“የነጭ ጠንቋዮች” ዘመን ማብቂያ እና የአፍሪካ አሰልጣኞች ትንሳኤ

0
142

ለዐስርት ዓመታት የአፍሪካ ዋንጫ ሲካሄድ ተመልካች በቴሌቪዥን መስኮት የሚመለከተው አንድ የተለመደ ምስል ነበር። በሜዳው ላይ የሚሮጡት፣ የሚላተሙት እና ሜዳ ላይ የሚጠበቡት ጥቁር አፍሪካውያን ሲሆኑ ከሜዳው ውጭ ቆሞ የሚጮኸው፣ ታክቲክ የሚነድፈው እና ድሉን የሚያጣጥመው ግን አውሮፓዊ አሰልጣኝ ነበር። እነዚህ አሰልጣኞች በአፍሪካ እግር ኳስ መገናኛ አውታር ዘንድ ነጭ ጠንቋዮች (White Witch Doctors) የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷቸው ነበር። ስያሜውን ያገኘው በአጭር ጊዜ መጥተው የሀገራትን ካዝና የሚያራቁት ዶላር ዘግነው ቡድኖችን ለውድድር አሳልፈው ወደ ሀገራቸው የመመለስ አስማታዊ በሚመስል አካሄዳቸው ነበር።

አንድ የአፍሪካ ሀገር ብሄራዊ ቡድን ውጤት ሲርቀው የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ቀዳሚ መፍትሄ አድርጎ የሚወስደው እርምጃ የአካባቢውን ባለሙያ ማበረታታት ወይም ዘላቂ  መዋቅር መዘርጋት ሳይሆን ወደ ፓሪስ፣ ብራሰልስ ወይም ሊዝበን መብረር ነበር። ከዚያም በገዛ ሀገሩ ሥራ ያጣን ምናልባትም በሦስተኛ ዲቪዚዮን የሚመራን ወይም ጡረታ የወጣን አሰልጣኝ ለአፍሪካ ይሆናል በሚል ስሌት በውድ ደመወዝ ቀጥሮ ያመጣል። እነዚህ አሰልጣኞች የአፍሪካን ፀሐይ፣ የአፍሪካን ሜዳ፣ የአፍሪካን ምግብ እና የአፍሪካን ተጫዋቾች ስነ ልቦና ሳያውቁ እንደ አዳኝ መጥተው እንደ ጎብኝ ይመለሱ ነበር።

ይህ አካሄድ አፍሪካውያን በራሳቸው አቅም ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ያደረገ ስፖርት  ብቻ ሳይሆን የስነ ልቦና ጦርነት  ጭምር እንጂ። ነገር ግን አሁን ላይ የአፍሪካ እግር ኳስ ራሱን ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እያላቀቀ ይገኛል። በሞሮኮ እየተካሄደ ባለው የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚታየውም ይህንን እውነት በአደባባይ አረጋግጧል። አሁን ብዙው የብሄራዊ ቡድኖች የአሰልጣኞች ዙፋን የተያዘው በውጭ ዜጎች ሳይሆን በሀገር ውስጥ አሰልጣኞች ነው። የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ውድድሮች በተለየ መልኩ የአፍሪካውያን አሰልጣኞች የበላይነት የታየበት ታሪካዊ መድረክ እንደሆነ የፍራንስ 24 መረጃ ያስነብባል።

ህጉሪቱ ለዘመናት በውጭ አሰልጣኞች ላይ የነበራትን ጥገኝነት በመስበር አብዛኛዎቹን ብሄራዊ ቡድኖች ለገዛ ልጆቿ አስረክባለች። በውድድሩ ላይ የሚሳተፉትን 24 ቡድኖች ስንመለከት የአሰልጣኞቹ ስብጥር በግልጽ የሚያሳየው ይህንን ሽግግር ነው። ከ24ቱ ተሳታፊ ሀገራት ውስጥ 14ቱ ወይም 58 በመቶ የሚሆኑት በአፍሪካውያን አሰልጣኞች የሚመሩ ሲሆን 10ሩ ወይም 42 በመቶ የሚሆኑት ብቻ የውጭ ዜጎች ናቸው። ይህ የቁጥር ብልጫ በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን ባለፉት ዐስርት ዓመታት የተደረገው የትግል እና የእምነት ለውጥ ውጤት ነው ይላል የቢቢሲ አፍሪካ ሰፖርት መረጃ።

ከዚህ ቀደም ብዙ አፍሪካዊ አሰልጣኞች በገዛ ሀገራቸው መገናኛ ብዙኃን ሳይቀር ብቃት የላቸውም እየተባሉ ሲብጠለጠ እንደነበር አይዘነጋም፤ ዛሬ ግን የብሄራዊ ቡድኑ ቁልፍ ሰዎች ሆኖ እየታዩ ነው። በውድድሩ ላይ የሚታዩት አሰልጣኞች ቁጥር የሚያሳየው የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ከውጭ የሚመጣ ሁሉ ወርቅ ነው የሚለውን አስተሳሰብ እርግፍ አድርገው በመተው ተሰጥኦው ከዚሁ ከቤታችን አለ ወደሚለው እምነት መሸጋገራቸውን ነው።

የገዛ ሀገራቸውን የሚመሩ አሰልጣኞች በታሪክ አብዛኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በማንሳት ቀዳሚዎች ናቸው። ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ የመገናኛ አውታሮች ለውጭ አሰልጣኞች የተለየ ትኩረት ቢሰጡም እውነታው ግን ዋንጫው በብዛት የተወሰደው በአፍሪካውያን አሰልጣኞች ነው። እስካሁን ከተካሄዱት 34 የአፍሪካ ዋንጫዎች ውስጥ 18ቱን ያሸነፉት የገዛ ሀገራቸውን የመሩ አፍሪካውያን አሰልጣኞች መሆናቸውን ካፍ ኦላይን ያስነብባል። ይህ አሃዝ በቅርብ ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣ ሲሆን ባለፉት ሦስት ተከታታይ የአፍሪካ ዋንጫዎች ማለትም በ2019፣ 2021 እና 2023 ዋንጫውን ያነሱት በሙሉ ሀገር በቀል አሰልጣኞች ናቸው። እነሱም ጃሜል ቤልማዲ ከአልጄሪያ፣ አሊዩ ሲሴ ከሴኔጋል እና ኤመርስ ፋዬ ከኮትዲቫር ናቸው።

የአፍሪካ ዋንጫን ሦስት ጊዜ በማንሳት ክብረወሰን የያዙት ሁለት አሰልጣኞች ብቻ ናቸው። እነሱም የጋናው ቻርልስ ጂያምፊ እና የግብፁ ሀሰን ሸሀታ ሲሆኑ ሁለቱም የገዛ ሀገራቸውን እየመሩ ስኬትን የተጎናጸፉ ጀግና አሰልጣኞች ናቸው። በአንጻሩ ከአፍሪካ ውጪ የመጡ አሰልጣኞች በተለይም ከ1980ዎቹ እስከ 2010 እ.አ.አ አጋማሽ ድረስ የአፍሪካን እግር ኳስ በበላይነት ተቆጣጥሮ ነበር። በአጠቃላይ 16 የአፍሪካ ዋንጫዎችን ያሸነፉ ሲሆን ፈረንሳዊው ሄርቬ ሬናርድ በሁለት የተለያዩ ሀገራት ማለትም በዛምቢያ እ.አ.አ በ2012 እና በኮትዲቫር በ2015 ዋንጫውን ያነሱ ብቸኛው አሰልጣኝ መሆናቸውን ቢቢሲ ስፖርት አመልክቷል። ይህ ስኬታቸው አሁን እየቀነሰ መጥቷል። ከውጪ ሀገር አሰልጣኞች ለመጨረሻ ጊዜ ስኬታማ የሆነው እ.ኤ.አ በ2017 ካሜሩንን የመሩት ቤልጂየማዊው ሂዩጎ ብሩስ ናቸው። ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ግን የውጭ አሰልጣኞች ለፍጻሜ ከመድረስ ባለፈ ዋንጫውን መንካት አልቻሉም። ይህም “የነጭ ጠንቋዮች” ዘመን ማብቃቱን የሚያመላክት ትልቅ ማሳያ ነው ሲል ካፍ ኦንላይን አስነብቧል። ሌላው በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ አንድ አፍሪካዊ አሰልጣኝ የሌላ አፍሪካ ሀገርን ብሔራዊ ቡድን በመምራት ዋንጫውን አሸንፎ አያውቅም። ናይጄሪያዊው ስቲቨን ኬሺ ቶጎን ወደ ዓለም ዋንጫ በመውሰድ ታሪክ ሠርተው ነበር፤ ነገር ግን የአፍሪካን ዋንጫ ማሳካት አልቻሉም።

የአፍሪካን እግር ኳስ ለውጥ ለመረዳት የሴኔጋሉን አሊዩ ሲሴን እና የሞሮኮውን ዋሊድ ሬግራጉን ጉዞ መመልከት በቂ ነው። የሴኔጋል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአሊዩ ሲሴ ጊዜ በመስጠት ያሳየው ትዕግስት ለሌሎች አርአያ የሚሆን ነው። እ.አ.አ በ2002 የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ፍጹም ቅጣት ስቶ ዋንጫ ያሳጣው ሲሴ በ2021 አሰልጣኝ ሆኖ ሴኔጋልን ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን አደረገ። በሌላ በኩል “የአቮካዶ ጭንቅላት” በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ዋሊድ ሬግራጉ ሞሮኮን በዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ በማድረስ የአፍሪካን አሰልጣኞች ስም በዓለም አደባባይ አስጠራ። የሬግራጉ ትልቁ ጥንካሬ የዲያስፖራ ተጫዋቾችን ከሀገር ውስጥ ተጫዋቾተን ጋር የማዋሃድ ችሎታው ነው።

እ.አ.አ በ2023 ኮትዲቫር በሀገሯ ባስተናገደችው ድግስ በፈረንሳዊው ዣን ሉዊስ ጋሴት ስር በገዛ ሀገሯ አራት ለባዶ ተሸንፋ ተዋርዳ ከውድድሩ ልትወጣ ጫፍ ደርሳ እንደነበር የሚታወስ ነው። ነገር ግን ኤመርስ ፋዬ ዋንጫውን አነሳው። የውጭ አሰልጣኞች ዘመን ማብቃት ለአፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ እፎይታ እና ፖለቲካዊ ትርጉም አለው። የውጭ አሰልጣኞች በወር ከ40 ሺህ እስከ 100 ሺህ ዶላር እና ከዚያ በላይ ይከፈላቸዋል። ይህ ገንዘብ ከአፍሪካ ድሃ ሀገራት ካዝና ወጥቶ ወደ አውሮፓ ባንኮች ይገባ ነበር። ለምሳሌ ግብፅ ለቀድሞ አሰልጣኞቿ ትከፍል የነበረው ሚሊዮን ዶላሮች አሁን ለሀገር ውስጥ የእግር ኳስ ልማት እያዋለች ትገኛለች። የአፍሪካ መሪዎችም አሁን በፖለቲካዊ ጫና ምክንያት ወደ ሀገር በቀል አሰልጣኞች ፊታቸውን እያዞሩ ነው። ሕዝቡ የራሳችን ልጅ ይምራን የሚል ጥያቄ ሲያነሳ መንግሥታትም ምላሽ ለመስጠት እየተገደዱ ነው።

እነ አሊዩ ሲሴ፣ ዋሊድ ሬግራጉ፣ እና ጀመል ቤልማዲ የእግር ኳስ ሳይንስን ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው። እነዚህ አሰልጣኞች የአውሮፓን እግር ኳስ እውቀት ከአፍሪካዊ ተፈጥሮ ጋር አዋህደውታል። ይህ ታክቲካዊ ተለዋዋጭነት ለአፍሪካ ቡድኖች ድል ቁልፍ መሳሪያ ሆኗል። አሁን አፍሪካውያን አሰልጣኞች ቴክኖሎጂን፣ ዳታ አናሊቲክስን እና ዘመናዊ የህክምና ሳይንስን በመጠቀም ከማንም እንደማያንሱ እያረጋገጡ ነው።

ምንም እንኳን ለውጡ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም አሁንም ፈተናዎች አልጠፉም። አንዳንድ የአፍሪካ ፌዴሬሽኖች አሁንም የነጭ አሰልጣኝ ናፍቆት አለባቸው። ለሀገር ውስጥ አሰልጣኝ የሚሰጠው ክብር፣ ደመወዝ እና የውል ስምምነት ዋስትና አሁንም አናሳ ነው። ነገር ግን ውጤቶቹ አፍ አውጥተው እየተናገሩ ነው። በቅርቡ ግብፅ፣ ቱኒዚያ፣ ጋና እና ካሜሩን ብሄራዊ ቡድኖች በውጭ አሰልጣኞች ትልቅ ውድቀት እንደገጠማቸው አይዘነጋም፤ እናም የውጭ አሰልጣኞች ዋስትና ከመሆን አልፈው ሸክም እየሆኑ ነው ሲል የካፍ ኦንላይን መረጃ አመልክቷል።

 

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የታህሣስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here