የአረጋዊያን መብቶች

0
200

በዓለም አቀፍ ደረጃ አረጋዊነት ከጡረታ መውጫ ዕድሜ ጋር ተያይዞ ይተረጎማል::  በኢትዮጵያም  በአዋጅ  ቁጥር     345/2003 እንደሰፈረው ከመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ መውጫ ዕድሜ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ይገኛል፤ ይህም ትርጓሜውን እንደተቀበለችው ማሳያ ነው::

በታዳጊ ሀገራት አረጋዊያን ራሳቸው ህብረተሰቡ ለነሱ ያለውን የተዛባ አመለካከት “አሜን” ብለው በመቀበል ራሳቸውንም ጭምር ከተለያዩ ማህበራዊ ተሳትፎ ያገላሉ:: በዛ ዕድሜም ምንም ማድረግ የማይቻልበት ዘመን መሆኑን ተቀብለው እየኖሩ እንደሆነ  የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጥናቶን መሰረት አድርጎ አመልክቷል::

የዕድሜ ዘመን ቆይታን ተከትለው የሚከሰቱ ሥነ-ልቦናዊ፣ ማህበራዊ፣ አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የጤና ሁኔታ ለውጦች አረጋዊያንን ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ያደርጓቸዋል::

እ.አ.አ በ1980 የታተመ ጥናት /Glascock, /አረጋዊነት በታዳጊ ሀገራት ውስጥ የእድሜ ዘመን መግፋት፣ የማኅበራዊ ሚና እና በአቅም እና ችሎታ ላይ ለውጥ መታየት እንደሆነ አመላክቷል::

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው ደግሞ በዓለማችን ዕድሜያቸው 60 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው አረጋውያን ቁጥር እ.አ.አ በ1950 ሁለት መቶ ሚሊዮን እንዲሁም በ2000 አምስት መቶ ዘጠና ሚሊዮን ነበር:: በ2050 ደግሞ ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን እንደሚደርስ ተተንብይዋል::

በኢትዮጵያ ያለው የአረጋውያን ቁጥር በ1998 ዓ.ም ይፋ በተደረገ  መረጃ  3 ሚሊዮን 568 ሺህ 810  ነበር:: ይህም ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ሕዝብ 4 ነጥብ 8 ከመቶ  ይወክላል:: ከዚህም  54 ነጥብ 6 ከመቶ ወንዶች እንዲሁም 45 ነጥብ 5 ከመቶ ደግሞ ሴቶች ናቸው::

አረጋዊያን የራሳቸው የሆኑ መሰረታዊ መብቶች እና ፍላጎቶች አሏቸው::  ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ የሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ከአረጋዊያን ጋር ተያይዞ አስፈፃሚ አካላት መመሪያዎች፣ ውሳኔዎች እና አሠራሮች፣ ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች እና ሕጎች የማይቃረኑ መሆናቸውን የመቆጣጠር፣ ቅሬታዎችን ሲመረምር የአረጋዊያንን መብት ጥሰት የመጠበቅ፣ ፍላጎታቸውን ታሳቢ የማድረግ፣ አስፈጻሚ አካላት በኃላፊነት  የእኩል እድል ተጠቃሚ ማድረጋቸውን የመከታተል እና የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው::

በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሻሻለው የአስፈጻሚ አካላት እንደገና ማቋቋሚያ፣ ስልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 280/2014 ዓ.ም በቢሮዎች የወል ሥልጣንና ተግባር ላይ “እያንዳንዱ ተቋም በየሥራ ዘርፉ ተገቢነት ባለው መልክ የሴቶችን፣ የሕፃናትን፣ የወጣቶችን፣ የአካል ጉዳተኞችን እና የአረጋውያንን ሕገ-መንግሥታዊ እኩልነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ በዕቅድ አካቶ ይሠራል”ይላል::

በሕግ ለአረጋዊያን የተሰጧቸው መብቶች ምን ምን ናቸው?

ሰብዓዊ መብቶች ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚያገኙዋቸው  ዓለም ዓቀፋዊ፣  የማይነጣጠሉ፣ የማይገረሠሱ፣ በጾታ፣ በሃይማኖት፣ በብሄር፣ በዘር፣ በዕድሜ   እና በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ መሰረት ተደርጎ መድሎ የማይፈጸምባቸው የሰው ልጆች መብቶች ናቸው::

ምንም እንኳን እንደ ሌሎች ትኩረት እንደሚያሻቸው የማህበረሰብ ክፍሎች /ሴቶች፣ ሕጻናት እና አካል ጉዳተኞች/ ራሱን የቻለ የአረጋዊያንን መብት ሊያስከብር የሚችል ዓለም ዓቀፋዊም ሆነ ሀጉራዊ ሕግ የለም:: ሆኖም ግልጽ ባልሆነ መልኩ የአረጋዊያን መብቶች በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ሰምምነቶች ውስጥ ተካተው ይገኛሉ::

ከእነዚህም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በባህላዊ መብቶች ኮንቬንሽን (IESC) ላይ ከተቀመጡት  ውስጥ ከአረጋዊያን የሥራ ሁኔታ ጋር የተያያዙ በአንቀጽ ስድስት እና ሰባት ሰፍረዋል:: እነዚህም አረጋውያን ዕድሜያቸው በመጨመሩ  ጡረታ በመውጣታቸው ወይም በሌላ ምክንያት ቀድሞ የሚያገኙት ገቢ እየቀነሰ ይመጣል::

ለዚህም አግባብ ያለው የሥራ እድል ሊፈጠርላቸው፣ የብድር አገልግሎት እና ሌሎች ገቢ ማስገኛ ድጋፎች የሚያገኙበት መንገድ ሊመቻችላቸው ይገባል::

በሀገራችን አረጋውያን ተቀጥረው የመሥራት ዕድል ስለማያገኙ ቋሚ  ገቢ የላቸውም:: ይህን ተከትሎም መሰረታዊ አገልግሎቶችን የማግኘት ዕድል አይኖራቸውም:: ለአብነት  ለመኖር አስፈላጊ የሆኑትን መጠለያ፣ ምግብ…እንዲሁም አልባሳትን  ለማሟላት አስቸጋሪ ነው:: በዚህም አብዛኞቹ አረጋውያን  በልመና ተግባር ይተዳደራሉ:: በመሆኑም ሁኔታቸውን ያገናዘበ የሥራ ዕድል እና የብድር አገልግሎት የማግኘት መብታቸው ሲጠበቅ የሚጠቀሙት አረጋውያን ብቻ ሳይሆኑ ማህበረሰቡ ጭምር በመሆኑ መንግሥት፣ የግል ድርጅቶች፣ በጎ አድራጎት ተቋማት…ናቸው:: በመሆኑም በአጠቃላይ ለአረጋዉያን ጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ የሚገባቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል::

ማኅበራዊ ደህንነት የማግኘት መብት

የማህበራዊ ደህንነት መብት በሥራ እጦት፣ በአደጋ፣ በህመም፣ በአካል ጉዳት፣ በዕድሜ መግፋት እና በመሳሰሉት የሕይወት ክንውኖች ለሚገጥሙ ችግሮች ዜጎች መንግሥት ጥበቃ/ድጋፍ እንዲያደርግላቸው የመጠየቅ መብትን ይሰጣል:: ይህም ለድህነት ቅነሳ ዋና መንገድ ነው::

የማህበራዊ ዋስትና መብት ካለምንም መድሎ በገንዘብም ሆነ እንደ ሀገሪቱ ሁኔታ በተለያየ መልኩ አረጋውያንን እና ቤተሰቦቻቸውን አስፈላጊ የጤና አገልግሎት፣ በቂ መጠለያ እና ቤት ፣ የውሀ፣ የንጽህና መጠበቂያ እና የምግብ ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን የሚስችልነው::

ለመኖር መሰረታዊ ነገሮችን የማግኘት መብት  አንቀፅ 11 አረጋውያን ዕድሜያቸው በመግፋቱ ብቻ “ከዚህ በኋላ ለመኖር የሚያስፈልጓቸው ነገሮች የሉም” ማለት አይቻልም:: በሚኖሩበት ዕድሜ ልክ በሙሉ ጤናቸው ተጠብቆ አስፈላጊው ነገር ተሟልቶላቸው እንዲኖሩ ለማስቻል ሀገራት ኢኮኖሚያቸው በሚፈቅደው መልኩ መሟላታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ የዓለም አቀፍ ስምነቶች ሰነድ ይጠቁማል::

ዓለም ዓቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች(ICCPR) መረጃ ደግሞ አረጋዊያን ከተሳትፎ አንጻር ሀሳባቸውን የመግለጽ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት እና በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ መብቶች እንዳሏቸው አመላክቷል::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የህዳር 23  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here