ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም
አረፈ ዓይኔ ሓጎስ አለቃ ገብረ ሀና እና ስራዎቻቸውን በሚመለከት ታሪካቸውን ሰንዶ መጽሐፍ አዘጋጅቷል:: አለቃ ገብረ ሀና፤ ተጫዋች እና ቧልተኛ፣ ጥበበኛ እና አዋቂ፣ ሊቅ እና አሳቢ ሆነው በታሪካቸው ውስጥ ይታያሉ::እንዲያውም አለቃ ሁለት ዓይነት ሰብዕና ያላቸው ሆነው ይታያሉ:: ቅኔ አዋቂ ሊቅ ብለናቸው ሳናበቃ ደግሞ ዋዛ ፈዛዛ የሚወዱ በቃላት በመተረብ አልባሌ ጨዋታ ላይ የሚያተኩሩ ሰው ሆነው እናስተውላለን::
አለቃ ሁለት መልኮች አሏቸው:: አንዱ የበቀሉበት እና ያደጉበት መንፈሳዊው ነው:: ሁለተኛው ደግሞ ዓለማዊው እና ቧልት የበዛበት ሕይወታቸው ነው:: አለቃ ገብረ ሀና ደስታ በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ናበጋ ጊዮርጊስ በተባለ ቦታ በ1814 ዓ.ም ነው የተወለዱ። ታሪካቸው እንደሚያስረዳው አለቃ ገብረ ሀና የቋንቋ ሊቅ፣ የፍትሐ ነገስት አዋቂ፣ የተክሌ ዝማሜ ቀማሪ እና የሌሎች እምቅ ክህሎቶች ሁሉ ባለቤት ናቸው።
ከተወለዱበት ጎንደር ተነስተው ጎጃም ተሻግረዋል፤ቅኔም ተምረዋል። በኋላም ወደ ጎንደር ተመልሰው ከመምሕራን ዜማን፤ ከባሕታዊያን አቋቋምን፤ እንዲሁም ሌሎች ትርጓሜ መጻሕፍት፤ ፍትሐ ነገሥትና የያሬድን ድጓ ጠንቅቀው ተምረዋል። በዚሕ እውቀታቸው ምክንያትም በ26 ዓመታቸው በጎንደር በሊቀ ካሕንነት ተሾመው ለሰባት ዓመታት ያሕል አገልግለዋል።
አለቃ ቧልት አዋቂ፤ ተረበኛ፤ በቃላት መጫዎት የሚችሉ በ1840 ዎች አካባቢ ጎልተው የወጡ እስከ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ድረስ የዘለቁ ሊቅ ናቸው። የአጼ ቴዎድሮስ፤ የአጼ ዮሐንስና የአጼ ምኒልክ ፍትሐ ነገሥት አዋቂና ዳኛ ሆነው አገልግለዋል። የድጓ፤ የአቡሻኸርና የመርኀ እውር ሊቅ፤ የአቋቋም አዋቂ፤ የፍትሐ ነገሥት ሊቅም እንደነበሩ ይነገርላቸዋል:: አለቃ ቀልድ የሸፈናቸው ብዙ ዕውቀትና ትምህርት ያላቸው የዘመኑ ሊቅ ናቸው በማለት የየዘመኑ ሊቃውንት ይናገሩላቸዋል።
ዛሬ በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሚያደገለግለውን ተክሌ አቋቋም ደርሰው ለትውልድ ያስተላለፉ ሊቅ እያሉ ጎልቶ የሚጠቀስላቸው ቀልድና ተረባቸው ነው። ባላቸው እውቀት ልክ ያልሰሩ፤ ያላቸውን እውቀት ያልተጠቀሙበት የባከኑ ሊቅም ሆነው ለብዙዎች ይታያሉ:: ከቅኔያቸው ይልቅ ጎልቶ የሚጠቀስላቸው ዋዛ ፈዛዛ እና ጨዋታቸው ነው::አለቃ ገብረ ሀና አራት ልጆችን ወልደው በ84 ዓመታቸው የካቲት 24 ቀን 1898 ዓመተ ምሕረት ጎንደር ውስጥ አርፈዋል።
ዛሬም እነዚህን ቀልዶቻቸውን ዞር እያልን በ አሉ ተባሉ እና በሰነድም ጭምር ስናገኛቸው ሳቅን ፈጥረው ዘና ያደርጉናል:: አለቃ ብልህ፣ ተረበኛ እና ጥርስ አያስከድኔ ሰው ነበሩ::አለቃ በቃላት ነው ጨዋታቸው:: ሰም እና ወርቅ ምስጢር ያላቸው ቃላትን በጨዋታቸው መሐል ጣል በማድረግ ይናገራሉ:: በ26 ዓመታቸው ጎንደር ውስጥ ሊቀ ካህን ተደርገው ተሾሙ::
አንድ ቀን አንዲት ሴት ጠበል ይቅመሱ ብላ ትጠራቸዋለች:: ወደ ጥሪው ቤት እየገሰገሱም ሳለ ከጠበሉ ቤት የሚወጡት ሰዎች ጠላው ግም ነው እያሉ ሲወጡ አለቃ ይሰማሉ:: ተመልሰውም ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ:: አለቃ በመቅረታቸው ያዘነችው ሴትም አለቃ ምነው ጠበል ጠርቼዎት የቀሩ ብላ ወደ ቤታቸው ሔዳ ትወቅሳቸዋለች:: “ኧረ መጥቼ ሰው ግም ግም” ሲል ጊዜ ነው የተመለስኩት” ብለው ቤትሽ በሰው ሞልቶብኝ መቀመጫ አጥቼ ተመለስሁ የሚመስል መልስ ሰጧት ይባላል::
አለቃ በቁመት አጭር መልከ ቀና እና ድምጸ መልካም፤ እግራቸው ደግሞ ሸፋፋ ነበር ይባላል:: አንድ የሚጠሉት መልከ ጥፉ ቄስ ነበር አሉ:: ቄሱም የአለቃን ሸፋፋነት ያውቅ ነበርና “አባ ሽፍን ጫማ በሸዋ በኩል መጥቷል ይባላል እና እንዳያመልጥዎ” ሲል ያሽሟጥጥባቸዋል:: በነገር የማይቀደሙት አለቃም “አንተ ፊት ግዛና” ብለው ኩምሽሽ አደረጉት:: በጎንደር ባህል መጠጥ ሲጠጣ ጎድሎ መታየት የለበትም:: አሳላፊው አሁንም አሁንም እየመጣ ከብርሌው አንገት “ፉት” እንዳሉት ሞልቶባቸው ይሄዳል:: አለቃ በዚህ አልተደሰቱም:: ከድግሱ ቤት ሲወጡ አንዱ አለቃ ስንት ብርሌ ጠጅ ጠጡ ብሎ ይጠይቃቸዋል:: በቅሬታ ስሜት “ዘጠኝ አንገት ጠጣሁ” አሉት::
የካቲት 5 ቀን 1947 አጼ ቴዎድሮስ ነጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ሲሾሙ አለቃ ገብረ ሀናን በቤተመንግሥት አገኗቸው:: የአለቃን ምሁርነት እና አዋቂነት የሚወዱት ንጉሡ በሌላ በኩል ቀልድ እና ፌዝን አልወደዱም:: አለቃ ተው ይህን ቀልድህን እያሉ ያስጠነቅቋቸውም ነበር:: አለቃም ቀልድ እና ምጽት አብሯቸው ያደገ ነውና ሊተውት አልቻሉም:: ብላታ አድጎ የሚባል የአጼ ቴዎድሮስ አሽከር ነበር:: አለቃ ይህንን ሰው “ብላታ አህዮ” እያሉ ይጠሩት ነበር:: ንጉሡ ይቆጣሉ:: “ታዲያ አባቱ ያወጣለትን ስም ምን ላድርግ፡ በግእዝ አድግ ማለት አህያ ማት ነው” ብለው አለቃ ይመልሳሉ:: አለቃ መኳንንቱን ሁሉ በነገር እየሸነቆጡ ሲያስቸግሩ ነጉሡ ቴዎድሮስ “ገብረ ሀና ፍትሐ ነገሥቱን ጻፍ፣ ፍርድም ስጥ፣ ገንዘብም ያውልሕ፣ ቀልድህን ግን ተወኝ፣ ተው ተመከር” ብለው ተግሳጽ ሰጧቸው::
ጥቅምት 25 ቀን 1882 ዓ.ም አጼ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ነገሡ:: በዚህ ጊዜ አለቃ ገብረ ሀና ጎንደር የሚገኘው የአቡነ ሐራ ገዳም አስተዳዳሪ ሆነው ይሰሩ ነበር:: ጥቂት ዓመታት እንደሰሩ በአካባቢው ድርቅ ገብቶ ሕዝቡ ተራበ:: አለቃ ከተሰበሰበው የስለት ገንዘብ አንድ ሺህ ያህሉን ለካህናቱ እና ለባላገሩ አከፋፈሉት:: ወዲያውም ካህናቱ አለቃን አዲስ አበባ አፈ ንጉስ ነሲቡ ዘንድ ከሰሷቸው:: አለቃ ተከሰው አዲስ አበባ ተጠሩ:: ገንዘቡን ለምን እንዳጠፉት ሲጠየቁም “በርግጥ ለነዳያን የሚሠጠውን አውጥቼ ሰጥቸዋለሁ፤ ለመስዋእት የሚውለውንም እንዲሁ:: የተረፈውን ግን ፍትሐ ነገሥቱ በሚያዘው መሰረት ለማህበሩ ሰጥቼ ተካፍለውታል” ብለው መለሱ:: “እንግዲያውስ ያጠፉትን ገንዘብ መክፈልዎ አይቀርም” አሏቸው አፈ ንጉስ ነሲቡ:: “ታዲያ እኔ ገብረ ሀና ምን ይመጣብኛል ብለው ነው? እንደ ምጥዋ እቃ በነሲብ አልሸጥ” ሲሏቸው አፈንጉሡ በደም ፍላት እንዲታሰሩ አዘዙ:: አለቃ ወደ ምኒልክ ችሎት ቀረቡ:: “ጌታ አባ ገብረ ሀና ፍትሐነገሥቱን አዋቂ አልነበሩምን? ምን ነካዎ? በማለት ምኒልክ ጠየቋቸው:: “ክፉ ቀን ቢሆን ለሕዝቡ አካፈልኳቸው:: አቡነሐራ እንደሁ አባታቸውን አይጦሩበት፣ ልጃቸውን አይድሩበት፣ ታዲያ ገንዘቡ ተቀምጦ ምን ይሆናል ብየ ነው ጃንሆይ” ሲሉ አብራሩ:: “አበጀህ ቀድሞውንስ የተማርክ አይደለህ” ብለው ምኒልክ በነጻ ለቀቋቸው::
አንድ ቀን በጎንደር ከተማ ሁለት ሴቶች ውኃ በእንስራ ተሸክመው በዳገት ሲወጡ አንደኛዋ ፈሷ ያመልጣታል:: አለቃም ከኋላ ነበሩና እየሳቁ ሲከተሉ ድጋሚ ፈስ ሲያመልጥ ሰሙ:: አንደኛዋ ሴት ደንግጣ ሰው መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ዘወር ብትል አለቃ ከጀርባዋ አሉ::
“ውይ አፈር በበላሁ! አባ መቼ መጡ?” ብላ ብትጠይቃቸው “በታሳስ ሄጅ በጠር መጣሁ” ብለው መለሱላት ይባላል:: አንድ ቀን እንዲሁ አለቃ ወደ ትውልድ መንደራቸው ናበጋ ተመልሰው መኖር ይጀምራሉ:: የጥምቀት ድግስ ለመብላት ወደ ሩቅ ዘመዳቸው በታንኳ ተሳፍረው ሄዱ:: ጣናን ተሻግረው እንደደረሱም ሙክት ታርዶ ጠላው ተቀድቶ ቀረበ:: አለቃ ጠላ እና ወጡን ሲቀምሱ የማይረባ ይሆንባቸዋል:: “ይብሉ ይጠጡ እንጂ አባ ለምን ችላ ይላሉ ?” ስትል ባልቴቷ ትጋብዛቸዋለች:: አለቃም “ኧረ እበላለሁ እጠጣለሁ፣ ይሕማ የመጣሁበት አይደል” በማለት ወጡም ጠላውም ተሻግሬው እንደመጣሁት ጣና ሐይቅ የቀጠነ ነው ብለው በጥበብ ተናገሩ::
አለቃ መንገድ ውለው ደክሟቸው አንዲት ዋንጫ ጠላ እንደ ጠጡ እንቅልፍ ይወስዳቸዋል::መንፈቀ ሌሊት አካባቢ አህያቸው ቡሊ ጩኸቱን ይለቀዋል:: አለቃ ባልሰማ እንቅልፋቸውን ተኙ:: ሚስታቸው ማዘንጊያ “ኧረ እባክዎ ይነሱ ቡሊን ጂብ ሊበላው ነው ያስጥሉት” እያሉ ወተወቷቸው:: “ተይኝ ማዘንጊያ እፈራለሁ” አሉ አለቃ:: ማዘንጊያ ተበሳጭተው “ለስሙ ነዋ ያንጠለጠሉት” ቢሏቸው “አየ ማዘንጊያ በሱማ ቡሊ አይበልጠኝም ብለሽ ነው” ብለው ተኙ::
በትዳር ዓለም ውስጥ ውለው ሲያድሩ አለቃ ሠራኛቸውን መወስለት ጀመሩ:: አንድ ቀን ሌሊት ሰራተኛቸው ጋር ተገኛኝተው ሲመለሱ ማዘንጊያ ነቅተው ነበርና “ወዴት ሄዱ አንቱ?” ቢሏቸው ውዳሴ ማርያም ልደግም ተነስቼ ነበር ብለው መለሱላቸው:: “ታዲያ ራቁትዎን ነው እንዴ የሚደግሙት” ማዘንጊያ ይጠይቃሉ:: አለቃም “ኧረ ራቁቴን ሆኜ በሰማችኝም ጥሩ ነበር” ብለው መለሱ:: ይህን ስርቆሽ አለቃ መደጋገም ይጀምራሉ:: ማዘንጊያ አድፍጠው ኩራዝ አጥፍተው ይከታተሉ ነበር:: ደርሰው ሲመለሱ ማዘንጊያ አለቃን በደረቅ ፍልጥ ይወግሯቸዋል:: አለቃም ያልተመቱ መስለው አልጋቸው ላይ ይወጡ እና “ምንድን ነው የወገርሽው ማዘንጊያ?” ሲሉ ቢጠይቋቸው “ኧረ ጥጃ መሳይ ነው መሰለኝ” አሏቸው:: አለቃም ዱላው ከንክኗቸው “ታዲያ ለድርቅ ጥጃ ውስ መች አነሰውና ነው በፍልጥ የመታሽው?” በማለት ለማዘንጊያ ጀርባቸውን ሰጥተዋቸው አደሩ:: ወይዘሮ ማዘንጊያ ረጅም መልከ መልካም ሴት ነበሩ ይባላል:: አለቃም በፍልጥ የተመቱትን ቂም አልረሱትም ነበር:: በማግስቱ ማዘንጊያ ጓዳ ውስጥ ጉድ ጉድ እያሉ “አንቱ ዝናቡ ወዴት ደርሷል?” ብለው ቢጠይቋቸው “ለሰማዩ አንቺ ትቀርቢ የለ?” አሏቸው ቆጣ ብለው::
አለቃን ለማስቀናት ብለው የጀሩት ነገር ወይዘሮ ማዘንጊያን ውሽማ እንዲዙ አደረጋቸው:: ውሽምዬ አለቃ ሲወጡ ቤት ይመጣል እና ከማዘንጊያ ጋር ተላምደው ኖሯል።አለቃ ከውጭ ድክም ብሏቸው መጥተው ደጃፍ ያለች መደብ ላይ ቁጭ ብለዋል። ማዘንጊያም ከውሽምዬ ጋር የስንብት ሲሳሳሙ አለቃ አይተው ዝም ይላሉ። ውሽምየው በጓሮ ተሸኝቶ ማዘንጊያ ወደ ደጃፍ ብቅ ሲሉ አለቃን ያዩዋቸውና «አለቃ መጥተዋል እንዴ?» ይላሉ። «እንዴ እዚህ ቁጭ ብዬ ሳመሽ አላየሽኝም እንዴ» ብለው ማዘንጊያ ሲሳሙ ማየታቸውን ተናገሩ።
አለቃ በነገር ወጋ ማድረግን የተካኑበት ነው:: አንድ ቀን ማዘንጊያ ወጥ እየሰሩ አለቃ ተቀምጠው ይመለከቷቸው ነበር:: ሚስቲቱም ወጡ መብሰሉን፣ ጨው ቅመሙ በአግባቡ መደረጉን ለማረጋገጥ ደጋግመው ማማሰያቸውን እያጠለቁ ይቀምሱ ነበር:: አለቃ ደግሞ ርቧቸው ትዕግስታቸው አልቆ “ማዘንጊያ ራታችን እሱ ከሆነ ለእኔም መቋሚያየን አቀብይኝ” በማለት አሳቋቸው::
አለቃ ተንኮልና ኩሸት አያጡም፤አንድ ቀን እቴጌ ጣይቱ ሰፊ ቀሚስ ለብሰው ደረጃ እየወጡ ሳሉ አለቃ ከታች ሆነው የንግሥቲቱን ገመና ለማየት ሽቅብ ሲያንጋጥጡ ድንገት ንግሥቷ ያያሉ። አለቃ ምን እያደረግህ ነው በማለትም ይጠይቋቸዋል። በቃላት መልስ የማይረቱት አለቃም “መውጪያ መውጪያየን እያየሁ ነው” ሲሉ ይመልሳሉ። “መውጪያ መውጪያየን” የተወለድሁበትን የሴት ኃፍረተ ስጋ እያየሁ ነው ማለታቸው ነበር ድብቁ ምስጢር።
እቴጌ ጣይቱ በአንድ ቀን ለአለቃ አንድ ንቅል ስጋ (አንድ እግር ስጋ) ይልኩላቸውና አለቃ ማነው የላከልኝ ይላሉ። በወቅቱም እቴጌዋ እንደላኩላቸው ይነገራቸዋል። በቃላት መጫዎት የሚወዱት አለቃም ተረባቸውን እንዲህ ሲሉ ይጀምራሉ። “እኒህ እቴጌ ለሁሉ እግር እያነሱ እየሰጡ ለመሆኑ ለምኒልክ ምን ሊቀራቸው ነው” ይላሉ። እግር እያነሱ ሁለት ምስጢር ያለው ቃል ነው። ምስጢሩ ከሌላ ወንድ ጋር ብልግና እያደረጉ ማለት ነው። ንግግሩ የቃላት ጨዋታ ነበርና እቴጌዋ ተበሳጩ፤ ይሄንን በሰሙበት ጊዜ አለቃ አዲስ አበባን ለቀው በግዞት ወደ ጎንደር ሄደው እንዲኖሩ አደረጓቸው።
አለቃ በዚህ ብቻ አያቆሙም፤ አንድ ጊዜ ደግሞ ድግስ ተጠርተው “እንዴ አለቃ አይበሉም፤ ይብሉ እንጂ ሲባሉ፤ “ቢሻን እንበላለን ቢሻን እንጠጣለን” በማለት የኦሮምኛ ቃልን ተጠቅመው የደገስሽው ድግስ ውኃ ውኃ ነው የሚለው ብለው ዘልፈዋል::
አለቃ ከሰዎች አካላዊ ማንነት፤ ከአነጋገራቸው፤ ከምግባሮቻቸው ባጠቃላይ ከሰብዓዊ ማንነታቸው እየተነሱ ሰዎችን ይተርባሉ:: አለቃ ከወንዶች ሴቶችን የሚቀርቡና ከሴቶች ጋር በብዛት ታሪክ ያላቸው ሰው ናቸው:: የሚውሉት ከታላላቅ የቤተክኅነት ሰዎችና መኳንንት ጋር ጭምር ነበር:: ምናልባትም አለቃ በትርክቶቻቸው አጼ ቴዎድሮስን፤ እቴጌ ጣይቱን፤ አጼ ምኒልክንና ሌሎችን መኳንንቶች ከመተረብና ከማሾፍም ያልቦዘኑ ነበሩ። አለቃ የላይኛውን መደብ አባላት መተረባቸው ትርክቶቻቸው እንዳይረሱ፣ እንዲጻፉ አድርጓል ቢባል ማጋነነን አይሆንም። አለቃ ገብረ ሀና ሰዎችን ሲተርቡ፤ ሲዘልፉ ለእሳቸው የተሰጠም ምላሽ ወይም አጸፋ አለመኖሩ አለቃ እንዳይረሱና አቤት ግሩም ምላሽ ብለን እንድናስብና እንድናስታውሳቸው አድርጓል።
አንድ የሚኒልክ መኮንን ስልብ ነበሩ ይባላል። መኮንኑ አንድ የጀግንነት ስራ ይሰሩና ሙሉ ትጥቅ ከነልብሱ ይሸለማሉ። አለቃን ያገኟቸውና “አለቃ እንዴት ነው? አላማረብኝም” ይላሉ። አለቃም መልሰው “አይ አስተታጠቅ አይ አለባበሥ አይ ጎራዴ አይ ጎራዴ አይ ጎራዴ” ይላሉ። ሌሎች መኳንንት መኮንኑን አለቃ ምን አሉህ? ይሉታል አደነቁኝ አይ አስተታጠቅ አይ ጎራዴ አሉኝ ይላል። መኳንንቱም ምን አደነቁህ ሰደቡህ እንጂ ስልብ ስለሆንክ ጎራዳ ነህ አይ ጎራዴ የኔ ጎራዳ ነው ያሉህ ብለው አብግነውት አለቃን ካልገደልኩ ብሎ በገላጋይ ነው አለቃ የተረፉት አሉ።
አለቃ ከዕለታት በአንድ ቀን ጣና ሀይቅ ዳርቻ አረፍ ብለው ሳለም አስገራሚ ትርዒት ይመለከታሉ። የሀይቁ ሞገድ በአካባቢው የሚገኙትን ሸንበቆዎች እያዘመመ ልክ ጣዕመ ዜማ እንደተቀመረላቸው ዳንኪራዎች አንዴ ወደ ግራ ቀጥሎም ወደ ቀኝ ሲያዘናፍላቸው ያያሉ። የሰው ልጅም በዚህ መልክ ሊወዛወዝ የተገባ ነው ብለው አዲስ የዝማሬ ትምህርትን ፈለሰፉ:: ይህንም በልጃቸው ተክሌ ስም አደረጉት:: የተክሌ አቋቋም ተብሎም በልጃቸው በኩል በስፋት ተዋወቀ::አለቃ ተክሌም አቋቋሙን በስፋት ያስተምር ነበርና ሌሎች ካህናት በቅናት መንፈስ አባቱ በሞተ በ10ኛው ዓመት በ1898ዓ.ም ተገደለ::
አለቃ ገብረ ሀና የሕይወታቸውን የመጨረሻውን ሁለት ዓመታት በዝምታ እና ጸጸት ውስጥ ሆነው አንደበታቸውን ዘግተው በተወለዱ በ84 አዓመታቸው አለፉ::
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም