የኑሮ ውድነቱ ከዕለት ወደ ዕለት እየከበደ
ነው፤ ግጭቱ ደግሞ ዋነኛ አባባሽ ምክንያት
ሆኗል:: ይህም አቅርቦት እንዲመናመን፣
የገንዘብ የመግዛት አቅም እንዲዳክም፣ ገደብ ያጣ
የግብይት ሥርዓት እንዲኖር አድርጓል፤ ምጣኔ
ሀብታዊ ችግርን በመፍጠር የማሕበረሰቡን
የመኖር አቅም ከመፈታተን አልፎ አንዳንዶች
ላይ የረሀብ አደጋ ደቅኗል::
በተለይም በአሁኑ ጊዜ በሰዓታት ውስጥ
በምርቶች ላይ የሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ
በማሕበረሰቡ ዘንድ አስጨናቂ የየዕለት መወያያ
አጀንዳ ሆኗል:: ከከተማ እስከ ገጠር የኑሮ
ውድነቱ ያልደረሰበት ቦታ የለም:: የችግሩ ዋነኛ
ገፈት ቀማሾች ደግሞ ዝቅተኛ እና ቋሚ ገቢ
ባላቸው በተለይ መንግሥታዊና መንግሥታዊ
ባልሆኑ ተቋማት ተቀጥረው የሚሠሩና የቀን
ሠራተኞች ናቸው::
ሐሳባቸውን ለበኩር ከሰጡን የባሕር ዳር
ከተማ ኗሪዎች መካከል ወ/ሮ ሊዲያ አስማማው
አንዷ ናቸው:: “ሁሉ ነገር ሰማይ ነካ:: የኑሮ
ውድነቱ ፈተነኝ” ይላሉ፤ በመንግሥት ሥራ
ተቀጥረው የሚተዳደሩት ነዋሪዋ 3 ሺህ 700
ብር በወር ተጣርቶ ይደርሳቸዋል:: ከዚህ
ውስጥ ሁለት ሺህ 500 ብር ለቤት ኪራይ
እንደሚከፍሉ ይናገራሉ። “ለቤት ኪራይ ከፍየ
እጄ ላይ የሚቀረው አንድ ሺህ 200 ብር ነው።
ሦስት ቤተሰበቼን በዚህ ብር ለማስተዳደር
ምኑን ከምን ላርገው? ይባስ ብሎም ሰሞኑን
የቤት ኪራይ 3500 ነው ተባልሁ” ብለዋል::
በመሆኑም ቤቱን በመልቀቅ ከሚሠሩበት ቦታ
ርቆ መሄድን የመጨረሻ አማራጭ አድርገዋል።
የችግሩን ከፍታም “መላው ጠፍቶብኝ እንጅ
ነገሩ ከባድ ነው። ከተከራየሁበት ቤቴ ዘይትም
ሽንኩርትም ገዝቼ ሰርቼ መብላት አቅቶኛል”
ሲሉ ነው የገለጹት፡፡ ዐይነስውርነታቸው ደግሞ
ሌላ ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡
ነዋሪዋ እንዳሉት የምርቶች ዋጋ እየጨመረ
የምርት ጥራትና አቅርቦት እየቀነሰ መጥቷል::
የመንግሥት ክትትልና ቁጥጥር በመዳከሙ
ነጋዴው በተጋነነ ዋጋ እየሸጠ ነው:: ከዚህ
በተጨማሪም ግጭት ከመቀስቀሱ በፊት በሸማች
ሕብረት ሥራ ማሕበር ይቀርብ የነበረው ምርት
ተቋርጠል::