የንግግራችን ጉዳይ !

0
135

የህዳር  2 ቀን 2017 ዓ.ም

ንግግር/ወግ/ ከጀመረ መቋጫ የሌለው፤ ለማንም እድል ሳይሰጥ ስለሁሉም ነገር አዋቂ ነኝ ባይ፤ አንድ ጎረቤት ነበረኝ። ታዲያ ሁሉም የአካባቢያችን ነዋሪ ከዚህ ሰው ጋር የሚደረግ ንግግርን በእጅጉ ይጠላል። እንዲያውም ገና ከርቀት እሱን የተመለከተ በሽሽት ማምለጥን ይመርጣል። እንዲያው ፊት ለፊት ተገናኝተው ወግ ከጀመረ ግን ማብቂያውን ፈጣሪ እንዲሰጠው ይመኛሉ። በዚህ የተነሳ አብሮት ያለን ሰው የሰፈሩ ነዋሪ “ዛሬ እትና ታስሯል” ይላል። ንግግሩ መቋጫ በሌለው ግለሰብ ተይዟል ለማለት ነው።
አንድ ዕለት ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ብርቱ ቀጠሮ ነበረን፤ እናም ከቤቴ ሳልወጣ ቁጭ ብዬ መጠባበቅ ጀመርኩ። 6:30 እደርሳለሁ ያለኝ ጓደኛዬ እስከ 7:30 ዘገዬ። ምን ሆኖት ዘገዬ ብዬ አሰብኩ። ምክንያቱም ይህ ጓደኛዬ በቀጠሮ የሚታማ አይደለም። በ8:45 የግቢው በር ተንኳኳ፤ ሲከፈትም የዘገየው ጓደኛዬ ዘው ብሎ ገባ። “ሳት ለብሶ ሳት ጎርሶ” እንዲሉ በእጅጉ ተናዶ ነበር። ምን ነው! ምን ገጠመህ? ብዬ ጥያቄ አቀረብኩ። “ተወኝ እባክህ! ታስሬ ነው” አለኝ። በምን ምክንያት? የት? ስለው “እዚሁ! አንተ በር” ብሎኝ እርፍ። እንዴት? “ጋሽ እትና አግኝቶ በወሬ ጠመደኝ። ይሉኝታ ይዞኝ ሳዳምጥ፤ የቆጥ የባጡን እያወራ ከአንድ ሰዓት በላይ አስሮ አቀየኝ” ብሎ አወጋኝ። … ይህ ብቻ አይደለም፤ ንግግር ከጀመረ መቋጫ ከሌለው ከዚህ ጎረቤታችን ጋር በተያያዘ ብዙ ገጠመኞችን ማንሳት ይቻላል። ነገር ግን የዚህ ፅሑፍ ዐብይ ትኩረት ባለመሆኑ በዚሁ ለመግታት ወሰንኩ። ይህን ግለሰብ መነሻ ለማድረግ የወሰንኩት ግን ያለአግባብ አለመሆኑን ልብ ይሏል። በዚህ የዛሬው የግል ሃሳብ ፅሑፌ ንግግራችን/ወጋችን/ ቀደም ሲል የነበረውን ለዛ በጥቂቱ ለማስታወስ እሞክራለሁ፤ አሁን የደረሰበትን ጉዳይም በሰፊው እዳስሳለሁ። በመግቢያነት ያነሳሁት ሃሳብም ለአሁኑ ንግግራችን አንዱ መገለጫ ነው።
የቀደመው ንግግራችን
እንዲህ እንደዛሬው ፈሩን ባልሳተበት ዘመን ንግግራችን ሁሉ መከባበርን መሰረት ያደረገ ነበር። ትልቅ/በእድሜ የሚበልጥ/ ሰው ባለበት ቦታ በእድሜ ትንሽ የሆነ ቀድሞ የማይናገርበት፤ የሚደረገው ንግግርም የእድሜ ደረጃን ያማከለ ርዕስ ላይ የተመሰረተ ነበር። የተገኘው ወሬ ሁሉ እየተቃረመ በእድሜ ለገፋውም ሆነ ለጎረምሳው አልያም ለህፃናት በጅምላ የሚደረግ ንግግር አልነበረም። ይህም በመሆኑ የሚነሳው ርዕሰ ጉዳይ መለያያ ሳይሆን መከባበሪያ እና አስተማሪ ነበር።
“በአፍ ይጠፉ፤ በለፈለፉ” በሚል የሚነገር የቆየ አባባል አለን። ከፍ ያለ መልዕክትንም ይዟል። በማይመለከት አልያም ተጨባጭ ባልሆነ ነገር ላይ ተመስርቶ መዘባረቅ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የከፋ መሆኑንም ቁልጭ አድርጎ ያስገነዝባል።
ከቀደመው ወርቃማ ንግግራችን መገለጫዎች መካከልም የሚተላለፉ መልዕክቶች አይረሴነት አንዱ ነው። ምክንያቱ ደግሞ እንደዛሬው ተናጋሪ የጀመረውን ሳይጨርስ፤ ካንተ ይልቅ እኔ አውቃለሁ በሚል ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት የሚደረግበት፤ አልያም ጣልቃ ተገብቶ ንግግሩ የሚቋረጥበት ሁኔታ አልነበረም። ተረኛው ሲናገር አድማጩ በወጉ ይከታተላል፤ መልስ የሚሰጠው ከሆነም ተራውን ጠብቆ ይቀጥላል። በተለይ በእድሜ የገፉ ሰዎች ተደማጭነታቸውም ሆነ የንግግር ለዛቸው በእጅጉ የተዋበ ነበር። በዚህም የተነሳ “አያቴ እንደነገሩኝ” እያልን አንዳንዱን ሃሳብ እያዋዛን ለዛሬው ንግግራችን እርሾ አድርገን እየተጠቀምንበት ነው።

የአሁኑ ንግግራችን
አንድ ዕለት የምሽት ሃይማኖታዊ ትምህርት መርሃግብር ለመሳተፍ በባህርዳር ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ተገኘሁ። በዚያን ዕለት ያስተማሩት ሰባኪ ያስተላለፉት መልዕክት ዛሬ ድረስ ከህሊናዬ አልጠፋም። እንዲህ አሉ “… እንዲያውም አሁንማ ንግግራችን ሁሉ ፈሩን እየሳተ ነው። ሰላምታ ልውውጣችን ደግሞ ለዚህ አይነተኛ መገለጫ ይሆናል። ቀደም ባሉት ጊዜያት ‘ደህና አደርህ፤ አልያም ደህና ዋልህ’ ሲባል መላሹ ‘ፈጣሪ ይመስገን፤ በጣም ደህና ነኝ! እና … ሌላም ሌላም በማለት ምላሽ ይሰጥ ነበር። አሁን ግን ያ! ባለለዛው የሰላምታ ልውውጥ ተለውጧል። ‘ጠፋህ? አዎ! ጠፋሁ፤ ተጠፋፋን’ ሆኗል። ልብ በሉ! እየጠፋን መሆኑን ለዛ ባጣው የሰላምታ ልውውጥ ንግግራችን ብልሽት አየተገለጸ ነው” በማለት አስተማሩ። አዎ! የንግግራችን ብልሽት ከሰላምታ ልውውጣችን ጀምሮ መሆኑን ከሰባኪው ንግግር በአግባቡ መገንዘብ በቂ ነው።
ለዛሬው የትዝብት ፅሑፌ ዋናው መነሻ የአሁኑ ንግግራችን ጉዳይ ነው። በእኔ እምነት አሁን ላይ ንግግራችን ፈሩን ስቷል። ለዚህም መገለጫ ያልኋቸውን አንኳር ነጥቦች እጠቃቅሳለሁ።
ከሁሉም በላይ የዘመኑ ንግግር ግብረገብነት ጎሎታል፤ የቀደመ ለዛውንም አጥቷል። መከባበር ብሎ ነገር በዛሬው ንግግራችን በጭራሽ አይስተዋልም።
ከዚህ ይልቅ ሁሉንም ነገር አውቃለሁ ባዩ በርክቷል። እድሜን፣ ቦታን፣ ርዕሰ ጉዳይን እና ወቅትን መሰረት ሳያደርግ የተሰማው ነገር ሁሉ በተገኘው ቦታ ይወራል፤ ይተነተናል።
ለንግግራችን ፈር መሳት ማህበራዊ ሚዲያ አንዱ ምክንያት ሆኗል። ሳንመርጥ እንሰማለን፤ እንዴት? እና ለምን ሆነ? ብለን የወሬውን መነሻ ምክንያት አንመረምርም፤ ዝም ብለን እናዳምጣለን። የኛ መሳት አልበቃ ብሎም፤ ተባለ በሚል ያልተረጋገጠ ወሬን በንግግራችን ሌሎች ላይ እንዘራለን።
ባልተረጋገጠ መረጃ እኛ ተደናግረን ለሌሎችምን ግራ ማጋባታችን አላዋቂነት ነው። የሁሉም ነገር ተንታኝ መሆን እንደማይቻል ማውቁ ግን የአዋቂነት መገለጫ መሆኑን መገንዘብ ተገቢነት አለው።
ተጨባጭ ያልሆነ ወሬን ከመንዛት ባለፈ ደግሞ የዘመኑን ንግግር የከፋ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የኔ ሃሳብ ብቻ ትክክለኛ ነው በሚል የሌሎችን ሃሳብ ለማድመጥ እና ለመቀበል አለመቻላችን ነው።
ሁሉም ሰው በአቅሙ እና በልኩ የሚያምንበት የራሱ የሆነ ሃሳብ አለው። ትክክለኛ ነው ወይንም አይደለም የሚለው ግን በመግባባት ላይ በሚመሰረት ውይይት የሚረጋገጥ እንጂ፤ የኔ ነው ትክክል በሚል ረብ የለሽ ድንፋታ አለመሆኑንም መገንዘብ ተገቢ ነው።
ባልገባን ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተመስርተን የምናደርገው ውይይትም አሁን ለደረስንበት ግራ መጋባት አንዱ መገለጫ ነው። ለዚህስ አንድ የቅርብ ገጠመኘን አብነት ላንሳ፤ አምስት ሰዎች ሰብሰብ ብለው የጀመሩት ንግግርን እኔም ስድስተኛ ሁኜ ተቀላቀልኩ። ከአምስቱ አንደኛው እኔ ነኝ አዋቂ በሚል ለቀሪዎቹ በተለያዬ ርዕስ ላይ ትንታኔ ያቀርባል። የሚለውን በአትኩሮት እዲያደምጡ እና እንዲቀበሉት ያስገድዳል።
የሁለም ነገር አዋቂ ሆኖ ፋታ ሳይሰጥ ንግግሩን ቀጠለ። በመሃል ላይ አንዱ “ይህን ደግሞ ማነው ያለ” ብሎ ጥያቄ አቀረበ። በንግግሬ መሃል ለምን ገባህ በሚል ሁኔታ “ሚዲያ ስለማትከታተል ነው ይህን የጠየቅህ! ትናንት የተወካዮች ምክር ቤት ላይ ነው የተነገረ” ብሎ እርፍ። በወረሃ መስከረም፤ ምክር ቤቱ ስራ ላይ በሌለበት። በዚህ ጌዜ አላስችለኝ ብሎ ይህን እውነታ ላስረዳ ሞከርኩ፤ ያ የሁሉ ነገር አዋቂ ነኝ ባይ እና ተንታኝ ግን አውነታውን መቀበል እሬት ሆነበት። ከዚህ አይነቱ ሰው ጋር ንግግርን መቀጠል ጉንጭ ማልፋት ነው ብዬ ከዚያ ረብ የለሽ የንትርክ መድረክ ራሴን አገለልኩ። ታዲያ ከዚህ በላይ ለንግግራችን ፈር መሳት ምን አብነት መጥቀስ ያሻል? አንዲያው በጥቅሉ ንግግራችን በጠና ታሟልና ወደቀደመው ለዛው አንዲመለስ የሁላችንንም ጥረት ይሻል እላለሁ።

ንግግራችን ምን ይምሰል?
የንግግራችን ህመም ተባብሶ እየተደናገርን ለከፋ ጉዳት እንዳንዳረግ፤ የትምህርት ስርዓታችን ቢመለከተው መልካም ይሆናል። ከዚህም በላይ በመልካም ስነምግባር የታነጸ ትውልድ እንዲኖር ወላጅ እና ቤተሰብ በመልካም ንግግር ግንባታ ላይ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ “ጦር ከፈታው፤ ወሬ የፈታው” የሚለወን አጢነን ንግግራችን ትክክለኛ መረጃ እና ማስረጃ ላይ የተመሠረተ ይሁን። የኔ ሃሳብ ይህ ነዉ! እናንተስ ምን ትላላችሁ? ቸር ይግጠመን።

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here