የአምናዉ እንዳይደገም…

0
418

ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ክልሉ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ከ33 በመቶ በላይ ይሸፍናል፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ በክልሉ ለወራት የቀጠለው ግጭት ግብርናውን አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቶታል::

በተመሳሳይ በ2015/16 የምርት ዘመን የተከሰተው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ዘርፉን ክፉኛ እንደፈተነው ይታወቃል፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ጊዜ የተከሰተው ችግር እንዳይደገም በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል:: ለ2016/2017 የምርት ዘመንም ከስምንት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል:: ግዥም ተፈጽሞ በመጓጓዝ ላይ ይገኛል::

ከቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2016/2017 ዓ.ም የመኸር እርሻ አምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ  ወደ ሥራ ተገብቷል:: በ2015/2016 የምርት ዘመን ከተገኘው ምርት በ24 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ብልጫ ይኖረዋል ተብሎም ይጠበቃል::

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው እስከ ሚያዚያ አጋማሽ 2016 ዓ.ም ድረስ ከአራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቶ ዩኒየኖች ላይ መድረሱ ተገልጿል:: እስካሁንም ከሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱ ታውቋል::

የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደህንነት ባለ ስልጣን በበኩሉ ለ2016/2017  የምርት ዘመን የሚውል 275 ሺህ በላይ ኩንታል ምርጥ ዘር መሰብሰቡን አስታውቋል:: ከዚህም ውስጥ 54 ሺህ ኩንታል ቀድመው ዘር ለሚጀምሩ አካባቢዎች “ቢ ኤች 661” የሚባል የበቆሎ ዘር እየተሰራጨ እንደሚገኝ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል፤ ነገር ግን የዘር አቅርቦቱ በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ የበቆሎ እና ሌሎች ምርጥ ዘሮች እንዲቀርቡላቸው አርሶ አደሮች ጠይቀዋል::

በስልክ ሐሳባቸውን ለበኩር የሰጡ አርሶ አደሮች እንደተናገሩት የአፈር ማዳበሪያ በአካባቢው ቢደርስም ለአርሶ አደሩ ግን በበቂ መጠን አልደረሰም፤ በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ የአርባዕቱ እንስሳ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር አየነው ዋሴ ለ2016/2017 የምርት ዘመን ማሳቸውን ከማጽዳት ጀምሮ በተደጋጋሚ መሬታቸውን አርሰው ለዘር ማዘጋጀታቸውን ነግረውናል:: በ10 ሄክታር በሚጠጋ ማሳቸው የተለያዩ ሰብሎችን ይሸፍናሉ:: በብዛት በቆሎ፣ ጤፍ እና ስንዴ እንደሚያመርቱ የሚናገሩት አርሶ አደሩ በአሁኑ ወቅትም በዘር ለሚሸፍኑት ማሳ ግብዓት ለማሟላት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ::

አርሶ አደሩ እንደተናሩት በምርት ዘመኑ ከ15 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ያስፈልጋቸዋል፤ ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት እስከ ሚያዚያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ያገኙት ግን ሁለት ኩንታል ተኩል ብቻ ነዉ::

በስድስት ሄክታር መሬታቸው በቆሎ ለመዝራት ቢያቅዱም በቂ ማዳበሪያ እንዳላገኙ ተናግረዋል:: ለበጋ መስኖ ከሁለት ሄክታር መሬት በላይ አርሰው የአፈር ማዳበሪያ ባለማግኘታቸው በዘር መሸፈን እንዳልቻሉ ገልፀዋል::

ባለፈው ዓመት በነበረው የግብዓት እጥረት ያቀዱትን ምርት እንዳላገኙ የተናገሩት አርሶ አደሩ በዚህ ዓመት ግን  “የምንፈልገው ግብዓት በእጃችን ባይደርስም ቀድሞ ወደ ዞኑ መግባቱ እና የዋጋ ቅናሽ መኖሩ መልካም ነው” ብለዋል::

ባፈው ዓመት አጋጥሞ የነበረውን የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ተከትሎ ከሕገ ወጥ ነጋዴዎች አንዱን ኩንታል እስከ 10 ሺህ ብር መግዛታቸውን ተናግረዋል:: ይህ ችግር ዘንድሮም እንዳይደገም ታዲያ የሚመለከተው አካል ፈጥኖ መፍትሄ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል:: ፍትሐዊ ክፍፍል እንዲደረግም ጠይቀዋል::

ሌላው በስልክ ያነጋገርናቸው በምሥራቅ ጎጃም ዞን የቢቡኝ ወረዳ ገና መምቻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደመላሽ ታረቀኝ ሦስት ሄክታር ማሳቸውን አርሰው ለመዝራት ቢያዘጋጁም የሚፈልጉትን የአፈር ማዳበሪያ ባለማግኘታቸው አስጨንቋቸዋል::

10 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቢያስፈልጋቸውም እስካሁን ግን አንድ ኩንታል ተኩል ብቻ እንዳገኙ ተናግረዋል:: ከዚህ በተጨማሪም በቂ የበቆሎ ምርጥ ዘር አለማግኘታቸውንም አክለዋል::

በሌላ በኩል የምሥራቅ ጎጃም ዞን 612 ሺህ 96 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ23 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ለማምረት አቅዶ እየሠራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ መኮንን ለበኩር በስልክ ተናግዋል:: በዚህ ወቅት ለበቆሎ ዘር የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ እየተሰራጨ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው በቀጣይም ለስንዴ እና ለጤፍ እንደሚቀርብ ተናግረዋል::

በምርት ዘመኑ በሰብል ለሚሸፈነዉ መሬት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል:: ከዚህ ውስጥም ሰባት መቶ ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ወደ ዞኑ ገብቷል:: ከ579 ሺህ ኩንታል በላይ ደግሞ ወደ ሕብረት ሥራ ማሕበራት ተጓጉዟል ብለዋል:: ከ377 ሺህ በላይ ኩንታል የሚሆነው አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች መሰራጨቱንም አክለዋል::

አቶ አበበ እንዳሉት ዞኑ 30 ሺህ 562 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ያስፈልገዋል፤ ይሁን እንጂ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈቀደለት 19 ሺህ 507 ኩንታል ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል:: ከዚህ ውስጥም ከ10 ሺህ በላይ ኩንታል ወደ ዞኑ ገብቷል:: ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሚያዚያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ሰባት ሺህ 625 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ለበኩር ጋዜጣ ተናግረዋል::

አርሶ አደሮች ያነሱትን የግብዓት እጥረት ጥያቄ አቶ አበበ ተጋርተዋል፤ በመሆኑም አርሶ አደሩ ሳይጉላላ ግብዓት በፍጥነት የሚያገኝበት አሠራር ተዘርግቶ ችግሩን ለመፍታት ግብዓት የማጓጓዝ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል::

የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አስማረ በበኩላቸዉ በምርት ዘመኑ 284 ሺህ 296 ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል:: ለዚህም 894 ሺህ 120 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል:: እስካሁንም ከ318 ሺህ በላይ ኩንታል የአፈር መዳበሪያ (ኤን ፒ ኤስ) እና ከ266 ሺህ በላይ ዩሪያ በአጠቃላይ ከ584 ሺህ በላይ ኩንታል ማዕከላዊ መጋዝን መቅረቡን አስረድተዋል:: ከቀረበው ውስጥም 259 ሺህ ያህል ኩንታሉ ተሰራጭቷል::

በተመሳሳይ በ2016/2017 የምርት ዘመን ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ ለመሸፈን በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል:: ለዚህም ከ23 ሺህ በላይ ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል:: ቢሆንም እስካሁን የቀረበው አምስት ሺህ 157 ኩንታል ብቻ ነው:: ከሁለት ሺህ በላይ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ገልጸዋል::

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here