የመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት ካዳከማቸው ሀገራት መካከል ሶሪያ አንዷ ናት፡፡ ኃያላን ሀገራቱ የእጅ አዙር ጦርነቶችን ከሚያካሂዱባቸው አውድማዎችም ዋነኛ የምትባል ናት፡፡ ከሰሞኑ በሶሪያ ዳግም ተቃውሞ እና ግጭት ተነስቷል፡፡ በሀገሪቱ ያለው ውጥረት እና አሰላለፍ ምን ይመስላል? እንቃኘዋለን፡፡
ሀያት ታህሪር አል-ሻም
ኤች ቲ ኤስ በተባለ ምሕፃረ ቃሉ የሚታወቀው ሀያት ታህሪር አል-ሻም ቡድን በአውሮፓውያኑ 2011 ሲቋቋም መጠሪያው ጃብሃት አል-ኑስራ ነበር። ነገር ግን ቡድኑ የአል-ቃይዳ ክንፍ ሆኖ ነው የተቋቋመው።
የኢስላሚክ ስቴት (እስላማዊ መንግሥት) መሪ የነበረው አቡ ባካር አል-ባግዳዲ ይህ ቡድን ሲቋቋም አስተዋፅዖ እንደነበረው ይነገራል። ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድን ተቃውመው ጠብመንጃ ካነሱ ታጣቂ ቡድኖች መካከል እጅግ ኃያሉ እና አደገኛው እንደሆነ ይነገርለታል። ነገር ግን ከአብዮታዊነት ይልቅ ወደ ጂሃዳዊ መርሆቹ ያደላል እየተባለ የሚወቀሰው ይህ ቡድን ፍሪ ሶሪያ ከተባለው ዋነኛው የአማፂያን ኃይል ኅብረት ጋር ግጭት ውስጥ ይገባ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2016 የቡድኑ መሪ አቡ ሞሐመድ አል-ጃውላኒ በይፋ ከአል-ቃይዳ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን ተናግረው ጃብሃት አል-ኑስራ መፍረሱን አሳወቁ። አቡ ሞሐመድ በቀድሞው ቡድን ፋንታ አዲስ ድርጅት ማቋቋመችውን ተናገሩ። አዲሱ ቡድን በተቋቋመ በአንድ ዓመቱ ሌሎች በርካታ አማፂ ቡድኖችን በማጣመር ሃያት ታህሪር አል-ሻም የሚል ስያሜ ተሰጠው።
ሶሪያን የሚቆጣጠራት ማነው?
ከዐሥር ዓመት በላይ ያስቆጠረው በሶሪያ እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት ባለፉት አራት ዓመታት ያበቃ መስሎ ነበር። የሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች በፕሬዝደንት ባሻር አል-አሳድ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ሲሆኑ፣ በሌሎች የሶሪያ አካባቢዎች ላይ ግን አሁንም አማፂያን ተንሰራፍተው ይገኛሉ። በተለይ በምሥራቁ ክፍል የሚገኙ በአብዛኛው ኩርዶች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ከእርስ በርስ ጦርነቱ መጀመር በኋላ ራሳቸውን ከሩሲያ መንግሥት ቁጥጥር ነፃ አውጥተዋል።
በ2011 እ.አ.አ በአሳድ መንግሥት ላይ የተነሳው አመፅ መነሻ በሆነው የደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል አልፎ አልፎ አለመረጋጋት ቢኖርም ከቁጥጥር ውጪ ግን ሆኖ አያውቅም። በሶሪያ በረሀ በኩል ራሱን ኢስላሚክ ስቴት ብሎ የሚጠራው ቡድን በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት ያደርሳል። በተለይ ደግሞ የአደን ወቅት በሚሆን ጊዜ ሶሪያዊያን ትራፍል የተባለውን ውድ ምግብ ለማምጣት ሲሄዱ ጥቃት ያደርስባቸዋል።
በሰሜን ምዕራብ የምትገኘው ኢድሊብ ግዛት በጦርነቱ ጊዜ ብቅ ብቅ ባሉ ጂሃዲስቶች እና አማፂያን ቁጥጥር ሥር ናት። ኢድሊብን የሚቆጣጠረው አማፂ ቡድን ነው ባለፈው ረቡዕ አሌፖ ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት በማድረስ የሶሪያ መንግሥት ወታደሮች ሥፍራውን ለቀው እንዲሸሹ ያስገደደው።
መራራ ግጭት
የሶሪያ መንግሥት ወታደሮች ኢድሊብን ከአማፂያን ቁጥጥር ለማስለቀቅ ለዓመታት መራር የሚባል ጦርነት አካሂደዋል። በአውሮፓውያኑ 2020 የአሳድ መንግሥት የረዥም ጊዜ አጋር በሆነችው ሩሲያ እና የአማፂያኑ ደጋፊ በሆነችው ቱርክ አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ስምምነት ተደረሰ። አራት ሚሊዮን ገደማ ሶሪያውያን ኢድሊብ ይኖራሉ። አብዛኞቹ የአሳድ ኃይሎች ከአማፂያን ጋር በሚያደርጉት ከባድ ጦርነት ምክንያት ከተለያዩ ከተሞች ሸሽተው የመጡ ናቸው።
አሌፖ እጅግ አስከፊ የሚባል ጦርነት ከተካሄደባቸው አካባቢዎች አንዷ ናት። የሶሪያ አማፂያን ትልቅ የሚባል ኪሳራ የደረሰባቸው አሌፖ በተደረገው ጦርነት ነው። ፕሬዝዳንት ባሽር አል-አሳድ ይህን ጦርነት ያሸነፉት ከሩሲያ አየር ኃይል በተደረገላቸው ድጋፍ እና ከኢራን በሚያገኙት የጦር መሣሪያ ምክንያት ነው። በኢራን የሚደገፉ ሚሊሻዎች ከሶሪያ መንግሥት ጎን ተሰልፈው ተዋግተዋል። ከእነዚህ መካከል የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ አንዱ ነው።
በቅርቡ እስራኤል በሊባኖሱ ቡድን ላይ የወሰደችው እርምጃ እና ሶሪያ በሚገኙ ኢራናውያን የጦር አዛዦች ላይ የፈፀመችው ጥቃት የኢድሊብ አማፂያን አሌፖ ላይ ያልጠተበቀ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ምክንያት ሆኗል ብለው የሚጠራጠሩ አሉ።
ሃያት ታህሪር አል-ሻም የተባለው አማፂ ቡድን መቀመጫውን ኢድሊብ አድርጎ አካባቢውን እያስተዳደረ ይገኛል። ነገር ግን ቡድኑ በአካካቢው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፅማል የሚል ወቀሳ ስለሚቀርብበት ተቀባይነት እንዳያገኝ አድርጎታል። አልፎም ከሌሎች አማፂያን ጋር ከባድ የሚባል ግጭት ውስጥ መግባቱ ይነገራል። ቡድኑ ከኢድሊብ ባለፈ ዓላማው ምንድነው የሚለው እስካሁን ግልፅ አይደለም።
አማጺ ቡድኑ ከአል-ቃይዳ ጋር ከተለያየበት ጊዜ ጀምሮ በሶሪያ እስላማዊ አገዛዝ ለመመሥረት ሲሞክር ይታያል። ቡድኑ የአሳድ መንግሥትን በመገርሰስ የሶሪያን ጦርነት ለማፋፋም ዕቅድ ያለው አይመስልም ነበር። አሁን ግን ሁኔታዎች የተቀየሩ ይመስላሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢራን ወታደሮችን ወደ ሶሪያ ለመላክ ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አል አረቢያ አል ጃቤድ ከተሰኘ የኳታር መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የሶሪያ መንግሥት ጥያቄ ካቀረበ ኢራን ወታደሮችን እንደምትልክ ተናግረዋል። ቴህራን በሶሪያ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ዳግም የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማርገብ እና ዘላቂ መፍትሄ ለመፈለግ እየተዘጋጀች መሆኑንም ነው የገለጹት።
ከአል-ቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው “ሃያት ታህሪር አል ሻም” የተሰኘው እና ሌሎች አማጺ ቡድኖች በኢድሊብ ግዛት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መጠነ ሰፊ ማጥቃት ጀምረዋል። የአሌፖ ከተማን ተቆጣጥረው የሶሪያ መንግሥት ጦርን ከከተማዋ ያስወጡት አማጺያን ሃማ የተሰኘችውን ከተማ ለመያዝ መቃረባቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። “የሽብር ቡድኖቹ ግስጋሴ ከኢራን በበለጠ እንደ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ እና ቱርክ ላሉ የሶሪያ ጎረቤቶች ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል” ያሉት የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከቱርክ ጋር ያለውን ልዩነት ለማጥበብም ቴህራን ማሸማገል ትችላለች ብለዋል።
ኢድሊብ ሩሲያ ባደራደረችው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት እ.አ.አ 2020 ጀምሮ በቱርክ ኃይሎች ጥበቃ እየተደረገላት ነው። ሩሲያ፣ ቱርክ እና ሶሪያ የመንግሥታቱ ድርጅት በሶሪያ ተኩስ እንዲቆም እና ፖለቲካዊ ሽግግር ለማምጣት በሚል በ2015 እ.አ.አ ያሳለፈውን የውሳኔ ሃሳብ ለማስፈጸም በ2017 እ.አ.አ በካዛኪስታን መዲና አስታና ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
የአስታናው ስምምነት ሦስቱ ሀገራት የጋራ የቁጥጥር ግብረ ኃይል በማቋቋም ለሶሪያ ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያበጁ ቢያዝዝም አፈጻጸሙ ላይ ክፍተት እንዳለ ይነገራል። ቴህራንም የቱርክ ወታደሮች ከሶሪያ ለቀው እንዲወጡ በተደጋጋሚ የጠየቀች ሲሆን የሶሪያ ሕዝቦች ሕጋዊ ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል የምትለው አንካራ ግን ጥያቄውን ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።
ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ቱርክ የሶሪያን ብሄራዊ አንድነት እና የግዛት ሉዓላዊነት እንደምታከብር ጠቅሰው ጦርነቱ እንዲቆም ግን የሀገሪቱን ሕዝቦች ፍላጎት ያማከለ ስምምነት ሊደረግ ይገባል ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ሃካን ፊዳን በበኩላቸው በቅርቡ ላገረሸው ግጭት ተቃዋሚዎች የሚያነሱት ሕጋዊ ጥያቄ አለመመለስን በምክንያትነት አንስተዋል።
ቴህራን ግን የአማጺያኑ ጥቃት እስራኤል እና አሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣናን የማተራመስ ዕቅድ አካል አድርጋ እንደምትመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አባስ አራጋቺ መግለጻቸው ይታወሳል። ሚኒስትሩ በወቅታዊው የሶሪያ ግጭት ዙሪያ ከሌላኛዋ የአሳድ ደጋፊ ሩሲያ ጋር ለመምከር ወደ ሞስኮ እንደሚያቀኑ መናገራቸውን አር ቲ አስነብቧል።
አሜሪካ በበኩሏ እየተባባሰ የመጣውን ተቃውሞ ተከትሎ በምሥራቃዊ ሶሪያ ጥቃት ማድረጓን አስታውቃለች፡፡ ጥቃቱ በታንክ እና በሮኬቶች የታገዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ተቃዋሚ ኃይሎች በፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ የሚመራውን መንግሥት ለመጣል ኃይላቸውን አጠናክረው በመገስገስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ በስፍራው ለሚገኘው የአሜሪካ ጦር ስጋት በመሆኑ ጥቃቱ ተሰንዝሯል ተብሏል፡፡
ተጨማሪ የመረጃ ምንጮቻችን፡- አልጀዚራ፣ ሲ ጂ ቲ ኤን እና ኒው ዮርክ ታይምስ ናቸው
(ቢኒያም መስፍ)
በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም