የችግሩ መውጫ የራስ ጽናት ብቻ ነው

0
239

በኲር ጋዜጣ በማህበራዊ እና በወጣቶች  አምዶቻችን  ከሱስ ስላገገሙ ወጣቶች ማስነበባችን ይታወሳል። በመጋቢት 2/2016 ዓ.ም በወጣው ጽሑፍ ከሱስ ካገገመ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ወጣት እናት እንደሚሉት  ልጃቸው ከሱስ ማገገሚያ ከወጣ በኋላ ከእርሳቸው በቀር ከድሮ ጓደኞቹ ርቆ ብቸኝነትን መምረጥ፣   ድብርት እና  ከሱስ ለመውጣት ያሳለፈው አሰቃቂ ጊዜ ተመልሶ እንዳይመጣ መፍራት ካስተዋሏቸው ችግሮች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው::

ሌላው ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዘ ለበኲር ጋዜጣ  ስሜ እንዳይጠቀስ ሲል አስተያየቱን የሰጠን ባለታሪካችንም በአሁኑ ወቅት ከሱስ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከወጣ ከሁለት ዓመት በላይ እንዳስቆጠረ ነግሮናል:: ከዚህ እስኪደርስ  ትልቁ ፈተና የነበረው ሰዓቱን ጠብቆ የሚከሰት ከፍተኛ ድብርት እና ቀድሞ ከነበሩት ጓደኞቹ ጋር አብሮ ከመቀጠል ይልቅ የብቸኝነት ስሜት  ከፍተኛ ፈተና እንደ ነበር ያነሳል::

ወጣቱ እንደሚለው በብቸኝነት ያለፈን መጥፎ ጊዜ  በማስታወስ ራስን መውቀስ  ከሱስ ከወጣ በኋላ ያጋጠመው ሌላ ፈተና ነው:: “መዋያ ራሱ ይቸግራል” ያለው ባለታሪካችን፤  ከፍተኛ ውጥረት፣ ምክንያት የሌለው ጭንቀት፣ የባዶነት ስሜት፣ “ምንም የማልጠቅም ሰው ነኝ” ብሎ  ማሰብ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ “የሚረዳኝ ሰው የለም ብሎ ማሰብ”፣ ከባድ ድካም እና አቅም ማጣት፣  በግል ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማጣት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና ድባቴ የረጅም ጊዜ ፈተና ሆኖበት እንደ ነበር ዛሬ ላይ ያስታውሳል::

እኛም ባለታሪኮቻችን  ከሱስ ከወጡ  በኋላ  ድጋሚ እንዳይመለሱ  ከማን ምን ይጠበቃል? ስንል በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሥነ ልቦና መምህር አቶ ሸጋው ሞላን ጠይቀናቸዋል:: እርሳቸው እንደሚሉት ሱሰኝነት አብሮ የሚወለድ ሳይሆን የሚለመድ (የሚማሩት)ነው። አንድ ሰው ወደ ሱሰኝነት ይገባል፣ ይወጣል፣ ተመልሶ ወደ ሱሱ ወይም ከነበረበት ወደ ከፋ ሁኔታ  የሚገባበት አጋጣሚም ይኖራል።

ሱስ ውስጥ የነበረ ሰው ከወጣ በኋላ ተመልሶ የነበረበትን ቦታ ሲያስብ ስለሚቆይ በሀሳቡ ሊመላለስ እንደሚችል አቶ ሸጋው ተናግረዋል፣ ምክንያቱ ደግሞ ለሱስ ያጋለጠው እፅ፣ መጠጥ፣ ሲጋራ… ሊናፍቀው እንዲሁም ስለነበረበት ሁኔታ ሊያወራ ይችላል። ድጋሚ ሱስ ውስጥ አለመግባት እንጅ  ወደ ኋላ ማሰብ  የማገገም ሂደት ነው:: በዚህ የማገገም ሂደት ራሱን መንከባከብ ሊያቆም ይችላል

ቀስቃሽ          ምክንያቶችም ይኖራሉ፣ ለምሳሌ አዘውትረው ይቅሙበት፣ ይጠጡበት፣ ያጨሱበት…በነበረ አካባቢ ካለፉ እና በሱስ ወቅት የነበሯቸውን ጓደኞቻቸውን ካገኙ  ወደ ቀድሞው ሱሳቸው ለመመለስ ይገፋፋሉ:: እናም ከእነዚህ  ካልራቀ  ድባቴ ሊሰማቸው ቀድሞ ወደ ነበሩበት  ሱስ  ተመልሰው  ሊገቡ ይችላሉ::

ባለሙያው እንደሚሉት ሱስ ውስጥ የቆዩ  ሰዎች ለብዙ ችግር ተጋላጭ በመሆናቸው  ቤተሰብ እገዛ ሊያደርግላቸው ይገባል:: በተለይ በቤት ውስጥ ቁጭ ብለው ቤተሰብ ሲያወሩ ካላወራ፣  የሚያስቡ ከሆነ ፣ ደስተኛ ካልሆኑ፣ የእንቅልፍ ችግር  ማለትም  ብዙ መተኛት ወይም እንቅልፍ ማጣት፣ አለመብላት /ብዙ መብላት ወይም ምግብ መተው/ ፣ መግባባት አለመቻል፣ መበሳጨት፣ ከሰው መራቅ…ምልክቶችን   ካስተዋሉ ልጆቻቸው  ችገር ላይ መሆናቸውን ተገንዝበው ከጎናቸው  ሊቆሙ ይገባል::

ቤተሰብ ማንኛውንም የሚናገሩትን ሁሉ የልጃቸውን ሥነ ልቦና እንዳይጎዳ መጠንቀቅ እንደሚገባም ባለሙያው መክረዋል። “በችግሩ ጊዜ ‘እኔ በሱ ጫማ ብሆን’ ብሎ ማሰብ እንጂ ‘የችግርህ ውጤት ነው’ ብሎ በንግግር ከመጉዳት እና ከመውቀስ ሊቆጠቡ ይገባል” ሲሉም ባለሙያው  አስገንዝበዋል::

ከሱስ ያገገሙ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከገቡበት ችግር ለመውጣት የሥነ ልቦና ምክር ያስፈልጋቸዋል:: ይህ ሲሆን ደግሞ ችግራቸውን  ዘርዝረው እንዲያወሩ እድል መስጠት ይገባል::

ድባቴ ተከስቶበት ከሁለት ሳምንት በላይ ከቆየ ወደ ህክምና መሄድ እንደሚገባም ባለሙያው አሳስበዋል፤ ይህ ሳይሆን  ብዙ ከቆየ ግን የአዕምሮ ሥርዓት ተቃውሶ መታወክ ሊከሰት እንደሚችል ነው የገለፁት::

“ሰዎች ከሱስ ከወጡ በኋላ ሙሉ ለሙሉ የመውጫ መንገዱ የራስ ጥረት እና   ፅናት እንደሆነ አቶ ሸጋው መክረዋል:: እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ችግሩን በራስ ለመወጣት ዝግጅነቱ ካለ የወጡበትን ችግር  ከሚያስታውሳቸው  ቦታ እና ሰዎች ራሳቸውን መራቅ እንዳለባቸውም አቶ ሸጋው አስገንዝበዋል።

ከዚህ ባሻገር ከሱስ የወጡ ሰዎች ወደ ነበሩበት አስከፊ ሁኔታ ላለመመለስ በተለያዩ ተግባራት   /በመዝናናት፣ ስፖርት በመሥራት፣ መንፈሳዊ  መዝሙሮችን እንደየ እምነታቸው  በማዳመጥ…/ ሊያሳልፉ እንደሚገባ መክረዋል:: ችግርን የመቋቋም ጽናት ማጠንከር፣ ወደ ሱስ ካልገቡ ሌሎች ጓደኞች እና  ከወላጅ  ጋር ግንኙነትን ማጠናከርም ዋናው መፍትሄ መሆኑን ባለሙያው መክረዋል::

በአዕምሮ ደረጃ የልቦና ውቅር እንዲስተካከል  በራስ አሊያም ከባለሙያ ጋር መሥራት ከችግሩ  መውጣትን ውጤታማ እንደሚያደርገውም ባለሙያው  ተናግረዋል::

የዓለም ጤና ድርጅት በሀገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ለረዥም ጊዜ በመቆየት ጉዳት ከሚያደርሱ እንደ ስኳር ካሉ በሽታዎች መካከል ድብርትን  እንደ አንዱ አስቀምጦታል:: ድብርት እንደ ማንኛውም አካላዊ ሕመም እንደ ስኳር፣ ኩላሊት፣ ወባ… በሽታ  ነው። ይህ ሕመም ከሰዎች ጋር አብሮ ለረዥም ጊዜ የሚኖር እና ከባድ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል የአዕምሮ በሽታ እንደሆነ ነው መረጃው የሚጠቁመው:: ድባቴ በዋናነት የሱስ መነሻ ውጤት እንደሆነም መረጃው አስፍሯል።

ጥቅሙን እና ጉዳቱን ሳያስቡ በጓደኛ ግፊት እና በሌሎች ምክንያቶች አብዛኞች ያለማንም ከልካይ የጀመሩት ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል መጠጥ፣ ሽሻ… ሲቆጣጠራቸው ሠራተኞች ሥራቸውን፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተገቢው ሁኔታ ማከናወን አቅቷቸው ከመንገዳቸው ይደናቀፋሉ:: መውጫው መንገዱም እንደአገባቡ ቀላል አይሆንም:: ችግሩ ዜጋን፣ ቤተሰብን፣  ሀገርን…ስለሚጎዳ  የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል::  ዋናው የችግሩ መውጫ መንገድ ግን  የራስ ጽናት ብቻ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያ አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል::

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here