የአብነት ትምህርት እና አበርክቶዉ

0
196

መምህር ኪዳነ ማርያም ጌታሁን ጥንታዊ የቆሎ ተማሪ በተሰኘ መጽሐፋቸው የቆሎ ተማሪን ‘ዘአልቦ ጥሪት’ ርስት የሌለው ሲሉ ይገልጹታል፡፡ የቆሎ (የአብነት) ተማሪ የቤተ ክህነት ዕውቀት ፍለጋን ሽቶ ከዘመድ ርቆ ይሰደዳል፡፡ የሚበላው፣ የሚጠጣው፣ የሚለብሰው፣ የሚኖርበት ሁሉ ጉዳዩ አይደለም፡፡ የቆሎ ተማሪዉ ጎጆን መኖሪያው አድርጎ ሲማር የነገ ሕያው ሊቅ መሆንን ራዕዩ አድርጎ ነው፡፡ የዳስ ቤት ብዙ ምቾት የለውም፤ በጋ ለፀሐይ፣ ክረምት ለዝናብ የተጋለጠ ነው፡፡

 

ሀገሬው የአብነት ትምህርትን በብዙ መንገድ ይጠራዋል፡፡ “የቆሎ ትምህርት ቤት፣ የቄስ ትምህርት ቤት፣ የቤተ ክህነት ትምህርት ቤት… በሚል ይታወቃል፡፡ መምህር ልዑለቃል አካሉ በክብረ ቅዱሳን ዶት ኦርግ (kibreqidusan.org) ድረ ገጽ ላይ ባጋሩት ጽሑፍ የአብነት ትምህርት የቆሎ ተማሪ ስያሜን እንዲይዝ የሆነው የተማሪዎቹን አመጋገብ እና የችግር ኑሮ የሚገልጥ በመሆኑ ነው፤ እንጂ የትምህርት ቤቱን ማንነት እና ዓላማ የማያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

የቄስ እና የቤተ ክህነት ትምህርት ቤተ መባሉ ግን የጥንታዊው ትምህርት ባለቤቶች፣ የሥርዐተ ትምህርቱ ቀራጮች እና መምህራኑ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች መሆናቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ በተጨማሪም የሃይማኖት አባቶች የጥንታዊ ሥልጣኔ መነሻዎች እና የዘመናዊ ትምህርት መሠረት መሆናቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ትክክለኛው ስያሜ “የአብነት ትምህርት ቤት” መሆኑን መምህር ልዑለቃል አካሉ ገልጸዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ማኅበረ ቅዱሳን የአብነት ትምህርት ከአባት የተገኘ፣ ከአበው የተወረሰ፣ ከጥንት የነበረ፣ የማንነት መገለጫ፣ በራስ ቋንቋ እና በራስ ፊደል፤ በራስ ሥራተ ትምህርት የሚሰጥ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ የትምህርት ሥርዓት ሲል ይገልጹታል፡፡

የአብነት ሥርዐተ ትምህርት ሀገር በቀል ቋንቋ እና ዕውቀት በዘርፉ በተካኑ ምሁራን /ሊቃውንት ይሰጣል፡፡ የአንድን ሀገር ጥንታዊ ሥነ ጥበብ፣ ፊደል፣ ዜማ፣ ባሕል፣ ሥነ ሥርዐት፣ ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ለዛ፣ ዘዬ፣ ወግ እና ማዕርግ በልዩ ልዩ አቀራረብ የሚሰጥ የትምህርት ሥርዓት መሆኑን መምህር ልዑለቃል አካሉ ገልጸዋል፡፡ የአብነት ትምህርት ዓለም አቀፋዊ ዕውቀትን የሚያንጸባርቅ፣ ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸውን ትምህርቶች በሀገራዊ ደረጃ የሚያቀርብ የመንፈሳዊ ትምህርት ሥርዓት አይነት ነው፡፡

 

የአብነት ትምህርት ለዘመናዊ ትምህርት መነሻ ከመሆንም ባሻገር ለቤተ መንግሥት እና ለኅብረተሰቡ ከፍተኛ አበርክቶ ጥለው ማለፋቸውን መምህር ልዑለቃል አካሉ  አብነቶችን እያነሱ ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ ባለፉት ዘመናት የነበሩት የኢትዮጵያ ነገሥታት የአብነት ትምህርትን የተማሩ፣ ሕዝባቸውን የሚመሩበትን ሕግ እና ጥበብም የተማሩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መምህራንም (ሊቃውንት) የነገዎቹን የሀገር መሪዎች የዛሬዎቹን ደቀ መዛሙርቶቻቸውን በሃይማኖት እና በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በሕግ እና ሥርዐት እንዲያስዳድሩ ያሰለጥኗቸው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ መምህር ልዑለቃል አካሉ ለዚህ ምሳሌ የጠቀሱት አባ ኢየሱስ ሞዐ የአፄ ይኩኖ አምላክ መምህር መሆናቸውን ነው፡፡ በዛጉዬ ዘመነ መንግሥት ሆነ በላሊበላ እና በአክሱም ዘመን የነበሩ ነገሥታት ካህናት መሆናቸውን በተጨማሪነት ጠቅሰዋል፡፡

 

የአብነት ትምህርት ቤት የሚሰጠው ራሳቸውን በቻሉ የትምህርት ዘርፎች (የጉባኤ ቤቶች)በተከፋፈለ እና ሥርዓትን በተከተለ መንገድ መሆኑን የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ መረጃ ያሳያል፡፡ ንባብ ቤት፣ ዜማ ቤት፣ አቋቋም ቤት፣ ቅኔ ቤት፣ ቅዳሴ ቤት እና መጻሕፍት ቤት ሲሆኑ ከዚህ በተጨማሪ  ባሕረ ሓሳብ (አቡሻሐር) እና አክሲማሮስ ራሳቸውን በቻሉ ጉባኤ ቤቶች ይሰጡ እንደነበር ተመልክቷል።

የአብነት ትምህርት ደረጃዎችን በተመለከተ ሰፋ ያለ ጽሁፍ ያጋራው ደግሞ አንደኛ ብሎግ ፖስት ዶት ኮም andegna.blogspot.com ነው፡፡ የመጀመሪያው የአብነት ትምህርት ደረጃ የንባብ ትምህር ነው፡፡ ይህም ከፊደል ጀምሮ እስከ መዝሙረ ዳዊት፤ ቁጥር፣ ግእዝ ንባብ፣ ውርድ ንባብ፣ እና ቍም ንባብ ክፍሎችን ያጠቃልላል፡፡

 

ሁለተኛው ዳረጃ ደግሞ “ፀዋትወ ዜማ” ወይም የዜማ ክፍል የሚባለው ነው፡፡ ማሪው የዜማ ትምህርቱን “ሰላም ለኪ” ይልና በውዳሴ ማርያም ዜማ ትምህርቱን ይጀምራል፤ በመቀጠልም ጾመ ድጓ፣  መዝገበ ድጓ፣ መዋሥዕት፣ ዝማሬ፤ አቋቋም ወይም ዝማሜ፣ መረግድ፣ ጽፍት የሚማርበት ነው፡፡

የቅኔ ትምህርት ሦስተኛው የአብነት ትምህርት ደረጃ ሲሆን የሚጀምረውም የግእዝን ቋንቋ በመማር ነው፡፡ ተማሪው መጀመሪያ የግእዝን ቋንቋ የአማርኛ ትርጉም እና የቃላቱን መዋቅር ባሕርይ ሥራና ጠባይ ወዘተ ይማራል፤ በመቀጠልም አብሮ ከቋንቋው ጥናት ጋር የቅኔን መንገድ እና መዋቅር መምህሩ በሚነድፍለት መዋቅር ድርሰት እየደረሰ ቅኔን የሚፈጥርበት ደረጃ ነው፡፡

ትርጓሜ መጻሕፍት የሚባለው የትምህርት ክፍል ከስያሜው እንደምንረዳው የቅዱሳት መጻሕፍትን ተደራራቢ ትርጉም እና ምሥጢር በማመሥጠር እና በማራቀቅ ታሪካዊ ምንጫቸውን እና ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መንፈሳዊ መልእክት በመረዳት ማስረዳት ነው፤ የትርጓሜ መጻሕፍት ትምህርትን መማር የሚችለው የቅኔ ትምህርትን የተማረ ተማሪ ብቻ ነው።

 

በአጠቃላይ በአብነት ትምህርት ሕግ አንድ ተማሪ የመጀመሪያውን ደረጃ በአግባቡ እስካላጠናቀቀ ጊዜ ድረስ ቀጣዩን ደረጃ አይጀምርም፡፡ ይህም ብቁ እና አገልጋይ አባቶችን ለማፍራት ትልቅ ጉልበት ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ጥንታዊ የአብነት ትምህርት ቤቶች የሀገራዊ ችግር መፍቻ ትልቅ አቅም እንደሚሆኑም ይታመናል፡፡ እንዴት ከተባለ የአብነት ትምህርት ቤቶች ትውልድ በስነ ምግባር የሚታነጽባቸው፣ ግብረ ገብነት መገለጫቸው የሆኑ በመሆናቸው ነው፡፡ ይህንንም ሀገራዊ ፋይዳ ዕውን ለማድረግ የዘርፉን ሊቃውንት መታደግ፣ ቁጥራቸውንም ማብዛት ይገባል፡፡

 

መሠረቱን ኢትዮጵያ ያደረገው እና የአብነት ትምህርት ዋና ማጠንጠኛ የሆነው ግዕዝ ከእኛ በላይ በአውሮፓ ሀገራት (ጀርመን) የበለጠ ምስጢራዊነቱ ተገልጦ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ በአብነት ትምህርት ቤት ሃይማኖት፣ ትውፊት፣ ሥርዐት፣ ወግ፣ ልማድ፣ ቋንቋ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ዜማ፥ ትርጓሜ መጻሕፍት፣ ሥርዐተ ማኅሌት፣ ክብር እና ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍ ችለዋል። “ባሕልና ክርስቲያናዊ ትውፊት በኢትዮጵያ” በተሰኘው የካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔር  መጽሐፍ የአብነት ትምህርት ቤቶች ነባሩን ባሕል እና ወግ ጠብቀው እንዲሻገሩ ከዘመናዊው ትምህርት ጎን ለጎን ትኩረት ተሰጥቶ ሊቀጥል እንደሚገባ ጽፈዋል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here