“የአማራ ሕዝብ ፍላጐት ጥያቄዎቹን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን እንዲመለሱለትም መፈለግ ነው”

0
268

የዚህ ዕትም እንግዳችን ተወልደው ያደጉት በቀድሞ አጠራሩ ጐንደር ክፍለ ሀገር (በጌምድር)፣ሊቦ አውራጃ፣ በለሳ ወረዳ፣ ጐሀላ በምትባል መንደር ውስጥ ነው:: ትምህርታቸውን የጀመሩትም በጐሀላ መንደር ውስጥ ሲሆን በወቅቱ ኢሕዴን ይባል የነበረው የፖለቲካ ድርጅት በአካባቢው የትጥቅ ትግል በመጀመሩ ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል:: እንግዳችንም ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የቤተሰብ ግፊት አድሮባቸው እስከ አምስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን አቅራቢያቸው በምትገኘው የአዲስ ዘመን ከተማ ቀጥለዋል:: ያም ሆኖ ግን ትምህርታቸውን ከስምንተኛ ክፍል በማቋረጥ ለትግል ወደ በረሃ አቅንተዋል::
እንግዳችን ትምህርታቸውን ለ10 ዓመታት ካቋረጡ በኋላ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም መንግሥት መውደቁን ተከትሎ ትምህርታቸውን ካቋረጡበት ቀጥለዋል:: የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት አያያዝ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሕዝብ ሥራ አመራር ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል::
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ኢሕዴን/ ታጋይ እና ካድሬ በመሆን ሥራቸውን የጀመሩ ሲሆን የአርማጭሆ ወረዳ አስተዳዳሪ፣ የጐንደር ከተማ ብአዴን ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የአማራ ክልል ከተማ እና ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ፣ የሠራተኛ እና ማህበራዊ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና አሁን ደግሞ በአማራ ክልል ሥራ አመራር ተቋም የምርምር እና ሥርፀት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ::
እንግዳችን “ዳገት ያበረታው የአማራ ፍኖት” በሚል ርዕስ በ2011 ዓ.ም ዳጐስ ያለ የታሪክ መጽሐፍ ለአንባቢያን አቅርበዋል:: ከእንግዳችን ዶ/ር ቹቹ አለባቸው ጋር የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታዎች እና ሌሎች ጉዳዮችን አንስተን ቆይታ አድርገናል::
መልካም ንባብ!

ለአማራ ዳገት እና ብርታት የሆኑበት የትኞቹ ችግሮቹ ናቸው?
“ዳገት ያበረታው የአማራ ፍኖት” በሚለው የታሪክ መጽሐፌ ውስጥ የአማራ ሕዝብ ላይ የደረሱትን ተደጋጋሚ በደሎች እና የአማራ ሕዝብም በእነዚህ ተደራራቢ በደሎች ጉልበቱ ሳይዝል ዳገቶችን የወጣባቸውን መንገዶች ለመግለጽ ሞክሬያለሁ:: በዚያ መጽሐፌ ላይ ከማውቀው እውነት በመነሳት በአማራ ሕዝብ ላይ ይደርሱበት የነበሩትን ተደራራቢ መከራዎች እንዲሁም በሕዝቡ ይነሱ የነበሩ መሠረታዊ ጥያቄዎችንም ለመግለጽ ሞክሬያለሁ::
የአማራ ሕዝብ ችግሮች ውስብስብ እና ሥር የሰደዱ ናቸው፤ ጠላቶቹም የበዙ ናቸው:: የአማራን ሕዝብ ማዳከም የተጀመረው ከጣሊያን ወረራ በፊት ነው:: የተለያዩ የውጭ ፀሐፍት ኢትዮጵያን እና አማራን አስመልክተው ይጽፏቸው የነበሯቸው ጽሑፎች ኢትዮጵያን በጣሊያን እንድትወረር በር የከፈቱ ነበሩ:: በተለይ አንዳንድ መጽሐፎች ኢትዮጵያን ማዳከም ተቀዳሚው ዓላማቸው ቢሆንም አማራን እና የኦርቶዶክስ እምነትን ነጥሎ በማጥቃት ሌላው ዓለምም ይህንን ሕዝብ በመጥፎ እንዲስለው ጥረት ያደርጉ ነበር::
በእነዚህ ክፉ የፈጠራ ድርሰቶች ውስጥ የአማራ ሕዝብ እና የኦርቶዶክስ እምነት ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን እና እምነቶችን እንደሚበድሉ ተደርጐ መሳሉ አሁን ድረስ ያሉት የተሳሳቱ ተረኮች መወለጃ ጽንስ ሆነዋል:: ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የአማራ ሕዝብ ጨቋኝ እና በዳይ ተደርጐ እንዲሳል በመሆኑ ስሙ በክፋት የሚነሳ ሕዝብ ሆኗል:: ስሙ በክፋት መነሳቱ ብቻ ሳይሆን ላልበደለው በደል መከራን እንዲያጭድ የተደረገ ሕዝብ ነው- አማራ::
በእነዚህ የተሳሳቱ ተረኮች ምክንያት ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ ጠላቶች የበዙበት የአማራ ሕዝብ ችግሮቹን የሚረዳው ወገን እስከማጣት የደረሰ ነው:: የውጪው ዓለምም ፊቱን እንዲያዞርበት በርካታ የተሳሳቱ ተረኮች ቀርበውበታል:: የኢትዮጵያ ሌሎች ብሔሮችም ቢሆኑ በዚህ ሕዝብ ላይ ከጣሊያን ወረራ በፊትም ሆነ በኋላ በተዘሩት መጥፎ ትርክቶች ይህንን ሕዝብ እንደ ጨቋኝ ለማየት ተገደዋል::
የአማራ ሕዝብ በተሳሳቱ ተረኮች ምክንያት ያልደረሰበት መከራ እና ግፍ የለም:: የአማራ ሕዝብ በፖለቲካ ሥልጣን በሚገባው ልክ የተወከለ አይደለም፤ በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ አማራዎች እንዲጠሉ፣ እንዲገደሉ እና እንዲሰደዱ የተሳሳቱ ተረኮቹ ትልቅ ሚና ነበራቸው:: የሀገሪቱ ሕገ መንግሥትም የአማራን ሕዝብ በሚጐዳ መልኩ የተረቀቀ ነው:: በአጭሩ ግን የአማራ ሕዝብ በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብትም ሆነ በማህበራዊ ጉዳዮቹ ዝርዝር በደሎች እንደደረሱበት ዳገት ያበረታው የአማራ ፍኖት በሚለው መጽሐፌ ላይ ለማሳየት ሞክሬለሁ፤ እነዚህ የአማራ ሕዝብ ቁስሎች ዛሬም ድረስ ያልታከሙ እና ያልሻሩ ናቸው::
እነዚህን ሁሉ በአማራ ሕዝብ ላይ የደረሱ በደሎች አንስቶ፣ ሕዝቡ የደረሱበትን ተደራራቢ በደሎች ለመቋቋም ያደረገውን ጽናት ስናይ የአማራ ሕዝብ ምን ያህል የማይሰበር ሕዝብ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል:: የአማራ ሕዝብ ፈተናዎች የበዙ ቢሆንም የሕዝቡ ፈተናዎችን የመቋቋም አቅም እና ጽናት ደግሞ ከፈተናዎቹም በላቀ ከፍታ ላይ የሚገኙ ናቸው::
የአማራ ሕዝብ ችግሮች በመጽሐፌ ላይ እንዳሰፈርኩት እና አሁንም ድረስ እንደማምነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወይም በድንገት የተከሰቱ አይደሉም:: የአማራ ሕዝብ ችግሮቹን እና መፍትሔዎቹን አሻግሮ የሚያይለት ወይም የሚፈታለት ሁነኛ መሪ ያጣ ሕዝብም ሆኖ ከርሟል:: ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታትም የአማራ ሕዝብ ወቅቱን የሚመጥኑ መሪዎችን በመፈለግ ላይ ይገኛል:: አሁን ላይ በስፋት የሚቀነቀነው የብሔር ፖለቲካ አማራን በጨቋኝነት የፈረጀ ነው::
ለአማራ ሕዝብ ዳገት የሆኑበት በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ሕዝቡ ችግሮቹን ለመጋፈጥ ያሳየው ጽናት ደግሞ የብርታቱን አስገራሚነት የሚያሳዩ ናቸው:: በተሳሳተ መንገድ የውጭ እና የውስጥ ጠላቶች የበዙበት የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነቱ ማማ ሳይወርድ ለነዚህ ሁሉ ዓመታት መዝለቁ በእጅጉ የሚደነቅ ሕዝብ ስለመሆኑ ማሳያዎቹ ናቸው::

ለአማራ ሕዝብ አሁንስ ዳገቱ ቀንሷል?
ዳገቱ ቀንሷል ማለት አይቻልም፤ ብዙ የተሻሻሉ ነገሮች አሉ ለማለትም ይከብዳል፤ የአማራ ሕዝብ ዳገቱ እንዲቀንስለት ፖለቲካዊ ትግል ማድረግ የጀመረው በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ በኩል ነው:: በብአዴን እና ከዚያ በፊት በነበሩት መሪ ድርጅቶች ዘንድ ለአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንኳን እውቅና የመስጠት ዝንባሌዎች አልነበሩም:: ከ1983 ዓ.ም የሥርዓት ለውጥ በኋላ አንዳንድ የአማራ ኤሊቶች እና ሕዝቡ መጪው ጊዜ ለአማራ የበለጠ የከፋ እንደሚሆን አውቀው ነበር:: ይህንን አስተሳሰብ አብዛኛው የአማራ ታጋይም ሆነ ሕዝቡ በተገቢው መልኩ አልተረዳውም::
የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች መነሳት የጀመሩት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ነው:: በተለይ የማንነት ጉዳይ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ሆኖ ተነስቷል:: ብአዴን ፈርሶ አዴፓ ሲመሰረት ደግሞ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ነጥረው ወጥተዋል:: አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት… ተብለው የተነሱትን የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በሕዝቡም ሆነ በአዴፓ መሪዎች ከሞላ ጐደል የአማራ ሕዝብ የመታገያ ጥያቄዎች እነዚህ ናቸው ተብሎ ነበር፤ ጥያቄዎቹን ለማስመለስ በጋራ የመቆም አዝማሚያም ታይቶ ነበር፤ ይሄ ጥሩ ጅምር ነበር::

Bekur /በኲር, [2/12/2024 5:06 PM]
ሲገፋ የኖረው እና ጥያቄዎቹ ተቀባይነት አጥተው የነበረው የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንዳሉት ማሳወቁ በራሱ አንድ ጥሩ እርምጃ ነው:: የአማራ ሕዝብ ፍላጐት ግን ጥያቄዎቹን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን እንዲመለሱለት መፈለግም ጭምር ነው:: ይህ ደግሞ ትክክለኛው አካሄድ ነው:: አሁን ላይ ችግር የሆነው እነዚያ የአማራ ጥያቄዎች በዚያን ወቅት ብቻ አይደለም አሁንም ድረስ ያለመመለሳቸው ነው:: በተለይም በለውጡ ወቅት ይመለሳሉ ተብለው በሕዘቡ ዘንድ ተስፋ የተጣለባቸው ጥያቄዎቹ ለውጡ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ በመውደቁ ጥያቄዎቹን ለመመለስ ፈተና ሆኗል::
የአማራ ብልጽግና የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ለመቀበል አልተቸገረም፤ ጥያቄዎቹ ተገቢነት ያላቸው ለመሆኑም አይጠራጠርም፤ በመመለሱ ረገድ ግን አንድ እርምጃም ቢሆን ወደፊት አልተሄደም:: ይሄው ችግርም አሁን ላይ በክልሉ ውስጥ ለተፈጠረው የሰላም መደፍረስ እርሾ ሆኖ አገልግሏል:: እዚህ ላይ በጥሩ ነገር የሚነሳው የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ከግለሰቦች እና ከመንደር ወጥቶ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ እውቅና የተቸረው ሆኗል::
አሁን ላይ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ የሚታወቁ ሆነዋል፤ ይህም ለአማራ ሕዝብ መታገያ ምክንያቱ ነው፤ ጥያቄዎቹ ግን አሁንም ድረስ በበቂ ሁኔታ ላለመመለሳቸው ብዙ ማሳያዎች አሉ::

ከወሰን እና ማንነት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮች ምንጫቸው ምን ይሆን? መፍትሔያቸውስ?
ለወሰን እና ማንነት ጥያቄዎች መነሻው እየተከተልን ያለነው የፖለቲካ ሥርዓት ነው:: ችግሩ በአማራ ክልል ውስጥ ጐልቶ የሚታይ ቢሆንም በሌሎቹ የሀገራችን ክፍሎችም የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች ተደጋግመው እየተሰሙ ነው:: የሀገራችን ሕገ መንግሥት መሬትን እና ማንነትን አጣብቆ የሰጠ ነው፡ ይህ ማለት ደግሞ መሬት የሚሰጠው ለብሔር ነው እንደማለት ነው:: የወሰን እና የማንነት ችግር በኢትዮጵያም ሆነ በአማራ ክልል አስቸጋሪ ሆነው የመጡት ሀገሪቱ የተዋቀረችበት የፖለቲካ ሥርዓት ወይም የፌዴራል ሥርዓቱ መሬትን ከማንነት ጋር ያያያዘ በመሆኑ ነው::
መሬት እና ማንነት መያያዛቸው ብቻ ሳይሆን ተያይዘውም በአግባቡ እየተተገበሩ አይደለም:: ለምሳሌ ቋንቋን እና ማንነትን መሰረት አድርጐ ይከለል ቢባል፤ እንደ አብነት የወልቃይት፣ ራያ እና ጠለምት አካባቢዎች በተገቢው መልኩ የተከለሉ አይደሉም:: የሥርዓቱ አወቃቀር ከመጀመሪያውም ስህተት ነው:: ከነስህተቱም ቢሆን ደግሞ በነዚህ አካባቢዎች ያለው አወቃቀር ሌላ ስህተት የታከለበት ነው::
የወልቃይት፣ ራያ እና ጠለምት ሕዝብ ጥያቄ ሕገ መንግሥቱ ላይ በሰፈረው አግባብ እንኳን ማንነታቸውን ባከበረ መልኩ አልተመለሰም:: ይሄ በኢትዮጵያ ከወሰን እና ማንነት ጋር ተያይዞ ለመጣው መሰረታዊ ችግር የፌዴራል ሥርዓቱ መሬትን ከሕዝብ ጋር አያይዞ ማዋቀሩ የችግሮቹ መነሻ እንዲሆን አድርጐታል:: ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሆነውም ይሄንኑ ጉዳይ ማስተካከል ነው::
ፌዴራላዊ ሥርዓት ለኢትዮጵያ አስፈላጊዋ መሆኑን ባልጠራጠርም እንዴት መዋቀር እንዳለበት ስናስብ ግን ብዙ ነገሮችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆን አለበት:: በተለይ የሕዝብን አንድነት የሚያፀና መሆን ይኖርበታል:: በፌዴራል ሥርዓቱ ምክንያት ሕዝብ ከሕዝብ ጋር መጋጨት እና የቂም ቁርሾ መያዝ የለበትም:: ከችግሮቹ በመማር፣ ችግሮቹን ለማስወገድ መሥራት ከመንግሥትም ሆነ ከሕዝብ የሚጠበቅ አንኳር ጉዳይ ነው::መንግሥትም ይህንን ጉዳይ በተገቢው መልኩ ይረዳዋል የሚል እምነቱ አለኝ::
ይቀጥላል

(እሱባለው ይርጋ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here