ግጭትን፣ ጎጠኝነትን ያስከትላል። በአሁኑ ወቅት
በሀገራችን የሚታየው የሰላም እጦትም ከዚህ ጋር
የተገናኘ ነው።
የዘመናዊት ኢትዮጵያ መሠረት የተጣለው
በአፄ ምኒልክ ዘመን መሆኑን የታሪክ ምሁሩ
ያነሳሉ። ከ1966 ዓ.ም ዐቢዮት ጀምሮ ግን ብሔር
ተኮር ችግር እየሰፋ ሄዶ “አሁንም ድረስ በችግር
እንማቅቃለን። ሰላማዊዉ ሕዝብ እየተጎዳ
እናያለን” ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም በንጽጽር
የተወሰኑ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ብቻ
ሰላም የሰፈነባቸው መሆኑን በማንሳት አማራ፣
አሮሚያ፣ ትግራይ፣ … ክልሎች ሰላም የራቃቸው
መሆኑን ዘርዝረዋል።
በሀገራችን እንደ ሀገርም እንደ ክልልም በቁጥር
ደረጃ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይገኛሉ።
ሁሉም ደግሞ የሕዝብን ፍላጎት ከመረዳት ይልቅ
የስልጣን ሽኩቻ የተጠናወታቸው ናቸው። ከዚህ
አልፎም በመከፋፈል፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር
በማጣላት የተጠመዱ ናቸው። በዚህ ምክንያት

በአንድነቱ እና ተከባብሮ በመኖር የሚታወቀውን
ሕዝባችንን “እንዲዳማ፣ ወደ ባሰ ድህነት እንዲገባ
አድርገውታል” ሲሉ ነው የሀገራችን የከፋ ችግር
የፖለቲከኞች ውጤት መሆኑን ያብራሩት።
ለዚህ አብነትም በታሪክ ተመራማሪነታቸው
ካገኙት ዕውቀት ባሻገር በዕድሜ ዘመናቸው
የታዘቡት (ምሁሩ 80 ዓመትን የተሻገሩ የዕድሜ
ባለፀጋ መሆናቸውንም ልብ ይሏል) መሆኑን
ጠቁመዋል።
“በኢትዮጵያዊያን መካከል በማንነት፣
በቋንቋ፣ … ምክንያት ግጭት የተከሰተበትን
ዘመን አላውቅም። በአማራ እና በትግሬ ጦርነት
የተካሄደበትን ዘመን አላውቅም። በአሁኑ ወቅት
የሚታየው ሁሉ አዲስ ፈጠራ ነው። ይህ ሁሉ
የሚሆነው በግለሰቦች ወይም በፈጠሯቸው
የፖለቲካ ድርጅቶች ነው” ብለዋል።
በእልኸኝነት የሚቀና ሀገር የለም የሚሉት
ፕሮፌሰር ገብሩ በተለይ ፖለቲከኞች ከራስ በላይ
ሀገር እና ከሕዝብ መሆኑን ተረድተው፣ የሕዝብን
ደህንነት እና ዕድገት አስቀድመው መሥራት
እንዳለባቸው አስረድተዋል።
በሀገራችን ለሚታየው የሰላም እጦት
መፍትሔ ለመስጠት የውይይት በሮች ክፍት
መሆናቸውን መንግሥት በተደጋጋሚ ይናገራል።
ይሁን እንጂ ከቃሉ ባለፈ ተግባር የራቀው
መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለአብነትም ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ የተደረጉት
ድርድሮች ግልጽነት የጎደላቸው እንደነበሩ
ይነሳል። ድርድሮቹም የተጨበጠ ውጤት
ሳያስገኙ ተደራዳሪዎች ተበትነዋል።
ድርድሮች ለምን ይከሽፋሉ ስንል ለፕሮፌሰር
ገብሬ ጥያቄ አንስተንላቸዋል። እርሳቸውም
“የመክሸፉ ምክንያት አንድ እና ሁለት የለውም።
ሁሉም ስልጣን ፈላጊዎች ናቸው። ከስልጣን በላይ
ሀገር፣ ሕዝብ እንዳለ የዘነጉ ናቸው” ሲሉ ነው
ምክንያታቸውን ያስረዱት። ከችግሩ ለመውጣት
እና ውጤት ለማስመዝገብ ታዲያ ሁሉም አካላት
የሕዝብን ፍላጎት መረዳትና ማክበር፣ ከራስ
በላይ ለሀገር መቆም፣ ወደ አንድነት መምጣት
እንደሚገባ ሙያዊ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here