በአህጉረ ደቡብ አሜሪካ ሰሜን ምስራቅ ጠረፍ ላይ ያለች የአህጉሩ አራተኛ ትንሽ ሀገር ናት። በመጠን ብታንስም ትንሿ ጉያዋ መላ አህጉሩን ወካይ እጅግ ውብ አሻራዎችን እና ገና ያልተገለጡ በርካታ ሚስጥራትን ሰውራ የያዘች አስገራሚ ምድር ናት። በአካባቢ፣ በባህል እና በተፈጥሯዊ የመሬት አቀማመጥ ፣ በፍጥረታት ብዝሀነት የታወቀች የብዝሃነት መነሀሪያ ናት። የምድር ወገብ የሀሳብ መስመር በሀገሪቱ መሀል የሚያልፍባት የምድር ወገብ ሪፐብሊክ እንደማለት በስፓኒሽኛ ኢኳዶር የተባለችውን ሀገር ለበኩር ሽርሽር መርጠናታል፣ መልካም ንባብ።
“የአራት ዓለማት ሀገር” በሚል ቅፅል ስም ይጠሯታል፤ ምክንያቱም ከፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ እስከ አማዞን ጫካ የተዘረጋ፣ አስደማሚው የኤንደስ ተራራ ሰንሰለት እና አስደማሚው የጋላፓጎስ ደሴቶች መሀል አልፎ የሚሄድ ድንቅ ጅኦግራፊያዊ ብዝሃነት ያላት ሀገር በመሆኗ ነው የአራት ዓለማት ሀገር እያሉ የሚጠሯት። እያንዳንዱ ክልል የራሱ የሆነ ልዩ ባህል አለው፤ ከአለባበስ እስከ ምግብ ድረስ ሁሉም ነገር ይለያያል። እንዲያውም በኢኳዶር በተለይ በገጠር የሚኖሩ ተወላጆች የሚጠቀሙባቸው ቋንቋዎች ይለያያሉ። እንደ ኪችዋ ባሉ የክልል ቋንቋዎች ላይ ስፓኒሽ በሀገሪቱ ውስጥ የበላይ እየሆነ በመምጣቱ እንደ ብሔራዊ ቋንቋ ያገለግላል።
ኢኩየተር ዛሬ የምናውቃት ነጻ ሀገር ከመሆኗ በፊት ማእከሉን ፔሩ በነበረው ጥንታዊው የኢንካ ግዛት እና በኋላም በስፔን ቅኝ ትገዛ ነበር። የስፔን ወረራ የጀመረው በ1526 ዓ.ም ሲሆን ኢኳዶር እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ለ300 ዓመታት ያህል በስፔን ቅኝ ግዛት ሥር ቆይታለች። ይህ የቅኝ ግዛት በኢኳዶር ባህል፣ ስነ ሕንፃ እና ብሔራዊ ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።
ኢኳዶር ከስፔን ነፃ ከወጣች በኋላ ከቬንዙዌላ፣ ኮሎምቢያ እና ፓናማ ጋር በመተባበር ታላቋ ኮሎምቢያን መሰረተች። ነገር ግን ህብረቱ ከ1811 እስከ 1822 ዓ.ም ድረስ ብቻ ነበር የቆየው እና ፈረሰ። ከዚያ በኋላ ኢኳዶር ራሷን የቻለች ሪፐብሊክ ሆነች።
ኢኳዶር እስከ 1822 ዓ.ም ድረስ ሙሉ በሙሉ ነፃ የሆነች ሪፐብሊክ ባትሆንም በ1822 ዓ.ም የፒቺንቻ ጦርነትን ተከትሎ ግዛቱ ከስፔን ነፃነቷን አገኘች። ይህንን በደቡብ አሜሪካ ታሪክ ውስጥ ጉልህ የሆነ ታሪካዊ ክስተት በማስታወስ ግንቦት 24 ቀን በኢኳዶር የነፃነት ቀን ተብሎ ይከበራል።
ውብ ተፈጥሯዊ አቀማመጠ የታደለች፣ አቅፋ ከያዘቻቸው ብርቅየ አእዋፋት እና እንስሳት ከሌላው የዓለማችን ቦታዎች የተለየች እና ውበት የደረበች ድንቅ ተመራጭ መዳረሻ ናት፣ ኢኳዶር።
የጋላፓጎስ የደሴቶች ስብስብ ኢኳዶር በአብዛኛው የምትታወቅበት አንድ እሴቷ ነው። በምድራችን ጋላፓጎስ ደሴቶችን የሚመስል ምንም ነገር የለም ነው የሚባለው፤ ሙሉ ለሙሉ የተገለሉ እና እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሰዎች ያልሰፈሩባቸው በመሆኑ በደሴቶቹ ዛፎች እና እንስሳት በተለየ መንገድ ተራብተዋል፤ ይህም በሌላው ዓለም የሌሉ ዝርያዎች እንዲነሱ አድርጓል። የጋላፓጎስ ደሴቶች በፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ ከኢኳዶር ምእራብ ዳርቻ 1ሺ ኪሎ ሜትር ራቅ ብለው የሚገኙ የሀገሪቱ አካል ናቸው። ይህ የደሴቶች ስብስብ ልዩ በሆነው ብዝሃሕይወት እና በቻርልስ ዳርዊን ቲወሪ ኦፍ ኢቮሉሽን ላይ ባላቸው ሚና ዓለማቀፍ እውቅናን ተቀዳጅተዋል። እነዚህን ደሴቶች ለማየት መታደል ከጉብኝት ያለፈ ትርጉም ያለው ራስን በምድር ላይ የሕይወት ድንቃ ድንቅ መሀል እንደመነከር ያህል ነው።
በ1827 ዓ.ም ቻርለስ ዳርዊን የጋላፓጎስ ደሴቶችን መጎብኘት ተከትሎ በናቱራል ሴሌክሽን ኦፍ ኢቮሉሽን ንድፈ ሀሳብ ዙሪያ ወሳኝ ማስረጃዎችን አቅርቧል። በደሴቶቹ ላይ በሚገኙ የአእዋፍ ዝርያዎችና ሌሎች የዱር አራዊት መካከል የተመለከታቸው ልዩ ማስተካከያዎች በ1851 ዓ.ም ለታተመው “የዝርያ አመጣጥ” ለተሰኘው ታላቅ ሥራ መሠረት ሆነዋል።
የጋላፓጎስ ደሴቶች ከ 9,000 የሚበልጡ የተለያዩ ዝርያዎች መኖሪያ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ በምድር ላይ በየትኛውም ቦታ ሊገኙ አይችሉም፡፡ ከእነዚህ ያልተለመዱ ዝርያዎች ውስጥ የባህር ኢጉዋናስ፣ ግዙፍ ኤሊዎች፣ ሰማያዊ እግር ያላቸው ቡቢዎች እና የዳርዊን ፊንችስ ይገኙበታል። የደሴቶቹ መገለል ለዝግመተ ለውጥ የተፈጥሮ ላብራቶሪ ፈጥሯል, ለሳይንቲስቶች ጠቃሚ ግንዛቤዎችን መስጠቱን ቀጥሏል።
ሀገሪቱ ኢኳዶር የተባለችው ኢኳቶር(የምድር ወገብ) በውስጧ ስለሚያልፍ ሲሆን ይህ በዓለም ላይ በጂኦግራፊያዊ ባህሪ መነሻነት ስሟ የተሰየመ ብቸኛ ሀገር ያደርጋታል። ከዋና ከተማዋ ከኩዊቶ ወጣ ብሎ ሚታድ ዴል ሙንዶ (የአለም መሃል) የሚባል ዝነኛ ሀውልት አለ፤ በኢኳቶሪያል የሀሳብ መስመር ላይ። በእውነቱ፣ ሃውልቱ ከትክክለኛው ወገብ 240 ሜትሮች ይርቃል፣ ግን አሁንም ጥሩ ጉብኝት ነው። እዚያ ሙዚየም እና ጥቂት የገበያ መሰል ሱቆች እና ምግብ ቤቶች አሉ።
በተጨማሪም በመታሰቢያ ሐውልቱ ላይ መውጣት እና የኢኳዶርን እይታዎች ከላይ መመልከት ይቻላል። “እውነተኛ” ኢኳተርን የሚያመለክት መስተጋብራዊ ሙዚየም ነው፡፡ ምንም እንኳን የምድር ወገብ 5 ኪሎ ሜትር ስፋት ቢኖረውም ሁለቱም ሙዚየሞች በምድር ወገብ ላይ ይገኛሉ ለጠፈር በጣም ቅርብ የሆነች ሀገር ናት። ከኤቨረስት የበለጠ ቅርብ ናት። ምክንያቱ ምድር ፍፁም ጠፍጣፋ የሆነች ሉል አይደለችም ከሚለው ሀቅ ጋር ይገናኛል። በምድር ወገብ ላይ አበጥ ብላ ትወጣለች። ኢኳዶር የሚቀመጠው በዚያ ጉልላት ላይ በመሆኑ ረጅሙ ተራራው የቺምቦራዞ ተራራ ከምድር መሀል በፕላኔታችን ላይ ካሉት ከማንኛውም ነጥቦች ርቆ ይገኛል። በመሆኑም በከፍታው ላይ በቆማችሁ ጊዜ በኤቨረስት ላይ ካለ ከማንኛውም ሰው ይልቅ በአካል ወደ ጠፈር ትቀርባላችሁ። ለጨረቃ ብቸኛው ቅርብ ስፍራም ነው።
በብዙ የኢኳዶር አካባቢዎች በተለይም በአንዲያን ክልል ካለው ከፍታ የተነሳ ውሃ ከመደበኛው 100°C (212°F) ባነሰ የሙቀት መጠን ይፈላል። ከባህር ጠለል በላይ በግምት 2,850 ሜትሮች ላይ በምትቀመጠው ዋና ከተማ ኩዊቶ ውስጥ ውሃ በ91°ሴንቲግሬድ ወይም (196°F) አካባቢ የሚፈላበት የዓለማችን ብቸኛ ስፍራ ያደርገዋል።
ኢኳዶር ለተፈጥሮ ሕገ-መንግሥታዊ የሕጋዊ ሰውነት መብቶችን የሰጠች የመጀመሪያዋ ሀገር ናት። እ.ኤ.አ. በ 2008 ኢኳዶር ሕገ መንግሥቷን እንደገና ጽፋ እና ተፈጥሮን እንደ ሕጋዊ አካል በመቁጠር የመብት እውቅና የሰጠች የመጀመሪያ ሀገር ሆነች። ያም ማለት ወንዞች፣ ደኖች እና አጠቃላይ ስነ-ምህዳሮች ልክ እንደ አንድ ሰው የመኖር፣ የመብቀል እና የመልሶ የመልማት ሕጋዊ መብት አላቸው ማለት ነው። ይህ እርምጃም ሌሎች ሀገሮችን አነሳስቷቸዋል።
አጭር እውነታ
o ቦታ፡- ምዕራብ ደቡብ አሜሪካ፣ ኢኳቶር ላይ ከፓስፊክ ውቅያኖስ ጋር፣ በኮሎምቢያ እና በፔሩ
መካከል ይገኛል፡፡
o የህዝብ ብዛት፡ 13,183,978 (ሐምሌ 2001 እ.ኤ.አ.)
o አጠቃላይ ስፋት:- 283,560 ካሬ ኪሎ ሜትር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 276,840 ካሬ ኪሎ ሜትር
ያህሉ የብስ ሲሆን በውሃ የተሸፈነው 6,720 ካሬ ኪሎ ሜትር ይገመታል፤ ይህ የውሃ ክፍል
የጋላፓጎስ ደሴቶችን ያካትታል።
o የአየር ንብረት፡- ሞቃታማ የባህር ዳርቻዎች፣ ከፍ ባለ ቦታ ላይ ወደ ውስጥ ቀዝቀዝ ያለ
መሆን፣ ሞቃታማ የአማዞን ጫካ ቆላማ አካባቢዎች
o የመሬት አቀማመጥ፡- የባህር ዳርቻ ሜዳ (ኮስታ)፣ የአንዲያን ማእከላዊ ደጋማ ቦታዎች (ሴራራ)
እና ጠፍጣፋ እስከ ተንከባላይ ምስራቃዊ ጫካ (ኦሪየንቴ)
o የመገኛው ልኬታ፡-ዝቅተኛው ነጥብ: የፓሲፊክ ውቅያኖስ 0 ሜትር
o ከፍተኛ ነጥብ:- የችምቦራዞ ተራራ 6,267 ሜትር።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የህዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


