የነዳጅ ሥርጭት አዋጅ

0
95

የነዳጅ  ውጤቶች  ካላቸው ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ   ፋይዳ  አንጻር  ዋና  ምርቶች  ናቸው፡፡ ነዳጅ የንግድ እንቅስቃሴው እንዲሳለጥ እና ምጣኔ ሀብቱ የተሻለ እድገት እንዲያመጣ መሰረታዊ ጉዳይ እንደሆነ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ዐቃቢ ሕግ አቶ ሙሉጌታ አሻግሬ ተናግረዋል፡፡

“ልማትን ያለ ነዳጅ ማከናወን እጅግ አስቸጋሪ ነው” የሚሉት ባለሙያው  ነዳጅ ለመጓጓዣ/ለትራንስፖርት/፣ ለግብርና፣ ለሌሎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች እና ለልማት ተግባራት ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ቲ አር ቲ (TRT) የተባለው ዓለም አቀፍ የሬድዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠቀሙ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በመመደብ ከዓለም ገበያ ከምትገዛቸው ሸቀጦች አንዱ ነዳጅ እንደሆነ አቶ ሙሉጌታ ገልፀዋል፡፡ ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውም መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ በማድረግ ነው፡፡ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ መንግሥት 90 ቢሊዮን ብር የነዳጅ ድጎማ እንዳደረገም ተገልጿል፡፡

 

የነዳጅ ግብይት እና ስርጭት ችግሮች

የዐቃቢ ሕግ ባለሙያው  ለነዳጅ ስርጭት ችግር ያሏቸው በየአካባቢው እንደሚታየው ማደያዎች ነዳጅ በወቅቱ አለማምጣት እና  ተጭኖ የመጣውን  መሰወር፣ ማደያዎች ባራገፉት ነዳጅ ልክ ሳያስተናግዱ “አለቀ!” ብለው መዝጋት፣ ያለውንም ከታሪፍ በላይ መሸጥ፣ በበርሚል፣ በጀሪካን እና በፕላስቲክ ጠርሙስ/በሀይላንድ/ በመቅዳት ሕገ ወጥ ግብይት መፈጸም፣ በድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ ተሸከርካሪዎች ጭምር የወሰዱትን ነዳጅ ለሕዝብ አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ መሸጥ፣ አርሶ አደሮችን በትክክለኛ መንገድ እና ለትክክለኛው ዓላማ ነዳጅ እንዲያገኙ አለማድረግ፣ ተቆጣጣሪ እና ድጋፍ ሰጭ ተቋማት የቁጥጥር እና የክትትል ችግር እንዲሁም በሕገ ወጥ ተግባራት መሳተፍ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

 

የነዳጅ ውጤቶች መመሪያዎች እና አሠራሮች

የነዳጅ ውጤቶች የሥርጭት፣ የርክክብና የሽያጭ አፈጻጸም መመሪያ 904/2014 የነዳጅ ማደያ በሌላቸው ከተሞች እና አካባቢዋች የነዳጅ ችርቻሮ ፈቃድ /በጀሪካን፣በፕላስቲክ ጠርሙስ/ አሰጣጥና ቁጥጥር መመሪያ ተሰጥቷል፡፡

906/2014 መመሪያ ደግሞ ነዳጅን ከኩባንያዎች በቀጥታ በመግዛት ለሚጠቀሙ አካላት የአሠራር መመሪያ የነዳጅ ውጤቶች የዋጋ ግመታ፣ የታሪፍና የትርፍ ህዳግ መመሪያ እና የኮታ አሠራር ሥርዓት በነዳጅ ውጤቶች ላይ የሚፈጸመውን ብክነትና ሕገ ወጥነት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የዲጂታል ግብይት ሥርዓትና የነዳጅ ማኔጅመንት ሲስተም ፣ የነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች የጉዞ መቆጣጠሪያ /GPS /ተገጥሞላቸው እንቅስቃሴያቸውን ከማዕከል ለመቆጣጠር የሚያስችል አሰራር ነው፡፡

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የአማራ ክልል የነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭት ማስፈጸሚያ ደግሞ መመሪያ ቁጥር 03/2010 በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡ የወጣው የነዳጅ ግብይት አዋጅ ቁጥር 1363/17 ከውጭ በመግዛት ማቅረብን፣ ማደባለቅን፣ በጅምላና በችርቻሮ ማከፋፈልን፣ ማጓጓዝን ማከማቸን ወይም ተዛማጅ ተግባራትን የሚያጠቃልል የተገደበ የንግድ ሥራ መሆኑንም የዐቃቢ ሕግ ባለሙያው አብራርተዋል፡፡

 

አዋጁን ማውጣት ያስፈለገበት ምክንያቶች

የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦታቸው፣ ክምችታቸው፣ስርጭታቸው፣ደህንነታቸው፣ ጥራታቸው እና ዋጋቸው ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ የመመሪያው አስፈላጊነትም  የነዳጅ ውጤቶች በሰው ጤና፣ በንብረትና በአካባቢ ላይ  ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ መከናወናቸውን  ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ  ከአስመጪው ጀምሮ እስከ መጨረሻው ተጠቃሚ ድረስ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ አስተማማኝ፣ ፍትሐዊ  እና ተደራሽ የአቅርቦት፣ የስርጭት  እና የችርቻሮ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ እየታዩ ያሉ ሕገ-ወጥ ተግዳሮቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

የአዋጁ መውጣት በዘርፉ የተሰማሩ የነዳጅ ተቋማትና ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ልምድ በሚጠይቀው መሠረት በሚፈለገው የብቃት ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ደህንነቱ የተጠበቀና ሕጋዊ የነዳጅ ውጤቶች የግብይት ሥርዓት ለማስፈን የላቀ ጠቀሜታም ያለው በመሆኑ ነው፡፡

 

በነዳጅ ግብይት የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጭ ማከማቸት፣ ሆን ብሎ ከባእድ ነገሮች ጋር ቀላቅሎ ለሽያጭ ማቅረብ፣ መንግሥት ከተመነው መሸጫ ዋጋ በላይ ማቅረብ፣ የተረከባቸውን የነዳጅ ውጤቶች ከተፈቀደለት የማጓጓዣ መስመር  ውጪ ማጓጓዝ፣ ከተፈቀደለት ማራገፊያ ውጪ ማራገፍ ወይም ወደ ጎረቤት ሀገር በኮንትሮባንድ ማጓጓዝ ፤ አግባብ ካለው አካል በጽሁፍ ፈቃድ ሳያገኝ የነዳጅ ውጤቶችን የነዳጅ ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች መሸጥ ወይም በመመሪያ በተወሰነው መሠረት         አደጋ ያስከትላሉ በተባሉ መያዣዎች መሸጥ፤ የነዳጅ ግብይት የዲጂታል ሥርዓት ግዴታን መጣስ፣ ማጭበርበር፣ ተግባራዊ አለማድረግ፤ የባለሥልጣኑን ወይም አግባብ ያለውን አካል የቁጥጥር ሂደት መቃወም ፣ ማሰናከል ወይም በማንኛውም ሁኔታ ተፅኖ ማድረስ፤ በነዳጅ ግብይት አዋጅ ቁጥር 1363/17 አንቀጽ 22 በወንጀል የሚያስጠይቁ ግዴታዎች ሆነው ተመላክተዋል፡፡

 

የቅጣት አይነቶች

የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ያከማቸ፣ ከሚገባው ሰው፣ ቦታ እና የግብይት ሥርአት ውጪ ሲሸጥ የተገኘ ማንኛውም ሰው የተያዘው የነዳጅ ውጤት ተወርሶ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከብር 250 ሺህ እስከ 400 ሺህ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

የነዳጅ ውጤቶችን ሆን ብሎ ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለግብይት ያቀረበ ማንኛውም ሰው ነዳጁ እንዲወገድ ተደርጎ ከአራት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እና ከብር አንድ መቶ ሺህ እስከ ሦስት መቶ ሺህ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡ ወይም አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት  እና እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር የሚደርስ መቀጮ ያስቀጣል፡፡ ይህ ወንጀል የሕግ ሰውነት ባለው አካል ተፈጽሞ ሲገኝ  ደግሞ ከብር ሰባት መቶ ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እና አምስት ዓመት ድርጅት መዝጋት ናቸው፡፡ ያሉት ባሉያው አቶ አስማማው ይህንን የሚያስፈጽሙ አካላት ደግሞ  ፍትሕ ቢሮ ፣ፓሊስ፣ ፍርድ ቤቶች፣ ድጋፍ ሰጭ እና ተቆጣጣሪ ተቋ፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here