የነዳጅ ነገር

0
163

ፓወር ኢምፓክት ዶት ኮም (powerimpact.com) ድረ ገጽ “የቴክኖሎጂ ከፍታ በደረሰበት በዚህ ዘመናዊ ዓለም ኃይል (Power) ሁሉም ነገር ነው። ዘመናዊነት ያለ ኃይል ብዙ እርምጃን መራመድ አይቻለውም” በማለት ያስነብባል። ይህም ነዳጅ የዘመናዊነት ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ነው የሚያብራራው።

ድረ ገጹ አክሎም የኃያላን ሀገራት የኃይል ሚዛን ማስጠበቂያቸው፣ የምጣኔ ሀብታቸውም የዕድገት መሠረታቸው ነው ይላል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የነዳጅ ዋጋ ተፅዕኖም ዓለም አቀፋዊ ነው ሲል ነው የሚያትተው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ታዲያ የእስራኤል – ሃማስ ጦርነትን ተከትሎ ዋነኛ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር የሆነው ቀይ ባሕር ስጋት ውስጥ ከገባ ውሎ አድሯል። ይህም በነዳጅ ምርት ላይ የዋጋ ጭማሪን አስከትሏል። ይህ ደግሞ በተለይ በድሃ ሀገራት ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረትን ነው ያስከተለው።

ለአብነትም በሀገራችን አንድ ሊትር ቤንዚን በጥቁር ገበያ ከሁለት መቶ ብር በላይ እየተቸበቸበ ይገኛል። ይህ መሆኑም በተጠቃሚዎች ላይ ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ እንዲደረግባቸው በማድረግ የኑሮ ውድነቱን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል። ክስተቱን “እውነት ነው፣ እኛም አማራጭ በማጣታችን በጥቁር ገበያ በእጥፍ ዋጋ እንገዛለን” በማለት የነዋሪዎችን ምሬት የሚጋራው ወንድሙ ጥላሁን ነው።

ወንድሙ የባጃጅ አሽከርካሪ ነው፣ “ስምንት ሊትር ነዳጅ ለመቅዳት ሌት ተቀን እንሰለፋለን፣ ይህም ሆኖ ሳይደርሰን አለቀ ይባላል” በማለት ነው ችግሩን የሚያብራራው።

አማራጭ ሲጠፋም በብዙ የዋጋ ጭማሪ ለመግዛት እንደሚገደድ ነግሮናል። “ማደያ ላይ ነዳጅ ከሌለ ሌላ ቦታ እንዴት ተገኘ?” ብሎ የሚጠይቀው ወንድሙ፣ በከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ነዳጅ በመግዛቱ (በጥቁር ገበያ) ከዚህ ቀደም ለኮንትራት ይጠይቅ ከነበረው ዋጋ ጭማሪ ለማድረግ መገደዱን ነው የተናገረው።

ከዚህ ጋር በተገናኜ ሐሳቧን ለበኩር ያጋራችው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ነደጃ ጠፋ በተባለ ቁጥር ዋናው የችግሩ ገፈት ቀማሽ ተገልጋዩ ነው ትላለች፤ ወትሮውንም ከታሪፍ ጋር በተያያዘ ያለ አግባ ጭማሪ እንደሚደረግባቸው የምትናገረው ነዋሪዋ፣ ምንም አይነት የእርምት እርምጃ ሲወሰድ እንደማትመለከትም ትዝብቷን አጋርታናች:: ይባስ ብሎ ደግሞ ከሰሞኑ ነዳጅ ጠፋ በሚል ሰበብ ሕጋዊ በሚመስል መልኩ ያልተገባ የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ እንዳለ ተናግራለች::

ከሰሞኑ ተከሰተ የተባለው የነዳጅ እጥረት ታዲያ ጅቡቲ ላይ የዘነበውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ ድልድይ በመሰበሩ ነው ብሏል። በተጨማሪም ነዳጅ የጫነ አንድ የነዳጅ ቦቴ ተገልብጦ መንገድ በመዘጋቱ የነዳጅ እጥረት መከሰቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እንዳታወቀው ችግሩ በተከሰተበት ወቅትም ቢሆን ከመጠባበቂያ የነዳጅ ማከማቻ ወጪ ተደርጎ ለነዳጅ ማደያዎች እንዲደርስ በማድረግ ችግሩን ለመፍታት ሙከራ ተደርጓል:: በዚህም አሳሳቢ የሚባል የነዳጅ እጥረት አላጋጠመም ነው ያለው:: ረጅም የነዳጅ ሰልፍ እንዲኖር ያደረገው ግን (በተለይ በአዲስ አበባ) ኅብረተሰቡ ላይ የነዳጅ እጥረት አለ የሚል ስጋት መሆኑን ድርጅቱ ጠቁሟል:: በቀጣይ እንዲህ አይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ ቶሎ ምላሽ ለመስጠት ድርጅቱ በቂ መጠባበቂያ ነዳጅ በመያዝ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ አስታውቋል::

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here