ለግብርናው ዘርፍ ተግዳሮት የሆነውን የአሲዳማ አፈር ችግርን ለመፍታት መንግሥት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ:: “የአፈር ጤና ለሀገር ህልውና” በሚል መሪ ሃሳብ የ2016/17 ምርት ዘመን ሀገራዊ የግብርና ኖራ አቅርቦት እና ስርጭት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ከሰሞኑ ተካሂዷል::
ከግብርና ሚኒስቴር የማሕበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ እንዳመለካተው የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል እና የክልል አመራሮች በተገኙበት የግብርና ኖራ አቅርቦትና ስርጭት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል::
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ለምርትና ምርታማነት ማነቆዎች ከሆኑት መካከል አንዱ የአሲዳማ አፈር መስፋፋት ነው:: ስርጭቱ እና መጠኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል:: በመሆኑም መንግሥት ለአሲዳማ አፈር ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የግብርና ኖራን በግብርና ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ እንዲካተት በማድረግ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ሆኗል::
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር ጤንነትን መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በመናበብ እና በመግባባት መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም