የአምበር ተራራ ብሔራዊ ፓርክ

0
24

ብሔራዊ ፓርኩ በማዳጋስካር ደሴት ሰሜናዊ ቀጣና፤ በእሳተ ገሞራ በተፈጠረ ልምላሜን በተላበሰ ሰንሰለታማ ተራራ ላይ ነው የሚገኘው::

ፓርኩ በ1958 እ.አ.አ የተመሰረተ ሲሆን መገኛው ከ850 ሜትር እስከ 1475 ሜትር ከፍታን አካሏል:: አጠቃላይ ስፋቱም 230 ኪሎ ሜትር  ስኩዌር ነው::

የፓርኩን ቀጣና ባካተተው ተራራማ መልካአ ምድር ርጥበት አዘል ጥቅጥቅ ደን፣ ሐይቆች፣ የሚገኙበት ፀጥታ የሰፈነበት ለጐብኚዎች  በእግር ለመጓጓዝም የተመቸ ነው::

ቀጣናው የነባር  ማላጋሲ ጐሳዎች መኖሪያ ነው::  የሀገሪቱ የፓርኮች ጥበቃ ድርጅትም ከበጐ አድራጊ ድርጅቶች ጋር ማህበረሰቡ በደን ሀብት ላይ ያለውን ጥገኝነት በሚቀንስ አማራጭ የኑሮ ዘዴን ለማብቃት  እየሰራ ነው::  የፓርኩ ዓየር ንብረት ዝቅተኛው 15 ከፍተኛው ደግሞ 27 ዲግሪ ሴልሺየስ ተመዝግቧል::

በፓርኩ 75 የዓዕዋፍ ዝርያዎች ይገኛሉ ከነዚህ ውስጥ 35ቱ ብርቅዬ (እንዴሚክ) -መሆናቸውም ተጠቁሟል:: ከተሳቢ (አምፊቢያንስ) 60 ዝርያዎች፣ ከአጥቢዎች 25 ዝርያዎች መገኛም ነው::

በፓርኩ የሚገኘው ጥቅጥቅ ደን ለጐብኚዎች መስህብ ሆኖ ከሚያስገኘው ገቢ ለባሻገር ማገዶ እና ለመድሃኒት ግብአትነት ያገለግላል::

ብሔራዊ ፓርኩ ለሀገሪቱ ትክ የሌለው ተፈጥሯዊ ቅርስ ምሳሌ ነው:: ለም ለም መልክዓ ምድሩ እንስሳት እና እፅዋቱ፣  ተመራጭ የጐብኚዎች መዳረሻ አድርገውታል::

በቀጣናው የሚገኘውን ስነምህዳር በመጠበቅ ለብዝሃ ህይዎት ሀብቱ  መጠለያነቱን ማረጋገጥ፣ ኗሪዎቹን በማሳመን  አሁን ካለው ትውልድ ባሻገር ለመጪዎቹ ለማስተላለፍ ጥበቃውን ማጠናከር እንደሚገባም አፅንኦት በመስጠት ነው የድረገፆች ጽሁፍ የተደማደመው::

ለዘገባችን  በመረጃ ምንጭነት (ትራቭለርስ) ኦፍ ማዳጋስካር፣ ኧርዝ ትሪጥ፣ ጂንማን ሰፋሪ ድረገፆችን ተጠቅመናል::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሕዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here