የአትሌቲክስ ተሰጥኦ እንዴት ይለያል?

0
76

ኢትዮጵያ ለአትሌቲክስ ስፖርት የማይነጥፍ የተፈጥሮ ፀጋ ያላት ሀገር ናት። በየርቀቱ እንደ አብሪ ኮከብ የሚወረወሩ አትሌቶች የሚፈለፈሉባት ሀገር ጭምር ናት። ይሁን እንጂ ዛሬም በቆየው ባህላዊ የስልጠና ሂደት እና አስተሳሰብ መመራታችን ዓለም ከደረሰበት የስልጠና መንገድ  በብዙ ወደ ኋላ ለመቅረት ተገደናል።

 

ከዚህ በፊት ነጮች በአትሌቲክሱ ዘርፍ ኢትዮጵያውያንን፣ ኬኒያውያንን፣ ኡጋንዳውያንን እና የመሳሰሉትን ሀገራት አትሌቶች በገንዘብ በማስኮብለል ነበር ውጤታማ ሲሆኑ የሚስተዋሉት። አሁን ላይ ግን የስልጠና ደረጃቸውን እጅግ በማዘመናቸው አትሌቶቻቸው ከምስራቅ አፍሪካውያን አትሌቶች ቀድመው እንዲታዩ ሲያደርጉ እኛ ግን ባለንበት ተቸክለን ቀርተናል።

ዛሬም በኋላ ቀሩ አሠራር እየተጓዝንባቸው ካሉት መንገዶች መካከል በአትሌቲክስ ስፖርት ተሰጥኦን የምንለይበት መንገድ ነው። ምንም እንኳ በኋላ ቀሩ አሠራራችን  ውጤት እያስመዘገብን ቢሆንም አሁን ካለው የተሻለ ውጤት እንዳናስመዘግብ እና ባለተሰጥኦ አትሌቶች እንዲባክኑ ማድረጉ ግን የማይካድ ሀቅ ነው፡፡

 

ስፖርት የተሰጥኦ እና የከፍተኛ ልምምድ ውጤት ነው፡፡ የአትሌቲክስ ተሰጥኦ ማለት አንድ ስፖርተኛ ሲወለድ በተፈጥሮው ይዞት የሚመጣው አካላዊ ባህሪ፣ የጡንቻ ስሪት፣ የጊዜ እና የቦታ ግንዛቤ፣ ውስጣዊ ስሜት እና የመሳሰሉት መሆኑን የዓለም አትሌቲክስ በተሰጥኦ ልየታ ላይ የሠራው የዳሰሳ ጥናት ያመለክታል።

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት ያለው የተሰጥኦ መለያ መንገድ ዛሬም ከኋላ ቀሩ ስርዓት አልተላቀቀም። የመሬት አቀማመጥ እና የአየር ፀባይ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረገ ነው። አብዛኞች አትሌቶች የሚፈለፈሉት ከፍታ ካላችው መልክዓ ምድር ሲሆኑ የሀገራችን የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት እና ክለቦችም ከባህር ወለል በላይ ከሁለት ሺህ 800 ሜትር ከፍታ በላይ ነው የሚቋቋሙት። ይህም ጠንካራ ልብ እና የደም ቧንቧ (Cardiovascular system) እንዲኖራቸው ያደርጋል። እንዲሁም ከፍተኛ ጥንካሬ እንደሚያላብሳቸው ይነገራል።

 

በገጠሩ የሀገራችን ክፍል ተማሪዎች በእግራቸው ወደ ትምህርት ቤት መጓዛቸው በተፈጥሮ ጽናትን እንዲያዳብሩ ያደርጋቸዋል። ታዲያ ይህን የገጠር አኗኗር የተሰጥኦ መለያ ተደርጎ የሀገራችን አትሌቲክስ ባለሙያዎች ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፤ አሁንም እየተጠቀሙበት ነው። ምንም እንኳ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መቀዛቀዝ ቢታይበትም የትምህርት ቤቶች ፣ የክልሎች እና የዞኖች ውድድር በአትሌቲክስ ስፖርት ተሰጥኦን ለመለየት የሚያግዘው ዘዴ መሆኑን ከአሚኮ በኵር ስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኝ አማረ ሙጬ ይናገራሉ።

 

በዘመናዊ የአትሌቲክስ ስፖርት ተሰጥኦን መለየት አሁን ላይ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየሆነ ካለው አሠራር ጋር በእጅጉ የተራራቀ ነው። በለጋ እድሜአቸው በተፈጥሮ ብቃት እና ተሰጥኦ ያላቸውን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መለየት፣ መምረጥ፣ ማሳደግ እና ወደ ከፍተኛ ደረጃ የማሸጋገር ሂደት አሉት- በዘመናዊው አሠራር። ለአብነት በአሜሪካ፣ አወስትራሊያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ተሰጥኦን ለመለየት አካዳሚዎችን እና ሌሎች የስልጠና ፕሮግራሞችን እንደሚጠቀሙ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል። የዘርፉ ባለሙያዎች በቴክኖሎጂ በመታገዝ ቁጥራዊ መረጃዎችን በመተንተን ተሰጥኦን ይለያሉ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬኒያ፣ ዩጋንዳ እና በሌሎችም ያላደጉ ሀገራት መደበኛ እና ዘመናዊ ያልሆነ የምልመላ መንገድ የሚጠቀሙ ሲሆን የመሬት አቀማመጥን እና የአየር ጸባይ ሁኔታዎችንም መሰረት ይደረጋሉ። እንዲሁም ዘረመል፣ ከፍተኛ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት፣ የታዳጊ ወጣቶች ውድድር ተሰጥኦን ለመለየት የሚረዳ ሌላኛው ዘዴ ነው። ይህን ሁሉ ሂደት ቢያልፉም ግን በሀገራችን ትክከለኛ ባለተሰጥኦ ስፖርተኞች ይገኛሉ ማለት እንዳልሆነ አሰልጣኝ አማረ ተናግረዋል።

 

በሁሉም አካባቢ ያሉትን ባለተሰጥኦ አትሌቶች ለማግኘት የተደራሽነት ችግር አለ፤ አትሌቶች በተሰጥኦቸው ከተለዩ በኋላ ድጋፍ የሚያደርግላቸው የመንግስት አካል ወይም ግለሰብ ባለመኖሩ ብዙ ርቀት ሳይጓዙ ወደ ሌላ የሙያ ዘርፍ መቀላቀላቸውም እንደ ችግር ይነሳል። በሁሉም ቦታ ፍትሐዊ አሠራር ባለመኖሩ ብቁ እና ባለተሰጥኦ ስፖርተኞች በትክክል ተለይተዋ ዘርፉን እንዳይቀላቀሉም ምክንያት ሆኗል።

ተሰጥኦን መለየት አትሌቶች በሚፈልጉት ዘርፍ እና ርቀት እንዲሰማሩ ይረዳቸዋል። ከአካላዊ ባህሪያቸው ጋር የሚስማማ ስልጠና  እንዲያገኙ እና ለጉዳት እንዳይጋለጡ ያግዛቸዋል። ተሰጥኦን ማወቅ እና ማሳደግ አንድ አትሌት ለስፖርቱ የሚኖረው ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ከፍ እንዲል ያስችለዋል ብለዋል-ባለሙያው።

ብቁ እና ባለተሰጥኦ ስፖርተኞችን በተገቢው መንገድ መለየት ከፍተኛ አቅም ባላቸው አትሌቶች ላይ ብቻ በማተኮር ውጤታማ እና በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ያግዛል። ሌሎችም ባለተሰጥኦ አትሌቶችንም በማነሳሳት ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ያስችላል። በዘመናዊ የአትሌቲክስ ስፖርት ተሰጥኦን መለየት ቀላል ሳይሆን ውስብስብ ሂደት ነው። ዛሬ የትኛው አትሌት ብቁ እንደሆነ መለየት ብቻ ሳይሆን ወደፊት የትኛው አትሌት ተፎካካሪ እንደሚሆን መተንበይ ጭምር ነው።

 

በዘመናዊ አትሌቲክስ ተሰጥኦን መለየት የተለያዩ መመዘኛዎች እንዳሉት የተናገረው ባለሙያው ከእነዚህ መካከል የአትሌቶች የሰውነት አሠራር አንደኛው ነው። ይህም አንድ አትሌት ረጅም የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ለመቋቋም የሚያስችለውን የልብ እና የደምን ቧንቧ ጽናትን (Cardiovascular endurance) ያሳያል። የጡንቻ ጥንካሬ እና ኃይል (Muscular strength & power) እንዲላበስ ያደርገዋል። እንዲሁም ተለዋዋጭነትን እና የሰውነት ስብጥርንም ያካትታል። ተለዋዋጭነት (Flexibility) ጉዳትን ለመከላከል እና የእንቅስቃሴ መጠንን ለመጨመር የሚረዳ ሲሆን የሰውነት ስብጥር (Body composition) ደግሞ የጡንቻ እና የስብ መጠን ለአትሌቲክስ ስፖርት አስፈላጊ በመሆኑ ተሰጥኦን ለመለየት የሚያስችል ዘመናዊ ስልት ነው፡፡

 

ሌላኛው የአትሌቶችን እንቅስቃሴ ማጥናት ነው። የእንቅስቃሴ ትንተና፣ የኃይል ሰሌዳዎች እና የጡንቻ አጠቃቀምን እና ቅንጅትን ለመለየት የሚያስችለውን “ኤሌክትሮሚዮግራፊ” መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ባለሙያው ያስረዳል። ባለተሰጥኦ አትሌቶችን ለመለየት ከሚያስችሉ መመዘኛዎች መካከል የእውቀት እና ክህሎት መለኪያዎችም ይገኙበታል። ውሳኔ አሰጣጥ፣ የግንዛቤ ትኩረት እና ምላሽ አሰጣጥ አትሌቶች የሚገመገሙበት የእውቀት ችሎታ ነው። በቴክኒክ ክህሎታቸው፣ በስነልቦና ደረጃቸውም ሌላኛው ብቁ እና ባለተሰጥኦ ስፖርተኞችን ለመለየት ከሚያግዙት መካከል ይገኝበታል።

 

እንደ ዓለም አትሌቲክስ መረጃ ልዩ አቅም ያላቸውን ወጣት አትሌቶች መለየት እና ወደ ሚስማማቸው ዘርፍ እና ርቀት ለስልጠና ማመቻቸት በዘርፉ የማይቋርጥ የትውልድ ቅብብሎሽ ለመፍጠር ያግዛል። ተሰጥኦን ከስነ ምግባር ጋር በማዛመድ በመጀመሪያው ሂደት ባለሙያዎች ባለተሰጥኦዎችን መለየት እንዳለባቸው የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያስነብባል።

አካላዊ ምርመራን በማድረግ፣ ብቃታቸውን እና የስነ ልቦና ደረጃቸውን በመገምገም፣ የእድገት ደረጃቸውን በመከታተል እና ለስፖርቱ ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር እና ቁርጠኝነት በመስፈርቱ በማካተት ተሰጥኦን መለየት ይቻላል።

 

ተሰጥኦን ለመለየት በሀገራችን ያለው ልምድ ዘመናዊ ወይም ሳይንሳዊ አለመሆኑን አሰልጣኝ አማረ ያብራራሉ። “አሁን ላይ ተሰጥኦን ለመለየት እየተጠቀሙበት ያለው መንገድ ጊዜው እየሻራቸው ባሉ መንገዶች ነው፤ እንደ ሀገር ፕሮጀክቶች፣ ክለቦች እና ማሰልጠኛ ማዕከላት እየተጠቀሙበት ያለው ከሳይንሳዊው መንገድ ፍጹም የተለየ እና ኋላ ቀር ነው። ለምሳሌ የአንድን አትሌት አቅም ለመለየት ምን ያህል ከፍታ እንደሚዘል እንፈትሻለን” ሲል ያስረዳል አሰልጣኝ አማረ።

 

ዘመናዊ ለማድረግ አሁን ላይ ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉ የተናገሩት ባለሙያው በአትሌቲክስ ስፖርት ብቁ እና ባለተሰጥኦ ስፖርተኞችን ለመለየት የሚያስችል መንገድ ገና አልተጀመረም ብለዋል። የቴክኖሎጂ አለመኖር፣ መንግስት እና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት አለመስጠታቸውም ዛሬም በቆየው ኋላቀር አሰራር እንድንቀጥል አድርጎናል ባይ ናቸው። ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ውድ በመሆናቸው በግለሰብ ደረጃ ሊገዙ ባለመቻላቸው ችግሩን ለመፍታት የመንግስትን መልካም ፈቃድ ለመጠበቅ እንገደዳለን። ታዲያ በሀገራችን ብቁ እና ተተኪ አትሌቶችን በብዛት እና በጥራት ለማፍራት ተሰጥኦን ለመለየት የሚያስችል የአሰራር  ስርዓት  መዘርጋት፣ የስልጠና መንገዱን እንደገና ማጤን እና ሳይንሳዊ መንገድን መከተል እንደሚገባ ባለሙያው  ምክረ  ሃሳባቸውን  አስቀምጠዋል።።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here