የነዳጅ እጥረት ለመስኖ ልማት ፈተና ሆኗል

0
161

የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

የነዳጅ እጥረት በመስኖ ሥራቸው ላይ ፈተና እንደሆነባቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ፤ በሰሜን ጎጃም ዞን ባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ሙሉዓለም ካሳው ለመስኖ ልማት መሬታቸውን አለስልሰው ለመዝራት ተዘጋጅተዋል። የመኸር ሰብላቸውን በመሰብሰብ ስንዴ እና ሽንኩርት እንዲሁም ሌሎች አትክልት እና ፍራፍሬ ለማልማት ነው ዕቅዳቸው።
ነገር ግን ለመስኖ ልማቱ የሚሆን ነዳጅ (በዋናነት ቤንዚን) ማግኘት እንዳልቻሉ ነው ለበኩር የተናገሩት። አርሶ አደሩ ነዳጅ ለማግኘት የሚመለከተውን አካል በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ (ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም) ቤንዚን ማግኘት እንዳልቻሉ አስረድተዋል።
አርሶ አደር ሙሉዓለም የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፕ ለመስኖ ልማት በስፋት ይጠቀማሉ። ቤንዚን ደግሞ ለሞተር ፓምፕ ቁልፍ ግብዓት ስለሆነ ጉዳዩ በልዩ ትኩረት መታየት እንዳለበት አመላክተዋል። ሌሎች አርሶ አደሮችም የአርሶ አደር ሙሉዓምን ጥያቄ በመጋራት የገጠማቸው የነዳጅ እጥረት እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል፡፡
የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ አርሶ አደሮች ያነሱትን የነዳጅ እጥረት ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ተጋርቷል። የተከሰተውን የቤንዚን እጥረት ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ መልካሙ አለኸኝ ገልፀዋል። ምክትል ኃላፊው እንዳሉት የቤንዚን እጥረቱን ለመፍታት ከዞን እና ከክልል ባለሙያዎች ጋር በትኩረት እየተሠራ ነው።
የመስኖ ልማት የሚያለሙ እና የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፕ ተጠቃሚ አርሶ አደሮችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ ነውም ብለዋል። አቶ መልካሙ እዳሉት የቤንዚል እና የናፍጣ ችግሩን ለመፍታት ከክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ጋር እየተሠራ ነው።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here