ከጥራት፣ ከተደራሽነት፣ ከግብዓት ውስንነት፣ ከመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ ከመምህራን አቅም ማነስ እና ከትምህርት ሥርዓቱ ቀረጻ ጀምሮ የሚነሱ ችግሮች ኢትዮጵያ በቂ እና ብቁ ተወዳዳሪ የተማረ የሰው ኅይል እንዳታፈራ ያደረጉ ምክንያቶች ሆነው ለዓመታት ሲነሱ ኖረዋል፡፡ ግጭቶችን እና የተፈጥሮ አደጋዎችን ተንተርሰው እያጋጠሙ ያሉ መፈናቀሎች ደግሞ ወትሮውንም ችግር የነበረበትን የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ችግር “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ አድርገውታል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናትን የመማር መብት የሚነፍጉ እና የዕውቀት መንደሮች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ የሚከለክሉ ሕጎችን ቢደነግግም ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በከፍተኛ የትጥቅ ግጭት ውስጥ ያሉ ሀገራት የትምህርት እንቅስቃሴ ላይ ግን መፍትሔ አላመጣም፡፡ በዓለም በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል ከተባሉት 250 ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ ግማሾቹ መፍትሔ ባልተሰጣቸው ግጭቶች ምክንያት ከትምህርት የተፈናቀሉ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያም ሰባት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ልጆቿ ከትምህርት እንደራቁባት የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች እና የአየር ንብረት ለውጥን ተከተለው የሚያጋጥሙ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ደግሞ ገዥ ምክንያቶች ሆነው ይነሳሉ፡፡ እንደ ሀገር ከትምህርት ውጪ ናቸው ከተባሉት አካባቢዎች ውስጥ የአማራ ክልል ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከትምህርት መራቃቸው ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ ተማሪዎች ተጨንቀዋል፤ ተረብሸዋል፤ የነገን መልካም ቀን ተመኝተዋል፡፡
ዓለሙ ይታየው ክልሉ ባጋጠመው በትጥቅ በታገዘ ግጭት ምክንያት ለአንድ ዓመት ከሚወደው ትምህርቱ ርቆ ከርሟል፡፡ ለሁለተኛ ዓመት ከትምህርት ለመራቅ ግን አልፈለገም፡፡ ጉዞውንም አንጻራዊ ሰላም ወዳለበት ባሕር ዳር ከተማ አድርጓል፡፡
“የክልሉ ሰላም ባይደፈርስ እና የትምህርት እንቅስቃሴው ባይስተጓጎል ኖሮ በዚህ ዓመት 11ኛ ክፍል እደርስ ነበር” የሚለው ተማሪ ዓለሙ፣ በአሁኑ ወቅት በባሕር ዳር ከተማ የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል፡፡ በመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ከ96 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገበው ዓለሙ፣ ባለፈው መጸጸት እንደማይፈልግ ተናግሯል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎች እሱ ያገኘውን ዕድል ባለማግኘታቸው ለሁለተኛ ዓመት ከትምህርት ውጪ የሆኑ በመኖራቸው ነው፡፡ ተማሪ ዓለሙ የክልሉን ሰላም መሆን ተመኝቷል፡፡
አዲሡ ተስፋ ሌላው ክልሉ ባጋጠመው የሰላም መደፍረስ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ውጪ ሆኖ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በባሕር ዳር ከተማ የስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን እያስቀጠለ ይገኛል፡፡ የሰላም እጦቱ ብዙዎች ህልማቸውን ከዳር እንዳያደርሱ እያደረገ መሆኑን ለአንድ ዓመት ከትምህርት ርቆ በቆየበት ወቅት ታዝቧል፡፡ ብዙ ተማሪዎች በድብርት እና ጭንቀት ውስጥ መሆናቸውንም ተናግሯል፡፡ አንዳንዶችም ወዳልተፈለገ ሕይወት በመግባት ላይ ናቸው፤ በሱስ ውስጥ መዘፈቅ፣ ለስደት እና ላለዕድሜ ጋብቻ መዳረግ… ከብዙ መዘዞች ጥቂቶቹ ናቸው ሲል ገልጿል፡፡
ፍላጎት ክልሉ ወደ ቀደመ ሰላሙ ተመልሶ ትምህርቱን በተወለደበት አካባቢ ከወላጆቹ ሳይርቅ ማስቀጠል የተማሪ አዲሡ ፍላጎት ነው፡፡ በዚህም የትምህርት ግብዓት እና የምግብ ፍጆታ ሳይፈትነው ትምህርቱን ከችግር ነጻ ሆኖ በመከታተል ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆን ያምናል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ አዘጋጅቶት በነበረው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ያገኘናቸው የማኅበረሰብ ወኪሎችም ግጭቱ በትምህርት ዘርፉ ላይ ያደረሰው ጉዳት ከቃል በላይ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡ ከምሥራቅ ጎጃም ዞን የመጡት መምህር መላኩ በላይ ግጭቱ ከዚህ በላይ መቀጠል እንደሌለበትም ገልጸዋል፡፡ ግጭቱ “ዛሬ ላይ በትምህርት የምንፈጥራቸው የነገ አገልጋይ ዜጎችን እንድናጣ እያደረገን ነው” በማለት ግጭቱ በትውልድ ቅብብሎሽ ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና አንስተዋል፡፡
መምህሩ የችግሩን ስፋት በቃል ከመግለጽም በላይ በሚያስተምሩበት እና በሚኖሩበት አካባቢ በተማሪዎች እና በመምህራን ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት አንስተዋል፡፡ የትምህርት አሰጣጡ መስተጓጎል ገጥሞታል፤ ዛሬ የተከፈቱ ትምህርት ቤቶች ዓመቱን ሙሉ ተረጋግተው መማር ማስተማር እንዳያከናውኑ አድርጓቸዋል ነው ያሉት፡፡ የሰላም እጦቱ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡ መምህራን በነጻነት የመማር ማስተማር ሂደቱን እንዳያከናውኑ የሆኑት ግጭቱ መፍትሔ በማጣቱ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑ ሁሉም ለታላቁ የመኖር ዋስትና ሰላም ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ግጭቱ ከፍተኛ ተጽእኖ ከፈጠባቸው አካባቢዎች መካከል የምሥራቅ ጎጃም ዞን ይገኝበታል፡፡ የትምህርት መምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ደመላሽ ታደሠ ለአሚኮ እንዳስታወቁት በዞኑ 996 ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ክልሉ ባጋጠመው የሰላም እጦት ምክንያት በአሁኑ ወቅት በመማር ማስተማር ላይ የሚገኙት 158 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው፡፡
ችግሩ የፈጠረውን ክፍተት ለማሳየት አቶ ደመላሽ ያነሱት የተፈታኝ ተማሪዎችን ቁጥራዊ አኃዝ ነው፡፡ ዞኑ በስድስተኛ ክፍል አራት ሺህ 246፣ በስምንተኛ ክፍል 4 ሺህ 284 እና በ12ኛ ክፍል 4 ሺህ 62 ተማሪዎችን ያስፈትናል፡፡ በዓመቱ በሁሉም የክፍል ደረጃዎች ይፈተናሉ የተባሉት የተፈታኞች ቁጥር ክልሉ ሰላም በነበረበት ወቅት ከ12ኛ ክፍል ብቻ ከሚፈተኑት ያነሰ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ግጭቱ ምን ያህል በክልሉ የተማረ የሰው ኀይል ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረ መሆኑን ነው፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ለዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም እንዳስታወቀው በአንድ ሺህ 71 ትምህርት ቤቶች 896 ሺህ 165 ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ዕቅድ ተይዟል፡፡ ይህ መረጃ ከመምሪያው ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ በተጨባጨ መመዝገብ የተቻለው 249 ሺህ 879 ተማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ አሁንም 646 ሺህ 286 ተማሪዎች ወደ ትምህርት አልተመለሱም ማለት ነው፡፡ ከስድስት መቶ በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ 410 ትምህርት ቤቶችም ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡
የአማራ ክልል የተማሪ ወላጆች ማኅበር ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ተማሪ ወላጆች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አዱኛው እሸቴ በበኩላቸው በትምህርት ዘርፉ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር እንዲያበቃ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ተሳታፊ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡ እንደ አቶ አዱኛው እንደ ሀገር ከትምህርት ውጪ የሆኑት ከሰባት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ሀገርን ምን ያህል ከዓለም ሀገራት የውድድር መድረክ እንደሚያወጣት መገመት አያዳግትም ሲሉ ተጽእኖውን ገልጸዋል፡፡
“የአማራ ዶክተር የኦሮሞ፣ የትግራይ፣ የሲዳማ… በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ዶክተር ነው፤ መሀንዲሱ፣ ዳኛው፣ መምህሩ፣ ሹፌሩ… የሚያገለግሉት የአንድን ወገን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሎም የዓለምን ሕዝብ ነው” በማለት የተማረ ዜጋ ብሔር፣ ሃይማኖት… መርጦ ሳይሆኑ ሁሉንም በሰብዓዊነት ስለሚያገለግል ጉዳቱ ሀገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ሀገር የምትገነባው ብሎም ዕድገቷን የምታረጋግጠው፣ ትውልድ የሚቀጥለው… በትምህርት በረከትነት በመሆኑ ግጭት እንዲቀጥል ከሚያደርግ አስተሳሰብ መውጣትን በመፍትሔነት እንዲሠራበት ጠይቀዋል፡፡ ለዚህም በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኅይሎች እና መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አምነው በትኩረት መሥራት እንደሚኖርባቸ ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2017 የትምህርት ዘመን የስድስት ወር ዕቅድ አፈጻጸሙን በአዲስ አበባ በገመገመበት ወቅት ቢሮ ኃላፊዋ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) የዚህ ዘመን የአማራ ክልል ተቀዳሚ የትምህርት ሥራ 13 በመቶ ላይ የሚገኘውን የትምህርት ቤች ደረጃ ማሳደግ፣ አሁንም ድረስ ዳስ የሆኑ 46 ትምህርት ቤቶች እና 243 መማሪያ ክፍሎችን ደረጃቸውን ማሻሻል ሊሆን ይገባ ነበር ብለዋል፡፡ ይሁንና ባለፉት አምስት ዓመታት ያጋጠሙ የሰላም መደፍረሶች ዕቅዱ እንዳይሳካ በማድረግ በትምህርት ዘርፉ ላይ ያሳደሩትን ተጽእኖ አንስተዋል፡፡
የሰሜኑ ጦርነት በክልሉ አራት ሺህ 200 ትምህርት ቤቶች እንዲወድሙ ማድረጉ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ውስጥ አሥር በመቶ ለሚሆኑት ምላሽ መሰጠቱን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ያጋጠመው በትጥቅ በታገዘ ግጭት ሁለት ሺህ ትምህርት ቤቶች ላይ የተለያየ አይነት ጉዳት እንዲያጋጥም ምክንያት ሆኗል፡፡
ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው ጦርነት ግጭት ተቋማትን ለውድመት ከመዳረግ ባለፈ ነገ ተቋማትን በሚገነቡ፣ ቴክኖሎጂ በሚፈጥሩ፣ የታመመን በሚያክሙ፣ ያልተማረን በሚያስተምሩ… የዛሬ ላይ ትምህርት ፈላጊ ታዳጊዎችም ላይ የከፋ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡ እንደ ሙሉነሽ (ዶ/ር) የሰሜኑ ጦርነት ጦስ አሁንም መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ በሰሜኑ ጦርነት ሙሉ ለሙሉ ትምህርት ቤቶቻቸው የፈሩሱባቸው 136 ሺህ ተማሪዎች አሁንም ወደ ትምህርት አልተመለሱም፡፡ በክልሉ የተከሰተው ግጭትም በ2016 ዓ.ም ብቻ 42 በመቶ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ አልፏል፡፡
የሰላም መደፍረሱ አንጻራዊ ሰላም ላይ ደርሷል በተባለበት 2017 ዓ.ም እንኳ ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርት ቤት መሄድ አለመቻላቸውን ኃላፊዋ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ተመዝግበው ካልመጡ 400 ሺህ በላይ ተማሪዎች ጋር ሲደመር በዓለም ላይ ዝቅተኘ የሕዝብ ቁጥር ካላቸው 106 ሀገራት የሕዝብ ቁጥር የሚበልጥ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ በርብርብ አለመሥራት በክልሉ እና በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የሚፈጥረው የትውልድ ክፍተት ከፍተኛ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ይህም የትውልድ ክፍተት በተውሶ የማይሞላ ከባድ ውድቀትን ይዞ የሚመጣ እና የነገን ጉዞ የሚያደበዝዝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ዛሬ በአግባቡ ያላስተማርነው የነገ ሀኪም ህመማችንን አይፈውስም፤ ዛሬ በአግባቡ ያላስተማርነው መሀንዲስ ነገ ከተሞቻችንን አይገነባም፤ በየሙያ ዘርፉ እኛን ከተቀረው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርጉን ልጆች እናጣለን” ሲሉ አሁናዊ አሳሳቢነቱን ገልጸዋል፡፡
ማንኛውም ለልጆቹ የነገ ተስፋ እና ዘላለማዊ ቅርስ ማውረስ የሚፈልግ ሁሉ ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ሕጻናትን ወደ ትምህርት ቤት በመመለስ፣ ለመምህራን ጥላ እና ከለላ በመሆን የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ በመገንባት ሁሉም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም