ከውይይት፣ ከንግግር፣ ከድርድር፣ ከሙግት፣ ከመደማመጥ፣ ከትንተና፣ ከቢሆናዊ
ሐሳቦች የራቀ ፖለቲካ ሾተላይ መሆኑ አይቀሬ ነው። ሾተላይ ፖለቲካ የፀና ሀገረ መንግሥት
እና ማህበራዊ ሰላምን ለማስፈን ዕድል የለውም። በበርካታ ሀገራት እንደተሞከረው የፀና ሀገረ
መንግሥት የቆመው በአካታች ውይይት፣ በሀቀኛ ፖለቲካዊ ንግግር፣ በፍትሓዊ አስተዳድር እና
በሕግ የበላይነት መሆኑ ግልፅ ነው።
አሁን ላይ በክልላችን ብሎም በሀገራችን ስጋቶች፣ ግጭቶች፣ ጦርነቶች ፣ የተካረሩ ፍረጃዎች
የሰርክ ዜና ሆነዋል። ይህም ማህበራዊ ሰላምን ክፉኛ በማናጋቱ መስራት ቀርቶ የመኖር ዋስትና
ለማግኘት አዳጋች ሆኗል። ታሞ ለመታከም፣ ሸምቶም -ሽጦም ለመኖር፣ ስለነገ ለማለም አሁን
የተፈጠረው ውስብስብ ቀውስ አዳጋች አድርጎታል። እንደዚህ አይነት ቀውስ በተፈጠረ ጊዜ
ሁነኛው መፍትሄ ሀቀኛ ውይይት እና ድርድር መሆኑ ግልፅ ነው። በዕርስ በዕርስ ጦርነት አሸናፊ
ሳይሆን የጋራ ተሸናፊነት ይረጋገጥ ካልሆነ፣ ሌላ የሚያመጣው በረከት የለም። የዕርስ በዕርስ
ጦርነት የራስን ጥሪት እና ክቡር የሰው ሕይዎት ከራስ ጋር በማበላላት የሚደረግ የጥፋት ስምሪት
በመሆኑ አሸናፊም ተሸናፊም የለውም። “የሞተው ወንድምሽ፣ የገደለው ባልሽ” እንደሚባለው
ገዳይም ሟችም የአንድ ሀገር ዜጎች፣ የሚጠፋው ንብረትም የአንድ ሀገር እሴት ነው።
ይህ ውስብስብ ቀውስ የበለጠ እየተወሳሰበ ሞራላዊ፣ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ ታሪካዊ እና ዘላቂ
ችግርንም እየፈለፈለ እንዳይሄድ ተኩስ ቆሞ እውነተኛ ውይይት፣ ንግግር፣ ድርድር እንዲደረግ
ማመቻቸት ፖለቲካዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ ጉዳይ ነው። በዕርስ በዕርስ ጦርነት ፍፁም
አሸናፊ ሀይል ይኖራል ማለት መሬትን በሳሙና አጥቦ ከጭቃ እንደማፅዳት አይነት ከባድ ጉዳይ
በመሆኑ ከአፈሙዝ ይልቅ ሀቀኛ ውይይት፣ ከመፈራረጅ ይልቅ በግልፀኝነት መሞጋገት፣ በጦር
ከመፋለም ይልቅ በጠረጴዛ ዙርያ መደራደርን ማስቀደም የግድ ይላል። ለዚህ ደግሞ ፖለቲካዊ
ሾተላይ ሆኖ የሕዝብን ጥያቄ ሳይመልስ እንዳይቀር ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እና ማሻሻያዎች በእጅጉ
አስፈላጊ የሰላም መፍጠሪያ አላባዎች ናቸው። አፈሙዝ ተዘቅዝቆ ብዕር እና ወረቀት ከፍ እንዲል
ከሴራ ትንተና፣ ከፍረጃ እና ከጦርነት ቅስቀሳ የራቀ የሰላም ጥሪ ይደረግ። ቁራዎች ሳይሆኑ
እርግቦች በየመንደራችን እንዲበሩ የፖለቲካ አየሩ ጤናማ፣ ሀቀኛ፣ ፍትሐዊነትን የሚያረጋግጥ
መሆን ይኖርበታል።