የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ በጣም ሰፊ እና አውዳሚው ነው። ጦርነቱ ያስከተለው ውጤት ከሩሲያ እና ከዩክሬን አልፎ ሄዷል፡፡ ጦርነቱ ጥምረነትን እና አጋርነትን ቀይሯል፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ የጦርነት ስትራቴጂዎች እና ፅንሰ ሀሳቦችም ታይቶበታል፡፡
ጦርነቱ ቀድሞውንም በቋፍ ላይ የነበረውን የአውሮፓን እና የሩሲያን ግንኙነት ያባባሰ ነው፤ በሌላ በኩል በአሜሪካ እና በአውሮፓ መካከል ያለውን ግንኙነት ደግሞ ለማጠናከር ዕድልን ፈጥሯል፡፡ ሩሲያ ከቻይና፣ ከኢራን እና ከሰሜን ኮሪያ ጋር የነበራት ወዳጅነትም ይበልጥ ጎልብቷል፡፡
አውዳሚውን ጦርነት ለማስቆም ሙከራዎች ቢደረጉም ውጤት አላስገኙም፤ በተለይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርቱን በአጭር ጊዜ እንደሚያስቆሙት ቃል መግባታቸው የጦርቱን ዕድሜ ያሳጥረዋል የሚል ተስፋን ሰንቆ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከሙከራ ባለፈ ጥረቶች ውጤት አላስገኙም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር አዲስ የሰላም ድርድር ለማድረግ ሀሳብ አቅርባለች። ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ድርድሮች መቋረጣቸውን ልብ ይሏል፡፡ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ከሩሲያ ተደራዳሪዎች ጋር ለመሰብሰብ ሀሳብ ማቅረባቸውን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በአመራር ደረጃ ስብሰባ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ “የተኩስ አቁምን ለማሳካት ሁሉም ነገር መደረግ አለበት” ብለዋል። ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ፊት ለፊት ለመቀመጥ ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት።
ሀገራቱ በዚህ ዓመት በተርኪየ ሰላምን ለማምጣት ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ነበር፤ ቢሆንም ውይይታቸው የእስረኞችን እና የወታደሮቻቸውን አስከሬን ከመለዋወጥ የዘለለ ውጤት አላስገኘም።በቀደሙት የሰላም ድርድሮች ሩሲያ በዩክሬን ዘንድ ተቀባይነት ያላገኙ ጠንካራ ጥያቄዎችን ያነሳች ሲሆን እነሱም ለድርድሩ መፍረስ ምክንያቶች እንደሆኑ ነው አናዶሉ የዘገበው፡፡ ጥያቄዎቹም በጦርነት የያዘቻቸውን አራቱን የዩክሬን ክልሎች ለሩሲያ እንድትሰጥ፣ ከምዕራባዊያን የሚደረግላት ወታደራዊ ድጋፍ እንዲቆም እና የኔቶ አባልነት ጥያቄዋን እንድትተው የሚያዙ ነበሩ። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሞስኮ በዜሌንስኪ ሀሳብ (ሰሞናዊው የድርድር ሀሳብ) እንደተስማማች እና የሰላም ጥረቶች የበለጠ ፍጥነት እንደሚያስፈልጋቸው አሳውቀዋል። ይህ ለውጥ የመጣው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መጀመሪያ ላይ የማስታረቅ ዘዴን የተከተሉ መስለው በሞስኮ ላይ ጫና ካደረጉ በኋላ ነው።ትራምፕ ሞስኮ በዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት እንድታደርግ የመቶ በመቶ ታሪፍ ጭማሪ እና የሩሲያን ነዳጅ ዘይት በሚገዙ ሀገራት ላይ የሁለተኛ ደረጃ ማዕቀብ እንዲጣል የ50 ቀናት ቀነ ገደብ አስቀምጠዋል፡፡ በጦርነት ወደ ወደመችው ሀገር (ዩክሬን) የጦር መሣሪያ አቅርቦትን እንደሚያሳድጉ ቃል ገብተዋል። በቃላቸው መሠረትም አሜሪካ እና ጀርመን የዩክሬን ከተሞችን ከምሽት የሩሲያ ጥቃቶች ለመከላከል የሚያስችል የጦር መሣሪያ ለማቅረብ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ከሰሞኑ የጀርመኑ ቻንስለር ፍሬድሪክ ሜርዝ ሀገራቸው በአሜሪካ የተሠሩ የአየር መከላከያ ዘዴዎችን እንደምትገዛ ተናግረዋል፡፡ ሜርዝ በሮም በተካሄደው የዩክሬን የመልሶ ግንባታ ኮንፈረንስ ላይ እንደተናገሩት “ለዩክሬን ተጨማሪ ፓትሪዮት የተሰኙ የሚሳኤል ሥርዓቶችን ከአሜሪካ ለመግዛት ተዘጋጅተናል” ነው ያሉት፡፡ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ለኤን ቢ ሲ ዜና እንደተናገሩት በአሜሪካ የተሠሩ ፓትሪዮት ሚሳኤሎችን ጨምሮ ሌሎች የጦር መሣሪያዎችን ለኔቶ በመሸጥ ለዩክሬን እንዲደርስ ይደረጋል ብለዋል። ፓትሪዮት ሚሳኤል የረጅም ርቀት የአየር መከላከያ ሥርዓት ሲሆን አሜሪካ ሠራሽ ነው። ፓትሪዮት የሚሳኤል ሥርዓት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለመጠቀም በጣም ውድ ቢሆንም በዩክሬን ውስጥ የባሊስቲክ ሚሳኤሎችን መምታት የሚችል እና በክሩዝ ሚሳኤሎች ላይም ውጤታማ የሆነ ብቸኛው መሣሪያ ነው።የአሜሪካው ሴናተር ሊንዚ ግርሃም ለሲ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ “በሚቀጥሉት ቀናት ዩክሬን እራሷን በከፍተኛ ደረጃ ለመከላከል ትዘጋጃለች” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ከሰሞኑ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በሰሜን ምሥራቅ ካርኪቭ ውስጥ በዶንቶስክ እና በሶቦሌቭካ ምሥራቃዊ ክልል ውስጥ ዘሊዮናያ ዶሊናን የተባሉ ግዛቶችን መያዙን አሳውቋል። ሆኖም በዚህ ፍጥነት ሩሲያ በቀን 15 ካሬ ኪሎ ሜትር (ስድስት ስኩዌር ማይል) ነው በዩክሬን ግዛት ዘልቃ መግባት የቻለችው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ሩሲያ ሙሉ በሙሉ ዩክሬንን ለመያዝ 89 ዓመታት ያስፈልጋታል ሲል ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት አስታውቋል።አልጀዚራ እንደዘገበው ከሐምሌ ወር አንደኛ ሳምንት ጀምሮ ሩሲያ በየምሽቱ በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎችን በመጠቀም የዩክሬን ከተሞችን መምታቷን አጠናክራ ቀጥላለች። የዩክሬን አየር ኃይል በበኩሉ በአንድ ሌሊት ብቻ ከሩሲያ ከተተኮሱ 597 ሰው አልባ አውሮፕላኖች ውስጥ 577ቱን እና 25 (Kh-101) ክሩዝ ሚሳኤሎችን መትቶ መጣሉን ወይም በኤሌክትሮኒካዊ መንገድ ማፈኑን አሳውቋል።ይህ በእንዲህ እንዳለ በዩክሬን የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ተልዕኮ በሰኔ ወር በሦስት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የሆነው የዜጎች ሕይዎት ማለፉን አሳውቋል፡፡ ሟቾቹም 232 ሲሆኑ አንድ ሺህ 343 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። ትራምፕ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ ከመሸጥ ጋር በተያያዘ ባደረጉት ንግግር ዋይት ሀውስ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሣሪያ ሽያጭ ማፅደቁን አስታውቀዋል። አሜሪካ መሣሪያ የምትሸጥበትን እና የኔቶ አባላት ደግሞ የሚከፍሉበት ስምምነት መደረሱንም ገልጸዋል፡፡ &ዩክሬንን ለመርዳት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ካወጣን በኋላ ገንዘባችንን ሙሉ በሙሉ እየመለስን ነው” ብለዋል፡፡ አሜሪካ ለአውሮፓ አጋሮቿ ዩክሬንን ሊጠቅም የሚችል በርካታ የጦር መሣሪያ መሸጥ የምትጀምርበትን ዕቅድ እንዳለ ጠቁማለች፡፡ ይሁንና በዋሺንግተን ዲሲ የነበሩት የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ቦሪስ ፒስቶሪየስ ዝርዝሩን አልገለጹም። ሩሲያ እ.አ.አ ከ2025 መባቻ ጀምሮ በዩክሬን ከተሞች ላይ የምታደርሰው ጥቃት ጨምሯል። በሰኔ ወር ብቻ 330 ሚሳኤሎችን እና አምስት ሺህ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በዩክሬን ላይ አስወንጪፋለች።የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በሚያዝያ ወር እንደተናገሩት ዩክሬን ከተሞቿን ለመጠበቅ 10 ተጨማሪ የፓትሪዮት የሚሳኤል ሥርዓቶች እንደሚያስፈልጋት አሳውቀው ነበር። የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ በሩሲያ ላይ ቀጥተኛ ጦርነት በማወጅ አውሮፓን ለጦርነት ለማነሳሳት እየሞከሩ ነው በማለት ለዩክሬን ጦር መሣሪያ ለመግዛት የሚያደርጉትን ጥረት ተችተዋል። በሌላ በኩል ምንም እንኳን አስፈሪ ዛቻዎች ቢኖሩም (የአሜሪካን ማስጠንቀቂያ ጨምሮ) የሞስኮ የአክሲዮን ልውውጥ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል፤ ከትራምፕ ዛቻ በኋላ ወዲያውኑ በሁለት ነጥብ ሰባት በመቶ ጨምሯል። የሩሲያ ሩብል ዋጋም መጠናከሩን ነው ዘ ኮንቨርሴሽን ከሰሞኑ ያሳወቀው።በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ገበያ የተረጋጋ ይመስላል፣ ይህም ነጋዴዎች ምንም አይነት አደጋ እንደማይደርስባቸው ይጠቁማል። ሩሲያዊያን ከዋሺንግተን የተነገረውን ዛቻ ለመተንተን ጊዜ እንደሚያስፈልግ ቢገልጹም በሌሎች መግለጫዎች ግን ዛቻው ምንም ውጤት እንደሌለው ጠቁመዋል። ለአብነትም የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ “ሩሲያ ለትራምፕ ዛቻ ምንም ደንታ የላትም” ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ (www.usatoday.com) ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው እንደ ዩክሬን ግምት እ.አ.አ በየካቲት ወር 2022 ከሞስኮ ሙሉ ወረራ በፊት እና በኋላ ሩሲያ ከያዘችው ግዛት ሰባት በመቶ ያህሉን ግዛት ነፃ አውጥታለች። 19 በመቶ ያህል አሁንም በሩሲያ እጆች ውስጥ ይገኛል። ሞስኮ አሁንም እ.አ.አ በ2014 የቀላቀለቻትን ክሬሚያን እና ሁለት ሦስተኛውን የዩክሬን ሰፊ እና በኢንዱስትሪ የበለፀገውን የዶንትስክ ክልል ትቆጣጠራለች።
ተንታኞች እንደሚሉት በጦርነቱ ውስጥ ሩሲያ በወታደራዊ የሰው ኃይል የበላይ ሆና ብትቆይም የበለጠ ጉዳት ደርሶባታል፡፡ መድፎች፣ ታንኮች እና ሌሎች የጦር መሣሪያዎች እና የተሸከርካሪዎች ውድመቶች ከዩክሬን በላይ እንደሆነ ነው ዘገባው ያመላከተው።
ሩስያ በጦርነቱ የተሻለ ሆና እንድትታይ ያደረጋት ምክንያት በዩክሬን ላይ የምትሰነዝራቸው የድሮን ጥቃቶች እና ሚሳኤሎች ከምንግዜውም በላይ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሯ ነው። በሰኔ እና በሐምሌ የፈጸመቻቸው ጥቃቶች ከሌሎች ወራት ጋር ሲነጻጸርም በአማካይ በ31 በመቶ ወርሃዊ ፍጥነት እና ጭማሪ አለው። ሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀሟ በርካታ የዩክሬን ወታደሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ችላለች።
ይህ በእንዲህ እያለ የዩክሬን ወታደራዊ መሪዎች ሩሲያን ያለ ሰው አልባ አውሮፕላኖች መዋጋት ‘ከሞላ ጎደል የማይቻል ነው’ ሲሉ ማሳሰባቸውን ሲ ኤን ኤን የዘገበው ከሰሞኑ ነው፡፡ በሰኔ ወር ዩክሬን ከፊት መስመር በሺዎች የሚቆጠሩ ማይሎችን ርቀው በሚገኙት የሩሲያ አየር ማረፊያዎች ላይ መጠነ ሰፊ የድሮን ጥቃት ማካሄዷ ይታወቃል። ይህ አስተያየት የመጣው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪ የአየር መከላከያዎችን ወደ ዩክሬን ለመላክ ቃል ከገቡ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ )
በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም