የኑሮ እስትንፋስ- ብዝኃ ሕይወት

0
42

የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ ያለውን የብዝኃ ሕይወት ሀብት በአግባቡ በመጠበቅና በማልማት ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ዘርፉን የሚመራ ተቋም በማደራጀት እየሠራ ይገኛል። ከነዚህ ተቋማት መካከልም የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን አንዱ ነው። ተቋሙ በአዋጅ ቁጥር 280/2014 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በአዋጁ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሠረት የአካባቢ ብክለትን እና የብዝኃ ሕይወት መመናመንን በመከላከል፣ የአካባቢ፣ ደን እና ዱር እንስሳት ጥበቃ እና ልማት ሥርዓትን ለማስፈን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ባለስልጣኑ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ (ከ2018 ዓ.ም – 2022 ዓ.ም) በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን ባሳታፈ መልኩ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባቱን አስታውቋል፡፡

ዕቅዱ በዋናነት የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ፣ የአካባቢ ብክለትን እና ብክነትን መቆጣጠር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ሥራዎችን ማስተባበር፣ የደን እና ዱር እንስሳት ሀብቶችን በአግባቡ መጠበቅ እና ማልማት ላይ አተኩሮ ተዘጋጅቷል ነው የተባለው። ይህንንም በውጤታማነት ለመምራት ያስችል ዘንድ ከባለድርሻዎች ጋር የዕቅድ ትውውቅ አካሂዷል።

የክልሉ መንግሥት የ25 ዓመት አሻጋሪ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ትግበራ መግባቱ ይታወሳል፤ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱም ከዚህ በመነሳት ነው የአምስት ዓመታቱን ዕቅድ ያዘጋጀው።

በዕቅድ ትውውቁ ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል፤ ከእነዚህም መካከል የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ለበኩር የተናገሩት የሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢና ደን ጥበቃ ፅ/ቤት ኃላፊ አበበ ታደግ ናቸው። ፋብሪካዎች ባሉባቸው ከተሞች (ለአብነት ቡልጋ) አካባቢ ከብክለት ነፃ ሆነው እንዲሠሩ እና  የአካባቢው ማኅበረሰብ የጤና ችግር እንዳይገጥመው በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ አካባቢን በሚበክሉ እና በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ጉዳት በሚያደርሱ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች (ፋብሪካዎች) ላይ የቃል እና የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት እንዲሁም ፈቃድ እስከመሰረዝ ድረስ ሕጋዊ ርምጃ ተወስዷል።

በሌላ በኩል ፕላስቲክ በሰዎች፣ በእንስሳት እና በብዝኃ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፤ ግንዛቤም እየተፈጠረ ነው፡፡ በየቦታው ከመጣል በመቆጠብም ወደ ፋብሪካዎች በማስገባት መልሶ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ምቹ እና ጤናማ በሆነ አካባቢ ሠርቶ እንዲለወጥ ሥራዎች በበለጠ ተጠናክው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን አካባቢና ደን ጥበቃ ኃላፊ ዘነቡ ፈንቴ በበኩላቸው በ2017 ዓ.ም ሕገ ወጥ አደንን፣ የእሳት ቃጠሎን እና የደን ጭፍጨፋን ለመከላከል ጥረት መደረጉን ተናግረዋል። ለአብነትም በ23 ሄክታር የተፈጥሮ ደን ላይ በባለቤትነት እንዲጠበቁ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ስለመቻሉ እና በዚህም ደን እንዳይጨፈጨፍ መደረጉን አንስተዋል።

ሌላ ኃላፊዋ ያነሱት የደረቅ እና የፍሳሽ ቆሻሻን አወጋገድ የተመለከተ ነው፤ በተገቢው መንገድ ለማስወገድ እና ጥቅም ላይ ለማዋል አደረጃጅቶች ተፈጥረው መልካም ተግባራት ተከናውነዋል።

ወ/ሮ ዘነቡ እንዳሉት ፓርኮችን ማኅበረሰቡ በባለቤትነት እንዲጠብቅ እና ቁጥጥር እንዲያደርግ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል። የክልሉን አሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ፍኖተ ካርታ እስከታችኛው መዋቅር ተግባራዊ እንዲሆንም እየተሠራም ነው።

ከዚህ ጋር በተገናኘ በተለይ በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ለሚገኙ ብርቅየ እንስሳት (በዋናነት ዋልያ) እየተደረገ ያለውን ጥበቃ፣ በሕገ ወጥ አዳኞች ላይ እየተወሰደ ስላለው ርምጃ ጥያቄ አንስተንላቸው ነበር፤ ኃላፊዋ በምላሻቸውም ችግሩን በፈጠሩ ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ ርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል። ከአጋር መሥሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት በመሠራቱም ችግሩን መቀነስ መቻሉን አንስተዋል፡፡ ብርቅየ የዱር እንስሳትን በመጠበቅ እና በመንከባከብ ለቱሪዝም ማዕከል በማድረግ የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት በጥብቅ ሥፍራዎች ላይ ሕገ ወጥ እርሻ፣ ሰደድ እሳት፣ የእንስሳት አደን እና ሕገ ወጥ ሰፈራ እንደነበር ያነሱት ኃላፊዋ ከአካባቢዉ ማኅበረሰብ ጋር በተደረገ ውይይት የባለቤትነት ስሜት ተፈጥሯል፤ ማኅበረሰቡም በባለቤትነት እየጠበቀ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኃላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ እንዳሉት ተቋሙ የተሰጠውን ሥልጣን እና ተግባር በተገቢው መንገድ ውጤታማ አድርጎ ለመምራት የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅቷል፤ ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ለመፍጠርም እየተሠራ ነው። ለዚህ ደግሞ የአካባቢ፣ የደን እና የዱር እንስሳት ሀብቶችን በአግባቡ መጠበቅ፣ ማልማት እና ዘላቂነትን ማረጋገጥ ይገባል።

የተተከሉ ችግኞችን የጽድቀት ምጣኔ ለማሳደግ እና የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና የብዝኃ ሕይዎት ጥበቃ ላይ እንዲሁም ወንዞችን እና ሐይቆችን ከብክለት ለመከላከል የተከናወኑትን መልካም ሥራዎችን  አቶ ተስፋሁን አንስተዋል።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ 2017 ዓ.ም የአካባቢ እና ደን ጥበቃን በተመለከተ የወጡ አዋጆችን እና ሕጉን በማስከበር ውጤት የተመዘገበበት ዓመት ነበር። የልማት ሥራዎች የአካባቢን ሕግ ያከበሩ መሆናቸውን በማረጋገጥ እንዲሠሩ መደረጉም ለዚህ አብነት ነው።

ብሔራዊ ፓርኮችንም የመንከባከብ እና የመጠበቅ፣ ብርቅየ እንስሳት እና አዕዋፍ የሚገኙበትን የብዝኃ ሕይዎት አካባቢ ተገቢውን ጥበቃ እና እንክብካቤ ማድረግ እንደተቻለ በማንሳት ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የአካባቢ ቁጥጥር ሥራዎች የአንድ ወቅት እና የአንድ ተቋም ሥራ ብቻ አይደሉም ያሉት ኃላፊው የሁል ጊዜ እና የሁሉም ተቋማት ሥራ እንደሆነም አስረድተዋል። በክልሉ ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ ሕገ ወጥ አደን፣ ሕገ ወጥ ሰፈራ እና እርሻ፣ የዱር እንስሳት እና ውጤቶቻቸውን በሕገ ወጥ መንገድ ማዘዋወር፣ የአካባቢ ብክለትን በወጥነት አለመከላከል እና መሠል ውስንነቶች እንደነበሩ ጠቅሰዋል። በቀጣይም የነበሩ ውስንነቶችን  በመፍታት እና ጥንካሬዎችን በማስቀጠል የተሻለ ለመሥራት (ዕቅዱን ውጤታማ ለማድረግ) ሁሉም ባለድርሻዎች የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

 

መረጃ

ጥብቅ ሥፍራ ምንድን ነው?

ጥብቅ ሥፍራ የብዝኃ ሕይወት ሀብቱ እና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ እንዲሁም ወሰኑ በግልፅ ተለይቶ የታወቀ፣ ትኩረት የተሰጠው እና በሕግ ወይም በሌላ ውጤታማ መንገድ የሚመራ የረዥም ጊዜ ጥበቃ እና ልማት የሚደረግለት ቦታ ነው።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here