የአማራ ክልል የትምህርት እንቅስቃሴ ጉዳት ጅማሮውን የሚያደርገው በ2012 ዓ.ም የተከሰተው ዓለም አቀፉ የኮቪድ ወረርሽኝ የፈጠረውን ማኅበራዊ ክልከላ ተከትሎ ነው፡፡ ከዚያም ከጥቅም 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የተቀሰቀሰው የሰሜኑ ጦርነት በወረርሽኙ የተጎዳውን የትምህርት እንቅስቃሴ ለማካካስ የሚደረገውን ጥረት “ከድጡ ወደ ማጡ” እንደሚባለው አድርጎታል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ታኅሳስ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ከአሚኮ ወቅታዊ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት ጦርነቱ በክልሉ ከአራት ሺህ በላይ ትምህርት ተቋማት እንዲጎዱ አድርጓል፡፡ ከጦርነቱ በፊት ውስን አቋራጭ ተማሪዎችን ለመመለስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ይደረግ የነበረ ቢሆንም ከጦርነቱ /ከ2013 ዓ.ም/ ወዲህ ግን ሚሊዮኖች ከትምህርት ርቀዋል፡፡ ይህም የክልሉን ነባር የትምህርት እንቅስቃሴ ታሪክ ያጠፋ ሆኖ ይነሳል፡፡ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር እንዲቀንስ፣ ትምህርት የጀመሩት ዘግይተው እንዲጨርሱ… የሆነውም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
የሰሜኑ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መቋጨቱን ተከትሎ የክልሉን የትምህርት እንቅስቃሴ ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ የተቀሰቀሰው ውስጣዊ ግጭት ግን ጥረቱ ግቡን እንዳይመታ፣ እንዲያውም ችግሩን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” አድርጎታል፡፡
በክልሉ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ ሁለት ሺህ 833 ትምህርት ቤቶችን ለጉዳት መዳረጉን ቢሮ ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡ መፍትሔ ርቆት የቀጠለው በትጥቅ የታገዘ ግጭት እያሳደረ ያለው ተጽእኖ በትምህርት ተቋማት ጉዳት ላይ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ እንደ ክልል በ2017 የትምህርት ዘመን ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር በእቅድ ተይዞ ነበር፡፡ እስካሁን የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር ግን ሁለት ሚሊዮን 630 ሺህ 383 ብቻ ናቸው፡፡ ይህም በዓመቱ መዝግቦ ለማስተማር ከታቀደው ውስጥ 37 ነጥብ 2 በመቶ ነው፡፡
በክልሉ ከሚገኙ 181 ወረዳዎች ውስጥ 166 ወረዳዎች እና ስድስት ሺህ 636 ትምህርት ቤቶች በትምህርት ዘመኑ ምዝገባ መጀመራቸውን ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡ ዕቅዱን ለማሳካት የተማሪ ምዝገባ መቀጠሉን ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡ ባሁኑ ወቅት የሚመዘገቡ ተማሪዎች ቀድመው ተመዝግበው እየተማሩ ከሚገኙት ጋር ሳይቀላቀሉ ራሳቸውን አስችሎ ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ የተለየ የምህርት ካላንደር መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል፡፡
ለሁለተኛ ዙር ተመዝጋቢዎች የተዘጋጀው የትምህርት ካላንደር እስከ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቀጥል ቢሮ ኃላፊዋ አመላክተዋል፡፡ አሁናዊ ምዝገባው እያሳየ ያለው አዳጊ ሁኔታ አበረታች መሆኑንም ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡ የሚታለፉ ይዘቶች እንዳይኖሩ፣ ከእሁድ ውጪ ሁሉም ቀናት ለመደበኛ ትምህርት መማር ማስተማር እንዲውሉ በማድረግ ይዘቶችን በወቅቱ ለመሸፈን ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
ጥራት ያለው ትምህርት ሰጥቶ ስብዕናው የተገነባ ትውልድ ለማፍራት በርካታ አስቻይ ሁኔታዎች ሊሟሉ እንደሚገባ ሙሉነሽ (ዶ/ር) ያምናሉ፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች እስኪጠገኑ እና እንደ አዲስ እስኪሠሩ ከመጠበቅ ወጥቶ በተገኘው ምቹ አጋጣሚ ሁሉ ትምህርትን መጀመር እንደሚገባም ኃላፊዋ አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህም ከመምህራን፣ ርእሳነ መምህራን፣ ወላጆች እና ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ ለመድረስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ ውስጥ በድርቅ እና በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ጨምሮ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው ተማሪዎች ከትምህርት እንዳይርቁ አንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ በድጋፉም የአካባቢው ተወላጆች፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶች፣ አቅም ያላቸው ግለሰቦች እና ሌሎችም እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ደብተር መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
ትምህርት ቢሮም ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶች ባገኘነው ድጋፍ ባለፈው ዓመት ከሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ደብተር ማሰራጨቱን አስታውቀዋል፡፡ ቦርሳ፣ ስክርቢቶ፣ እርሳስ እና የተማሪ የደንብ ልብስ ድጋፍም እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ “አንድም ተማሪ በትምህርት ቁሳቁስ ምክንያት ከትምህርት ውጪ መሆን የለበትም” ያሉት ቢሮ ኃላፊዋ፤ አሁንም በግጭቱ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት ለደረሰባቸው ዳባት እና አየሁ ጓጉሳ ወረዳዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ግዥ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የትምህርት ቁሳቁስ ተማሪዎችን ከትምህርት እንዳያርቅ በርካቶች በከፍተኛ ትኩረት እየተንቀሳቀሱበት እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ ከአምስት ሺህ በላይ አጋዥ መጻሕፍት መሰብሰቡ ለትኩረቱ ማሳያ አድርገው አንስተዋል፡፡
የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተማሪ መጻሕፍት ስርጭትም ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ እንደሚገኝ ሙሉነሽ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ የአንደኛ ደረጃ መጻሕፍትን አሳትሞ የማሰራጨት የክልሉ መንግሥት ኃላፊነት ነው ያሉት ኃላፊዋ፣ እስከ 2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መጨረሻ 15 ሚሊዮን 517 ሺህ 698 መጻሕፍት መታተሙን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ እስከ 2016 ዓ.ም ሐምሌ ወር ድረስ 12 ሚሊዮን 143 ሺህ 69 መጻሕፍት መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጻሕፍት ሕትመት የሚከናወነው በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ነው፡፡ ባለፈው ዓመት አራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን መጻሕፍት ለክልሉ መድረሱን ያስታወቁት ሙሉነሽ (ዶ/ር)፣ ከዚህ ውስጥ አራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮኑ መሠራጨቱ ታውቋል፡፡
የመጻሕፍት ሕትመት እና ስርጭቱ በዚህ ዓመትም መቀጠሉን ቢሮ ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን መጻሕፍት ሕትመት መከናወኑ ተመላክቷል፡፡ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን መጻሕፍት ወደ ክልሉ መግባቱን ሙሉነሽ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች ሁሉ ስርጭት እየተካሄደ ነው፡፡
እንደ ቢሮ ኃላፊዋ የነገዋ ኢትዮጵያ ስትታሰብ የዛሬዎቹ ስብዕናቸው የተገነባ እና ያልተገነባ ትውልድ የማፍራት እና ያለማፍራት ጉዳይ ነው፡፡ ታዳጊዎችን ከትምህርት ማስቆም ራዐያቸውን እና ተስፋቸውን እንደማጨለም ይቆጠራል ያሉት ኃላፊዋ፤ በመሆኑም ሁሉም ለሕጻናት የመማር መብት መከበር ሊታገል እና ከለላ ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡ በትግል ላይ ያለውም አካል እየታገለ ያለው ለሕዝብ መብት መከበር ከሆነ ለሕጻናት የመማር መብት መከበር ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የታኅሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም