ሕይወታቸው የተጎሳቆለ ሰዎች፣ የፈረሱ መኖሪያ ቤቶች፣ የወደሙ መሠረተ ልማቶች ለዩክሬን መለያ ሆነዋል። የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የዓለም ምጣኔ ሀብት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዳያገግም አድርጓል።
ዩክሬን ከምድር እና ከሰማይ የሚምዘገዘጉ የሩሲያ ሚሳይሎችን ውርጅብኝ በአንጻራዊነት ተቋቁማ እስከ ዛሬ መዝለቅ ብትችልም ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ሕይወት ነጥቋል። በሚሊዮኖች ሲፈናቀሉ የዩክሬን ከተሞች እና መሠረተ ልማቶች ወድመዋል። ለዚህ በምሥራቃዊ ዩክሬን ክራስኖሆሪቭካ ከተማ በሚገኝ የፈረሰ ሆስፒታል የሚኖሩት ወይዘሮ ምስክር ናቸው። ወይዘሮዋ ቫለንቲያ ሞዝጎቫ እንዳሉት ከጦርነቱ በፊት በላብራቶሪ ባለሙያነት ያገለግሉበት የነበረ ሆስፒታል በሩሲያ ከባድ መሣሪያዎች ድብደባ እንዳልነበረ ሆኗል።
ውጊያው በርትቶ ባልደረቦቻቸው ሲሸሹ ወይዘሮዋ ለ40 ዓመታት ገደማ ባገለገሉበት ሆስፒታል በጥበቃ ሠራተኝነት ተቀጠሩ። ቫለንቲያ ሞዝጎቫ የሚጠብቁት ሆስፒታል የተለያዩ ሕክምናዎች ይሰጥባቸው የነበሩ ክፍሎች ፈርሰዋል። እንዲህ አይነቶቹ ጥቃቶች ወይዘሮዋን እጅግ የሚያብሰለስሉ ናቸው ሲል ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል።
በዩክሬን ሆስፒታሎች፣ የመኖሪያ ሕንጻዎች፣ እንደ ባቡር ያሉ መጓጓዣዎች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የኃይል ማመንጪያዎች እና የንግድ ተቋማት ከሰማይ እና ከባሕር በሚምዘገዘጉት የሩሲያ ሚሳይሎች ለብርቱ ጉዳት ተዳርገዋል። ብዙዎቹም እንዳልነበሩ ሆነዋል::
የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ ያደረገው ሰነድ ላይ እንደሰፈረው ሩሲያ በጤና ተቋማት ላይ በፈጸመቻቸው 750 ጥቃቶች 101 ሰዎች ተገድለዋል። የዩክሬን የጤና ሚኒስትር አንድ ሺህ 200 የጤና ተቋማት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መውደማቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥ 173 ሆስፒታሎች ተመልሰው ሊጠገኑ በማይችሉበት ደረጃ የፈረሱ ናቸው።
ዩክሬን በለም ጥቁር አፈሯ “የአውሮፓ የዳቦ ቅርጫት” የሚል ስም የተጎናጸፈች ሀገር ናት። ዩክሬን በ2014 ዓ.ም 106 ሚሊዮን ቶን እህል አምርታ በሰኔ እና ሐምሌ ወራት ብቻ 43 ሚሊዮን ቶኑን በዓለም ገበያ ሸጣለች። ይህ ግን አልዘለቀም። የዩክሬን የጥቁር ባሕር ወደቦች አሁን ዝግ ናቸው፤ አሊያም ከዚህ ቀደም በነበረ አቅማቸው ልክ ወደ ሌላው ዓለም የሚጓጓዝ እህል ወደ መርከቦች አይጭኑም።
በርካታ ገበሬዎች እንዳሻቸው በእርሻ ማሳዎቻቸው ሥራዎቻቸውን ማከናወን አይችሉም ወይም ገበሬዎቹ ራሳቸው የውጊያው ተሳታፊ ሆነዋል። በዚህ ሳቢያ የተከተለው ዳፋ ታዲያ ባሕር እና ድንበር ተሻግሮ በዓለም ገበያ ሁሉ የታዬ ነው። በአውሮፓ የምግብ ዋስትና ጥያቄ ባይነሳም በጦርነቱ የተስተጓጎለው የኃይል አቅርቦት እና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የኑሮ ውድነትን አስከትሏል።
በዓለም ገበያ የታየው የእህል ዋጋ ውድነት 50 በመቶ ገደማ ምግባቸውን ከሩሲያ እና ከዩክሬን በሚሸምቱ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ሀገራት ብርቱ የምግብ ዋስትና ቀውስን አስከትሏል። ሱዳን ከዓለም ገበያ ከምትሸምተው ስንዴ 87 በመቶው በዩክሬን እና በሩሲያ የተመረተ ነው። ጎረቤቷ ግብጽ ባለፉ ሁለት ዓመታት ከሸመተችው ስንዴ 80 በመቶው አሁን ጦርነት የገጠሙት የሁለቱ ሀገሮች ገበሬዎች ያመረቱት ነበር።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ለተቸገሩ ሰዎች እርዳታ የሚያቀርበው የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር ግማሽ ያህል ሸቀጡን የሚሸምተው ከዩክሬን ነበር። ድርጅቱ “በዓለም ዙሪያ 125 ሚሊዮን ሰዎች ለመመገብ ከሚያስፈልገን እህል 50 በመቶውን የምንሸምተው ከዩክሬን ነበር። ለዓለም ገበያ የሚቀርበው 30 በመቶ ስንዴ፣ 20 በመቶ በቆሎ፣ 20 በመቶ የሱፍ አበባ ዘይት በዩክሬን እና በሩሲያ የሚመረት ነው። ስለዚህ በዓለም ዙሪያ አስከፊ ተጽዕኖ አሳድሯል” ሲሉ ተናግረዋል።
ጦርነቱ እንደተጀመረ በአሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት የሚመራው የምዕራባውያን ጥምረት በሩሲያ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ ያነጣጠሩ በርካታ ማዕቀቦችን እያከታተለ በመጣል ጫና ለማሳደር ሞክሯል። በዚህም ሳቢያ የሩሲያ መገበያያ ገንዘብ የሆነው ሩብል ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን ተዳከመ፤ የሀገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔውን በእጥፍ ሲያሳድግ የሞስኮ የአክሲዮን ገበያ ለቀናት ለመዘጋት ተገደደ።
የአውሮፓ ባለሥልጣናት ማዕቀቦቹ “ግዙፍ እና ኃይለኛ ተጽዕኖ” የሚያሳድሩ ለመሆናቸው እምነት ነበራቸው። የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎችም በማዕቀቦቹ ጫና የሩሲያ ምጣኔ ሀብት እንደሚያሽቆለቁል ጠብቀዋል፤ ወይም ተንብየዋል። ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በጥር 2015 ዓ.ም ይፋ ያደረገው ትንበያ የሩሲያ ምጣኔ ሀብት በዩክሬን ጦርነት እና ጦርነቱን ተከትሎ በተጣሉበት በርከት ያሉ ማዕቀቦች የገጠመውን ፈተና ተቋቁሞ መዝለቁን አሳይቷል። ድርጅቱ ቀደም ብሎ በጎርጎሮሳዊያን አቆጣጠር 2023 የሩሲያ ምጣኔ ሀብት በሁለት ነጥብ ሁለት በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል የሰጠውን ትንበያ ከልሶ እንዲያውም በዜሮ ነጥብ ሦስት በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ይፋ አድርጓል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት የነዳጅ እና ጋዝ ሺያጭ የሩሲያን ምጣኔ ሀብት ታድጓል።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን “ምዕራባውያኑ ጦራቸውን በማዝመት እና በመረጃ ብቻ ሳይሆን በምጣኔ ሀብት ግንባርም ዘመቻ ከፍተውብናል። ነገር ግን ምንም አላሳኩም፤ ወደፊትም ምንም አያሳኩም። ከዚህ በላይ ግን የማዕቀቦቹ አመንጪዎች በየሀገራቸው የዋጋ ንረት፣ የሥራ አጥነት፣ የንግድ መደብሮች መዘጋት እና የኃይል እጥረት ቀውስ በመፍጠር ራሳቸውን ቀጥተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች እንደሚሉት የሩሲያ ምጣኔ ሀብት ከተጠበቀው የተሻለ እንዲሆን ያደረጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ቀዳሚው ሀገሪቱ የምታመርተው ነዳጅ እና ጋዝ ነው። የአውሮፓ ኅብረት ካለፈው ዓመት አብዛኛዎቹን ወራት የሩሲያን ነዳጅ እና ጋዝ ሲሸምት የቆዬ ሲሆን የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መንግሥት ከወደ ቻይና እና ሕንድ አዳዲስ ደንበኞችን አግኝቷል። ማዕቀቦቹም ቢሆኑ ሩሲያ ክሬሚያን ከዩክሬን ከገነጠለችበት ከጎርጎሮሳዊያን 2014 ጀምሮ የተለማመደቻቸው ናቸው። ሩሲያ ከሕንድ እና ቻይና ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ ማጠናከሯ ደግሞ ማዕቀቦቹን ለመቋቋም ሁነኛ መንገድ ሆኗታል።
ሩሲያ ምጣኔ ሀብቷን ከከባድ ጉዳት ብትታደግም ሰብዓዊ ኪሳራ ግን እየገጠማት ይገኛል:: ገለልተኛ የሆነ አንድ የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን 50 ሺህ የሚሆኑ የሩሲያ ጦር አባላት፤ ሩሲያ ከሁለት ዓመት በፊት በሙሉ ኃይሏ ዩክሬንን ከወረረችበት ጊዜ አንስቶ መሞታቸውን እና አሃዙ ከዚህ በብዙ ዐሥር ሺህዎች ሊልቅ እንደሚችል አስታውቋል።
ሚዲያ ዞና የተሰኘው እና ከቢቢሲ የዜና አውታር ጋር በመሆን የሞቱ የሩሲያ ወታደሮችን አሃዝ የሚከታተለው ይህ የመገናኛ ብዙኃን ተቋም እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ ከጎሮጎርሳዊያኑ የካቲት 2022 አንስቶ 50,471 የሩሲያ ወታደሮች ህይወታቸው ማለፉን ገልጿል። ሚዲያ ዞና አክሎም በሩሲያ የወታደር ቤተሰቦች መካከል ከ85 ሺህ በላይ የሚሆኑ የውርስ ሽግግሮች መደረጋቸውን እና በተጨማሪም ሩሲያ በሳምንት አንድ ሺህ 200 ወታደሮችን እያጣች መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል።
የዩክሬን ወታደራዊ ኃይል 451,730 የሩሲያ ወታደሮች በሞት እና በጉዳት ተገልለዋል በማለት ያስታወቀ ሲሆን ይሁን እንጂ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ የደህንነት ተቋማት ሩሲያ 300 ሺህ ሞት እና ጉዳቶች ደርሶባታል ሲሉ አስታውቀዋል።
ሩሲያ የሞቱ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ወታደሮቿን አሃዝ እምብዛም በይፋ የማስታወቅ ልማድ የላትም። በሌላ በኩል ዩክሬን ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ 31,000 ወታደሮቼን አጥቻለሁ ብላለች። ይሁን እንጂ የሟቾች ቁጥር ከዚህ በብዙ እጥፍ እንደሚበልጥ ሩሲያ አስታውቃለች::
ዩክሬን ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ጦሱ እዚያው የሚያበቃ አይደለም። የተለያዩ የዓለም ክፍሎችን መንካቱ ስለማይቀር የአፍሪካ ሀገራትንም በተለያየ ሁኔታ ይመለከታቸዋል። የአፍሪካ ሀገራት ከሩሲያ እና ከዩክሬን ጋር ምጣኔ ሀብታዊ እና ወታደራዊ ግንኙነቶች ስላላቸው ጦርነቱ የሚያስከትልባቸው ጫና ይኖራል። በተለይ ደግሞ ሩሲያ ምዕራባዊያን የአፍሪካ መንግሥታት ከጎናቸው እንዲቆሙ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ማሳደራቸው አይቀርም።
እስካሁን ጦርነቱን በተመለከተ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ጋና እና ጋቦን ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ዘመቻ አውግዘው በይፋ ተቃውመዋል። አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ግን ዝምታን የመረጡ ሲሆን፣ በይፋ ወጥቶ ከሩሲያ ጎን በመቆም ድጋፉን የገለጸም የለም። ነገር ግን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጎሎ (ሔሜቲ) ጦርነቱ በተጀመረበት ዕለት ለጉብኝት ሞስኮ ገብተዋል።
የጄነራሉ ጉብኝት በሱዳን መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶ በሀገሪቱ የተጀመረው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር መቀልበሱን ተከትሎ ምዕራባውያን በሱዳን ወታደራዊ መሪዎች ላይ ፊታቸውን በማዞራቸው ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር መሆኑ ተገልጿል።
በተለይ የሕክምና ትምህርትን በዝቅተኛ ክፍያ ለመማር የሚፈልጉ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ዩክሬን ውስጥ ያሉ ሲሆን ሌሎች አፍሪካውያን ደግሞ ለሥራ እና ለኑሮ እዚያው ይገኛሉ። ጦርነቱ ሲቀሰቀስ ግን ደኅንነታቸው አሳሳቢ ሆኗል። ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለትምህርት ዩክሬን የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች አሉ። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪ ያላቸው ሀገራት ሞሮኮ (ስምንት ሺህ)፣ ናይጄሪያ (አራት ሺህ) እና ግብፅ (ሦስት ሺህ 500) ሲሆኑ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችም ዩክሬን ውስጥ እንደሚገኙ ቢቢሲ አረጋግጧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን ኤፍ 16 ዘመናዊ ተዋጊ ጀቶችን ከአሜሪካ አግኝታለች:: በዚህም ዩክሬን ጥቁር ባሕር ከተሰኘው የክሬሚያ ይዞታ ሩሲያ እንድትወጣ አስገድዷታል:: ይህን ተከትሎ ሩሲያ ከሦስት መቶ በላይ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እና ከ20 ሺህ በላይ በሚሆኑ ወታደሮች በጥቁር ባሕር እና በአዞቭ ባሕር ከፍተኛ የተባለ ጥቃት እንድትከፍት አድርጓታል::
አሜሪካ እና ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን የሚያደርጉት ወታደራዊ ድጋፍ በጨመረ ቁጥር ሩሲያ ተጨማሪ የሰው ኃይል እና የጦር መሣሪያ በጦርነቱ እንድትጠቀም ሲያደርጋት ይስተዋላል:: ሩሲያ በባሕር ላይ እንዲሁም በመሬት የኒውክሌር ጥቃት ልምምዶችን እያደረገች መሆኑን ታስ የተሰኘው የሩሲያ የሀገር ውስጥ መገናኛ አውታር ዘግቧል:: ጉዳዩ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ሩሲያ እንደምትዝተው የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ልትጠቀም ትችላለች የሚል ስጋት በዓለም ላይ በተለይ በኔቶ አባል ሀገራት ላይ ፈጥሯል::
ሁለት ዓመታትን የተሻገረው ጦርነት ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፤ ይህን ተከትሎም ኃያላን ሀገራትን ከሁለት ጎራ ከፍሏቸዋል:: አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባዊን ያልተገደበ ድጋፋቸውን ለዩክሬን እየለገሱ ይገኛሉ::
ይህን ተከትሎም የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ኒውክሌር ልትጠቀም እንደምትችል በተደጋጋሚ ዝተዋል፤ ምዕራባዊያን የማያርፉ ከሆነ “አይቀጡ ቅጣት ይጠብቃቸዋል” ነው ያሉት:: ከዚህ በተጨማሪም ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ እና ከቻይና ጋር ተደጋጋሚ ሙሉ የጦር ልምምድ ስታደርግ ቆይታለች::
በተያያዘ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ በካርኪቭ ግዛት ተገኝተው የኪዬቭ ልዩ ኃይሎችን ጎብኝተዋል:: የኪዬቭ ኃይሎች ከፑቲን ወታደሮች ጋር መራራ የተባለለትን ጦርነት ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ እያካሄዱም ይገኛል::
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም