የአራጣ ወንጀል

0
230

አራጣ ማለት በሕግ ከተፈቀደው በላይ በሆነ የወለድ ምጣኔ ገንዘብ ማበደር ነው::  የአራጣ ብድር ድርጊት  በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑም በግልጽ ተደንግጓል:: ይህን አስመልክቶም በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀሎች አቃቢ ሕግ  አቶ ዓለምነህ ሹመቴ  አብራርተውልናል::

እርሳቸው እንደሚሉት በሰዎች መካከል በገንዘብ እና በቁሥ መበዳደር እና መተጋገዝ ይኖራል:: ነገር  ግን

ገንዘብን ወይም ቁስን  በወለድ ማበደር በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖታዊ አስተምህሮ የተወገዘ ተግባር ነው:: የሀሳቡ መነሻ ደግሞ መገበያያ ገንዘብ እንደ ንብረት ስለማይቆጠር እና እራሱም ምንም ብክነት ሆነ ጉድለት ሳይደርስበት ለአበዳሪው ስለሚመለስ እና አበዳሪውም ምንም አይነት አስተዋፅኦ ያላበረከተበት ስለሆነ ባበደረው ገንዘብ ላይ ወለድ መቀበል የለበትም የሚል ነው::

እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባ በብድሩ ላይ ምንም አይነት ወለድ ማሰብ የተከለከለ መሆኑን ነው:: ነገር ግን መገበያያ ገንዘብ በኢኮኖሚ ውስጥ ብቸኛ የሆነ የደም ስር እየሆነ ሲመጣ ይህንን ገንዘብ በባንኮች አማካኝነት ማስቀመጥ፣ ማዘዋወር እና ለኢንቨስትመንት ማበደር ሲጀመር በብድር በሚሰጥ ገንዘብ ላይ እንደ ፋይናንስ ገበያው ወይም ብሔራዊ ባንኮች በሚወስኑት መሰረት ተመጣጣኝ የሆነ ወለድ ማሰብ ተገቢ እና አስፈላጊ መሆኑ በዘመናዊው ኢኮኖሚ መዋቀር ታመነበት::

ነገር ግን በዘመናዊው የኢኮኖሚ መዋቅርም ቢሆን ከፍተኛ የወለድ መጠን ለኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ብሎም ፖለቲካዊ ጉዳቶች ምክንያት ስለሚሆን ሀገራት ከፍተኛውን የወለድ ምጣኔ ይወስናሉ:: ይህንን ጉዳት ለመከላከል በማሰብም ጉዳዩ በወንጀል የሚያስቀጣ ሆነ:: በሕግ ከተወሰነው የወለድ ምጣኔ በላይ ገንዘብ ማበደር በብዙ ሀገራት ዘንድ ወንጀል ተደርጎ ተደንግጓል፤ ወንጀሉም አራጣ በመባል ይታወቃል::

ይህ አስተሳሰብ የተወሰኑ ከፍተኛ ገንዘብ ያላቸው ባለሃብቶች አቅሙ ዝቅ ያለን ግለሰብ እያስፈራሩ የግል ተላላኪ እና ንብረት እንዲወረስ የሚዳርጉ ናቸው::

በኢትዮጵያ ሕግም  ከተፈቀደው የወለድ ጣሪያ በላይ  ማበደር እንደ ወንጀል ተቀምጧል:: የአራጣ ወንጀልን አስመልክቶም የተደነገገው በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ ነው::

የወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 712 የአራጣ ወንጀልን እንደሚከተለው ይተረጉመዋል::

“ማንም ሰው የተበዳዩን ችግረኝነት፣ የበታችነቱን ወይም የገንዘብ ችግሩን ወይም መንፈሰ ደካማነቱን ወይም ልምድ ወይም ችሎታ የሌለው መሆኑን መሰረት በማድረግ በሕግ ከተፈቀደው ወለድ በላይ ገንዘብ ያበደረ እንደሆነ ወይም  ካበደረው ገንዘብ ጋር በግልፅ ተመጣጣኝነት የሌለው ንብረት በምትኩ እንዲሰጠው ያደረገ ወይም ቃል ያስገባው እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም  ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ያስቀጣል’’ በሚል::  በተመሳሳይ ሁኔታ ማንኛውም ሰው  በአራጣ ላይ የተመሰረተ መብት የተቀበለ፣ በመከላከያነት የተጠቀመበት ወይም ለሌላ ሰው ያስተላለፈ እንደሆነ በተመሳሳይ ሁኔታ ይቀጣል::

አቶ ዓለምነህ እንደሚሉት ወደ አራጣ ከሚያመሩ ምክንያቶች ድህነትን ለማሸነፍ፣   ነግዶ ለማትረፍ የሚያጋጥም እዳ ነው:: የተበደረው ሰው ገንዘቡን እንደ ሁኔታው ለፍጆታ ወይም ለኢንቨስትመንት ሊያውለው ይችላል:: ድህነት በሰፈነበት ኢኮኖሚ ውስጥ ሰዎች እሉታዊ ችግራቸውን ለመቅረፍ ሲሉ ከፍተኛ ወለድ የሚታሰብበት  ብድር ለመውሰድ ይገደዳሉ::  በድህነት ከሚኖረው ማህበረሰብ ውስጥ ጥቂትም ቢሆን ጥሪት ያላቸው ሰዎች የአበዳሪነት ሚና በመያዝ በዝባዦች ሁነው ይሰየማሉ::

ከድህነት አስከሚወጣም ድርጊቱ ቀጣይ ይሆናል ማለት ነው:: በሌላ አገላለፅ ድህነት መገለጫው ባልሆነ ማህበረሰብ ውስጥም ሰዎች ለኢንቨስትመንት ሲሉ በአራጣ ይበደራሉ:: በዚህ ሁኔታ ለአራጣ ብድር መንስዔው ቀልጣፋ እና በቂ የፋይናንስ አገልግሎት አለመኖር ነው:: የፋይናንስ አገልግሎት ሰጭዎች ባንኮችን፣ ማይክሮ ባንኮችን…ያጠቃልላል::

መንግሥት ከፍተኛውን ግዥ ወይም ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ በሆነበት ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግሥት የግዥ እና ክፍያ አፈፃፀም ቅልጥፍና እና ግልፅነት አለመኖር ለአራጣ ብድር መንስዔ ሊሆን ይችላል:: አስተማማኝ የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት አለመኖር ሰዎች የአራጣ ብድር መውሰድን እንደ አማራጭ እንዲያዩ ያደርጋቸዋል:: ምክንያቱም ሰዎች የፋይናንስ ክፍተታቸውን ለመሙላት በሚያደርጉት ጥረት የፋይናንስ ተቋማት በጊዜ ሊደርሱላቸው ካልቻሉ በአራጣ ለመበደር ስለሚገደዱ ነው::

የአራጣ ወንጀል ጉዳቶች የአራጣ ወንጀሎች መጠናቸውና ግዝፈታቸው በጨመረ ቁጥር ከፍተኛ  ሀገራዊ ጉዳት ብሎም ሀገራዊ ህልውና ላይ ፈተና የሚጋርጡ ናቸው:: እነዚህ ወንጀሎች ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳት ቢኖራቸውም በጣም የከፋውን ጉዳት የሚያደርሱት ግን በኢኮኖሚ ላይ ነው::

ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች በአሁኑ ወቅት የዓለም ኢኮኖሚ በአጠቃላይ በሚባል ሁኔታ የሚንቀሳቀሰው በወለድ መርህ ነው:: በኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ንብረት ተመጣጣኝ የሆነ የገንዘብ ዋጋ እንዳለው ይታሰባል:: ገንዘብም በኢኮኖሚ ውስጥ ዕቃዎችን ለመግዛት፣ ኢንቨስት ለማድረግ፣ ምርቶችን ለመለዋወጥ እና ግዴታዎችን ለመወጣት  ብቸኛው መሳሪያ ነው:: ስለሆነም ይህንን ገንዘብ በኢኮኖሚ ውስጥ ተዋናይ ለሆኑ አካላት በማቅረብ የማይተካ ሚና ያላቸው የፋይናንስ ተቋማት ናቸው:: ዋነኞች የፋይናንስ ተቋማትም ባንኮች ይህንን ሥራ በሚያከናውኑበት ወቅት የሚመሩት ገንዘብ በሚበደሩት እና በአስቀማጮች ላይ በሚሰላ ወለድ ነው:: ሆኖም ይህ የባንኮች የወለድ መጠን መሬት ላይ ያለውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ(ገበያ) መሰረት የሚያደርግ እንጅ በዘፈቀደ የሚወሰን ወይም የተጋነነ አይደለም::

የወለድ መጠኑ የተጋነነ (አራጣ) ሲሆን የሚከተሉት ጉዳቶች አሉት:: የመጀመሪያው ጉዳት የአራጣ ወንጀል ከመነሻው በወንጀል ሕጉ በተደነገጉ ምክንያቶች ያልተገባ የወለድ ስሌት ተበዳሪዎችን በማስከፈል የሚፈፀም ነው:: እነዚህ ተበዳሪዎች እንዲከፍሉ የሚጠየቁት የወለድ መጠን በጣም የተጋነነ ስለሆነ ብድሩን መልሰው ሲጨርሱ ወይም በመካከል  ያላቸውን ሀብት ወይም በብድሩ ገንዘብ ሠርተው ያገኙት ትርፍ አበዳሪው ስለሚወስድባቸው ለኪሳራ ይዳረጋሉ:: ጥሪታቸውን ሁሉ ለአበዳሪያቸው አስረክበው ከሥራ ውጭ  እንዲቀመጡ ያደርጋል:: በዚህ ወቅት ምርትም ይቆማል ማለት ነው::

ተበዳሪዎች ጊዜያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ብለው በተበደሩት ገንዘብ ድህነትን ሸምተው ድሀ ሆነው ሲቀሩ፤ አበዳሪዎችም ምንም እሴት በኢኮኖሚ ውስጥ ሳይጨምሩ ሀብት የሚሰበስቡበት ሁኔታ ይፈጥራል:: ይህ ክስተት(ኢኮኖሚያዊ ጉዳት) በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው እና በአገልግሎት ክፍለ ኢኮኖሚዎች ላይ ሁሉ የሚሆን ነው::

ሁለተኛው ጉዳት የሚያያዘው ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ገንዘባቸውን ባንክ እንዳያስቀምጡ ከማድረግ ጋር የተያያዘ ነው:: ይህ ጉዳይ የሚከሰተው ጥቂትም ቢሆን ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ገንዘባቸውን ወደ ባንክ በማስቀመጥ ፋንታ አራጣ በማበደር እንዲሰማሩ ማድረጉ ነው:: ይህም ገንዘቡ በባንክ ተቀምጦ ለኢኮኖሚው ሊያበረክተው የሚችለውን አስተዋጽኦ ያስቀረዋል:: ወደ ባንኮች የሚሄደው ተቀማጭ እየቀነሰ መሄዱ በመጨራሻም ባንኮች አቅም እያጠራቸው እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል::

ባንኮች ለብድር የሚውል ተቀማጭ ገንዘብ እያጠራቸው ሲሄድ በተዘዋዋሪ አራጣ አበዳሪዎች የብድር አማራጭ እየሆኑ ይሄዳሉ:: ይህ መሆኑ ደግሞ በተመጣጣኝ ወለድ  ገንዘብ ተበድረው  ሊሠሩ የሚችሉ ሰዎች ብድር ሳያገኙ እንዲቀሩ በአራጣ ቢወስዱም እንኳ ውጤታማ ሳይሆኑ እንዲቀሩ ያደርጋል::

ሦስተኛው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በጣም አቅም ያላቸው ሰዎች ወደዚህ ወንጀል ሲሰማሩ የሚከሰተው አይነት ነው:: ከፍተኛ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች አራጣ ማበደር ሲጀምሩ ተጽዕኖው እየከፋ በመሄድ ባንኮች የብሄራዊ ባንክ መመሪያዎችን በመከተል ሥራቸውን ማከናወን  ከማይችሉበት ደረጃ ያደርሳቸዋል::

አራጣ የሚያበድሩ ሰዎች ምንም አይነት መመሪያ የማይከተሉና ከወለዱ መብዛት በቀር ቀለል  ያለ ውጣ ውረድን የማይጠይቁ ስለሆነ ተበዳሪዎችን በመሳብ የባንኮችን ሥራ ወደ መጋራት ደርሰዋል:: ከዚህ ባለፈም አበዳሪዎች ተበዳሪዎችን በመምረጥ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር እንዲፈጠር ያደርጋሉ፤ ተበዳሪዎች የተበደሩትን ገንዘብ የሚያውሉበትን የሥራ መስክ በመምረጥ ገንዘባቸው የሚመለስበትን ሁኔታ ብቻ በማመቻቸት ዘላቂ ልማት እና እሴት በማይጨምር መልኩ የሀገር ሀብት እንዲባክን ደደርጋሉ:: ይህ ተፅዕኖ በጣም ሲከፋም በዚህ ወንጀል ውስጥ ባንኮች እስከመሳተፍ የሚደርሱበት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል::

የመጨረሻው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በመንግሥት ላይ በቀጥታ የሚደርሰውን የሚመለከት ነው:: በአራጣ በሚዘዋወረው ገንዘብ ላይ መንግሥት እውቅና የሌለው ስለሆነ ከትርፉ ላይ ግብር ስለማይከፈል መንግሥት ገቢ ሳይሰበስብ ይቀራል:: ከፋይናንስ አገልግሎት ገቢ ሳይሰበሰብ መቅረቱ መንግሥትን ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስበት ይሆናል::  ማህበራዊ ጉዳቶች ከሞላ ጎደል ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች የሚመዙት ችግር ነው:: የኢኮኖሚ እድገቱ በመጎተቱ ምክንያት ወይም በየደረጃው ያሉ የግል ተበዳዩች በቀጥታ ለማህበራዊ ዝቅጠት ይዳረጋሉ::

ማህበራዊ ቀውስ የመጨረሻው ውጤት ይሆናል:: ፖለቲካዊ ጉዳቶች የኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውሶች በሚያመጡት ውጤት ወይም ከፍተኛ አቅም ያላቸው አራጣ አበዳሪዎች ፖለቲካውን ማለትም የመንግሥትን ሥልጣንና ፖሊሲዎችን በመዘወራቸው የሚገለፁ ናቸው::

በአጠቃላይ አራጣ የህሊና ፣ የሃይማኖት፣ የአስተዳደር፣ የወንጀል እና የፍትሐብሄር ተጠያቂነት ያለው ድርጊት  ነው ያሉት  አቶ ዓለምነህ ይህንን ችግር ለማስተካከል ደግሞ ችግሩ ከማሕበረሰቡ በመነሻነት መቅረብ እና ጥቆማ ማድረስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል::

( ማራኪ ሰውነት)

በኲር የታኅሳስ 14  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here